Concerned Irobs/ተቆርቋሪ ኢሮቦች

  • Home
  • Concerned Irobs/ተቆርቋሪ ኢሮቦች

Concerned Irobs/ተቆርቋሪ ኢሮቦች Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Concerned Irobs/ተቆርቋሪ ኢሮቦች, Social service, .

20/01/2025

The “Suruxso” people (ሱርክሶ ሕዝብ), correctly referred to as “Suri Kiso” (ሱሪ ኪሶ), are a group of Saho origin from the Buri Peninsula near the Red Sea. The name “Suri Kiso” in Saho means “descendants of Suri,” with “Suri” being the person’s name and “Kiso” meaning clan or descendants. Thus, the name “Suri-Kiso” signifies the descendants of Suri from Buri.

Their history traces back to the 6th century when two individuals migrated to the Irob region, specifically to Maebino (ማዕቢኖ) from the Buri (ቡሪ) Peninsula. One of these individuals, named Suri, became the namesake of the people, and his original tribe in Buri is known as Serwan (ሰርዋን). The Serwans (ሰርዋን), Turan (ጣሩዓን/ጣሩዓ), and Hazwan (ሓዝዋን/ሓዞ) are known Saho tribes in the region, particularly Eritrea. Maebino is situated a few kilometers from Assimba Mountain and is in close proximity to the Gundagundo Monastery and Alitena Town.

Maebino is notable for being the home of Abba Zewengel’s Meskele Kirstos Church, which was constructed in the 6th century during the reign of Emperor Geberemeskel, the son of Emperor Kaleb. Suri is believed to have been baptized in Maebino and was given land around Sebeya where the Suri-Kiso established themselves. Buri and the wider Buya and Galelo region are known for being some of the oldest settled regions in the world.

THE FRAGMENTED IROB CAN’T SURVIVE! The Irob community, an ethnic minority in Tigray, Ethiopia, has faced significant cha...
01/01/2025

THE FRAGMENTED IROB CAN’T SURVIVE!
The Irob community, an ethnic minority in Tigray, Ethiopia, has faced significant challenges over the past decades. In addition to the assimilation and fragmentation issues that have plagued the Irob since the rise of the TPLF, the 1998 invasion by Eritrean forces marked a devastating turning point. This invasion left the Irob economically and socially shattered. The aftermath of the 1998-2000 occupation and war saw the region remain a militarized zone until 2020, trapped in a state of no-war-no-peace due to contested claims by Eritrea. This prolonged militarization hindered strategic recovery projects and created constant anxiety and trauma among the Irob people, who lived in fear of another war breaking out at any moment. Consequently, many Irob youth fled the region, falling prey to human trafficking networks. As they feared, the 2020 Tigray war erupted, during which Eritrean forces re-occupied the region and committed heinous crimes.

THE FRAGMENTED IROB CAN’T SURVIVE!

05/04/2022

ቢቢሲ ከመቀሌ ነዋሪዎች አገኘሁ ባለው መረጃ

✔ በከተማዋ መቶ ኪሎ ጤፍ ከ 7,040 ብር ላይ ሆኗል።
✔አንድ ሌትር ነዳጅ አስከ 100 ብር ድረስ ይሸጣል።
✔ለአንድ ጉዞ የባጃጅ ተሳፋሪዎች እስከ 100 ብር ድረስ ያወጣሉ
✔ የመኪና ግዢ ፍላጎት እጅግ ስለቀነሰ 800, 000 ብር ሲሸጡ የነበሩ መኪኖች በ350,000 ብር ድረስ እየተሸጡ ነው።
✔24 ካራት የጣት ቀለበት ወርቅ ከ 3,200 ብር በላይ ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን በከተማዋ ከ620 ብር በታች እየተሸጠ ነው።
✔ትራንስፖርት ውድ ስለሆነ በከተማዋ ሳይክል የሚነዳ ሰው በዝቷል።
❤በዚህም የብስክሌት ዋጋ በጣም ጨምሯል።

