18/09/2026
ዲጂታል አጀንዳ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት - የቱሪዝም አዲስ ቅኝት!
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ39ኛ ጊዜ በመስከረም ወር በልዩ ልዩ ኩነቶች የሚከበረው የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በደመቀ ሁኔታ ሊከበር ዝግጅቱ ተጠናቋል። የዘንድሮው የቱሪዝም ቀን "Digital Agenda and Artificial Intelligence to Redesign Tourism" ወይም "ዲጂታል አጀንዳ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት - የቱሪዝም አዲስ ቅኝት" በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፣ ይህም የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል።
መስከረም ሀገራችን ኢትዮጵያ በአደይ አበባ አጊጣ፣ በተፈጥሮ ውበቷ ድምቅ ብላ ለዓለም የምትገለጥበት ልዩ ወር ነው። በዚህ ወር በሚከበረው የቱሪዝም ቀን፣ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ሀብቶች በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻነቷን በፅኑ መሰረት ላይ የምትገነባበትና አሰራሯን የምታዘምንበት ወርሀ መስከረም ነው።
በተመሳሳይ በዚህ ወር በዩኔስኮ የማይዳሰሱ የዓለም ቅርስ ሆነው የተመዘገቡት የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ መንፈሳዊና ባህላዊ ስነ-ስርዓት፣ የገዳ ስርዓት የላቀ መገለጫ የሆነው የኢሬቻ እንዲሁም የወላይታ ህዝብ የዘመን መለወጫ የሆነው የጊፋታ በዓል ይከበራሉ። እነዚህ ታላላቅ ባህላዊና መንፈሳዊ በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ የሀገራችንን ጥንታዊ ስልጣኔ፣ እርቅ፣ ፍቅርና የማህበራዊ እሴት ጥበባት ለዓለም የሚያበስሩ ድንቅ ህያው ቅርሶቻችን ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃትና የታደልነውን የተፈጥሮና ታሪካዊ ሀብት በብቃት ለመጠቀም ሰፋፊ የመሰረተ ልማትና የአሰራር ማሻሻያዎችን እያከናወነ ይገኛል። የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የአዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ግንባታ፣ የዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋት እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፉን በዘመናዊ መልኩ ለመቅረፅና የጎብኚዎችን ልምድ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው።
ዲጂታል አጀንዳዎችንና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፋችንን አዲስ ቅኝት ማስያዝ የሁላችንም ትኩረት ሊሆን ይገባል። በዚህ ወር ሁላችንም የሀገራችንን ድንቅ ባህሎችና መስህቦች በመጎብኘት፣ እንግዶቻችንን በመቀበልና የቱሪዝም ሀብቶቻችንን በዘመናዊ መንገድ በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ገፅታ ከፍ እናድርግ፤ የሀገራችን የቱሪዝም አምባሳደር እንሁን!
የቱሪዝም ሚኒስቴር-ኢትዮጵያ Ministry of Tourism-Ethiopia