ህይወት በመቀሌ!
❤ አንድ የመቀሌ ነዋራ የሆኑ አባት ከBBC አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዲህ ይላሉ።
"በየቀኑ በህይወት ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘት ከፍተኛ ጭንቀት አለው የሁለት ትንንሽ ልጆች አባት እንደመሆኔ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ሁሉ አለማሟላቴ ልቤን ሰብሮታል ባንኮች ስለተዘጉ ያለኝን ገንዘብ አውጥቼ መጠቀም ባለመቻሌ ምንም ማድረግ አልቻልኩም እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ ነዋሪዎች ይህንኑ ፈተና እየተጋፈጡ ነው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረትም አለ ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ አካውንቴ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ማውጣት ባለመቻሌ ከጓደኞች እና ዘመዶች ብር እየተበደርኩ ለቤተሰቤ ምግብ ለመግዛት ተገድጃለሁ።
✍️በውጭ ሃገር ያሉ ዘመዶቻችን መርዳት ቢፈልጉም የቴሌኮም አገልግሎቶች ስልክና ኢንተርኔት በመቋረጣቸው ይህንንም እርዳታ ልናገኝ አልቻልንም ይባስ ብሎ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ንሯል ዋነኛ ምግብ የሆነውን ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣በርበሬና ዘይት ዋጋ የማይቀመስ ሆኗል ከአመት በፊት 100 ኪሎግራም ጤፍ ወደ 4 ሺህ 200 ብር ገደማ ይሸጥ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን 7 ሺህ 600 ብር እየተሸጠ ነው አቅሙ ያላቸው አነስተኛ መጠን ያለው ጤፍ ገዝተው ከማሽላና ስንዴ ዱቁት ጋር በመቀላቀል እንጀራ ይጋግራሉ። ሆኖም ለበርካታ ነዋሪዎች ጤፍ መግዛት የማይታሰብ ነው።"
"በትግራይ ለምግብነት የማይውሉ የነበሩ ፍራፍሬዎች መንገድ ላይ እየተሸጡ ይገኛሉ በየግቢያችን አትክልት እንድንተክል ተነግሮን እነሱንን እየኮተኮትንና እያሳደግን ነበር። ችግሩ ግን ውሃ ማግኘት አልቻልንም። ቀደም ብሎ ለሳምንት የሚሆን 200 ሊትር የሚይዘውን በርሜል እንገዛ ነበር በአሁኑ ወቅት ግን እሱን ለመግዛት አቅሙ የለንም።
❤ስለዚህ ውሃ የምናመጣው ጥልቀት ከሌላቸው ጉድጓዶች እየቀዳን ነው።ለልጆች አዲስ ጫማ፣ ልብስ መግዛት እና ስጋ መብላት ቅንጦት ሆኗል። በመቀለ የውሃ እና የመብራት አገልግሎት የተገደበ ነው፤ ቀኑን ሙሉ ሲመጣና ሲጠፋ ነው የሚውለው። አንዳንድ ጊዜም ያው መብራት ሳናገኝ ቀናቶችን እናስቆጥራለን። በርካታ ነዋሪ እየሰራ አይደለም፤ ከስራ ውጭ ሆኗል። በርካታ ሱቆችና የንግድ ማዕከላትም ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው ወይም የሚሸጡት እቃዎች በማጣታቸው ተዘግተዋል። እነዚህን መከራዎች ለመወጣት ነዋሪዎች እንደ መኪና፣ የቤት እቃዎች እና ጌጣጌጦችን በኪሳራ ለመሸጥ ተገድደዋል። ከእነዝህ ብዙዎቹ ልጆች የያዙ እናቶች ናቸው። የጤና ማዕከላትም መድኃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ቁሳቁሶች አልቆባቸዋል።"
"ስር የሰደደ የጤና እክል ያለባቸው ህመምተኞች በመድኃኒት እጦት ምክንያት እየሞቱ ነው። የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ነዋሪዎች ደግሞ የጸረ ኤች አይቪ መድኃኒቶችን የሚያገኙት አንዳንድ ጊዜ ነው። በትግራይ ዘንድ ይከበሩ የነበሩና የማህበረሰቡ መገለጫ የሆኑት ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ሰርግና ሌሎች ድግሶች የሩቅ ጊዜ ትዝታ ሆነዋል። በየቀኑ ምን አደርጋለሁ? ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት አምሽቼ ነበር የምተኛው። ማታ፣ ማታ መሰብሰብ የቻልኳቸው ዜናዎች በሙሉ አዳምጣለሁ፤ ቪዲዮዎችንም አያለሁ። በቅርብ ቀናት የተከሰቱ ዜናዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው።"
"የኢንተርኔት አገልግሎት ስለሌለ ይልቁንም ቪዲዮዎችንና በድምፅ የተቀዱ ዜናዎችን የሚሸጡ ሱቆች ጋር እሄዳለሁ። እያንዳንዱን ቅጅ ወደ 10 ብር ገደማ ይሸጡታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ መፅሃፎችን አነባለሁ፣ ከጎረቤቶቼ ጋር እጫወታለሁ ወይም በእግሬ እራመዳለሁ። በመኪና መንቀሳቀስ አይታሰብም። አንድ ሊትር ቤንዚን ከጦርነቱ በፊት በነዳጅ ማደያዎች 22 ብር ይሸጥ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሊትር 515 ብር እየተሸጠ ይገኛል። በርካቶች ብስክሌት መጠቀም ቢጀምሩም ነገር ግን ብስክሌቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተወድደዋል። እዚህ ያለው ህዝብ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይፈልጋል እናም ባለፈው ሳምንት የተኩስ አቁሙን ስንሰማ በጣም ተደስተን ነበር።ሆኖም መሬት ላይ ባለው ኑሯችን ላይ ምንም አይነት ለውጥ አላመጣም፤ ምንም እንኳን የእርዳታ ጭነት መኪኖች ወደ ክልሉ እየመጡ ነው ቢባልም። ባንኮች ገና አልተከፈቱም አንዳንዶችም ተኩስ አቁም "ባዶ ቃል" ነበር በሚል እየተበሳጩ ይገኛሉ። በህይወት በመቆየቴና ታሪኬን ለናንተ በማካፈሌ ደስተኛ ነኝ፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በርካቶች ከኔ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉና አንዳንዶቹም እየሞቱም እንደሆነ አውቃለሁ። ምናልባት ከዚህ ሁሉ በጎ ነገር መጠቀስ የሚገባው የህዝቡ እርስ በርስ መደጋገፍና መረዳዳት ነው። "ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል" የሚል አባባል አለ እናም ነዋሪው ይህንን አባባል አጥብቆ ይዟል። ነገ እንደሚራቡ እንኳን ቢያውቁትም ማህበረሰቡ ያለውን ተካፍሎ ነው የሚበላው። አብረን ለመትረፍም ተባብረን ቆመናል።"

"እርሱ ያውቅልናል ልጄ! ደህና_ሁን!"
ሰላም ለኢትዮጵያ

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር አራትከበየነ ገብራይ/ደንማርክ  ሕዳር 2014 ዓ.ም.በ1968ቱ የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ የተሓህት ተወካይ ገለጻና የኢሮብ ተሰብሳቢው መልስ፣...
05/12/2021

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር አራት

ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ ሕዳር 2014 ዓ.ም.

በ1968ቱ የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ የተሓህት ተወካይ ገለጻና የኢሮብ ተሰብሳቢው መልስ፣

በቀጥታ ወደ የህወሓት ተወካይ ድርጅቱን ለማስተዋወቅ ያደረገው ገለጻና ለገለጻው ተስብሳቢው የሰጠው መልስ ከመግባቴ በፊት፣ በወቅቱ ተሓህት በኢሮብ ወረዳ የነበረው ይዘት፣ በወቅቱ የነበረው የኢሮብ ህዝብ ስነልቦና ምን ይመስል እንደነበረ ባጭሩ መጥቀስ ሃቁን ለማወቅ ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች እንደ መነሻ ሊሆን ስለምችል፣ እንዲሁም የአንድ ወገን (የህወሓት) ፕሮፓጋናዳና የነሱን ትርክት ብቻ ከመስማት ውጭ ሌላ አማራጭ ለሌላቸው አንባቢዎቼም በሌላ በኩል ያለውንም አይተው የራሳቸው ፍርድ ለመስጠት ስለሚጠቅም ባጭሩ ጠቅሼ ወደ ዋናው ርእሴ እገባለሁ።
ሀ) በወቅቱ ተሓህት በኢሮብ ወረዳ የነበረው ይዞታ፣

ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት)፤ ከ1972 በኋላ ስሙን ወደ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የቀየረው፤ ትጥቅ ትግሉን የጀመረው በ1967 ዓ.ም. በየካቲት ወር በምዕራብ ትግራይ ሽረ አውራጃ ደደቢት በረሃ ላይ ሲሆን፤ ወደ ምስራቅ ትግራይ (ዓጋመ አውራጃ) የመጣው በ1968 ሕዳር (ከ9 ወር በኋላ) ነበር። ተሓህት ወደ ዓጋመ አውራጃ እንደመጣ ዋና ቤዙን ያደረገው በሱቡሓ ሳዕሲዕ ወረዳ ልዩ ስሙ ማርዋ በሚባል አከባቢ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ ልክ ወደ ዓጋመ እንደመጣ በኢሮብ ወረዳም ልዩ ስሙ ዋርዓትለ በሚባል ቀበሌ “ገሪማት ኢንዳዓርቶ” (የገሪማ ዋርካ) ላይ ሰፈሩን በማድረግ ለአንድ አነስተኛ ቡድን የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና ሰጥቷል። ከዚህ አጭር በዋርዓትለ ወታደራዊ ስልጠና (ታዕሊም) መስጠት በኋላ ግን የኢሮብ ወረዳን ሙሉ በሙሉ ለቆ በመውጣት እንቅስቃሴውንና የማደራጀት ስራውን ያደርግ የነበረው ትግርኛ ተናጋሪ በሚኖርበት አከባቢ ላይ ብቻ ነበር።
ስለሆነም ከ1968 ሕዳር - 1970 ግንቦት በነበረው ጊዜ ተሓህት በኢሮብ ወረዳ በዋርዓትለ ቀበሌ ላጭር ጊዜ ከሰጠው ስልጠናና በዓይጋ (በዛጋብላ በረሃ ጫፍ) የነበረ አንድ ለረጅም ጊዜ የተለቀቀ ቤት ውስጥ በክፍለ ህክምና ስም ከነበሩት ጥቂት አባላት ውጭ በኢሮብ ወረዳ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሆነ ድርጅታዊ ስራ አልነበረውም። ለምን የሚል ጥያቄ መነሳቱ ስለማይቀር ምክንያቶቹም፣
1. በወቅቱ በአከባቢው ከማእከላዊ ኮሚቴ እስከ ተራ አባላት ብዙ የኢሮብ ብሄረሰብ ተወላጆች የነበሩበት ኢህአፓ/ሰ ዋና ቤዙን በኢሮብ/አሲምባ አድርጎ በምስራቃዊ ትግራይ ይንቀሳቀስ ስለነበረና፤ በውስጡ እንደነ ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ፣ ገብረስላሰ ተስፋይ/ገረይ፣ ተስፋይ ሃይለማሪያም. . . ወዘተ የመሳሰሉ ስመ ጥር የብሄረሰቡ ተወላጅ መሪዎች ስለነበሩት ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ ስለነበረ፣
2. ኢህአፓ/ሰ ገና ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅታዊ ስራውን በህቡእ በጥልቀት እየሰራ በህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ስለነበረ፤ ድርጅቱ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድኑን በ1967 አጋማሻ ላይ ወደ አከባቢው አስገብቶ ይንቀሳቀስ ስለነበረና፤ አልፎ ተርፎም በህዝቡ ጥያቄ መሰረት ህዝባዊ አስተዳደር መስርቶ ስለነበረ፤
3. ከጥቅት የትግርኛ ተናጋሪው አጎራባች አከባቢዎች ውጭ አብዛኛው የኢሮብ ህዝብ ትግርኛ የማይሰማ ሳሆ ተናጋሪ ህዝብ ስለነበረ፤ የተሓህት ታጋዮች ከህዝቡ ጋራ የሚገባቡበት ቋንቋ አለመኖሩ ደግሞ ሌላው ትልቁ ምክንያት ነበር።
ለ) የያኔ የኢሮብ ህዝብ ይዘትና ስነልቦና፣

በቁጥር ሶስት ዕትም በውሱን እንደተጠቀሰው፤ ያኔ የነበረው የኢሮብ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው አንድነቱና ኢሮባዊ ማንነቱ ዋና ምሶሶውች የሆኑ እሴቶች ነበሩት፡፡ ለምሳሌ ያህል፤ የራሱን ሚስጥር በውስጡ መጠበቅ፣ አንድን የኢሮብ ተወላጅ የፈለገ ጥፋት ቢያጠፋ ራሱ መቅጣት እንጂ ለውጭ አሳልፎ አለመስጠት፣ ማንኛውም በውስጡ የሚነሱ ችግሮች/ልዩነቶች በውይይት መፍታት፣ በውይይት ሊፈቱ ለማይችሉ ቅራኔዎች የሚፈታበት በጣም የዳበረ የሽምግልና ባህል የነበረው፣ ታናሽ ታላቁን የማክበር፣ ታላቅም ለታናሹ አርአያ የመሆን፣ . . . ወዘተ. ባህልና ስነልቦና እንደተጠበቀ ነበር። ያኔ የነበረው የኢሮብ ህዝብ በ% ለማስቀመጥ ባልችልም በጣም ውሱን ከትግርኛ ተናጋሪ አጎራባች በሆኑ አከባቢ ከሚኖረው ውጭ አብዝሃ የኢሮብ ህዝብ ትግርኛ መናገር ቀርቶ የማይሰማ ሳሆ ተናጋሪ ህዝብ ነበር። በኢኮኖሚ ደረጃም ከእርሻው በተጨማሪ ሲገለገልበት የነበረው የእንስሳ ርቢ እያሽቆለቆለ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙዎች ደህና እንደ ፍየል፣ ከብት፣ የንብ ርቢ ተጠቃሚዎች ስለነበሩ፤ ምንም ስደት የሚባል ነገር የማያውቅ፣ በጣም ውሱን በጣት የሚቆጠሩት በትምህርትና በስራ ምክንያት አከባቢውን ለቀው ከሚኖሩት ውጭ የተቀረው ከሌሎች ጎረቤቶቹ ብዙ ንኪኪና ግኑኝነት ሳይኖረው በወረዳው ተወስኖ የሚኖር ውሁድ ህዝብ ነበር።
ሐ) የተሓህት ተወካይ ገለጻ፣ ለገለጻው የአቤቶ ዓዶዑማር መልስና የኢሮብ ተሰብሳቢው ግብረመልስ፣

1. መንደርደሪያ፣

በቁጥር ሶስት ዕትም እንደተገለጸው የቦካለማኮ ስብሰባ የተጠራበት ብቸኛ ምክንያት/አጀንዳ የቆየውን የመሬት ስሪት/ህግ በመሬት ለአራሹ አዋጅ መሰረት ለማሻሻል ነበር። ከዚህ አጀንዳ ውጭ ሌላ አጀንዳ የያዙ ሰዎች ወደ ስብሰባው ይመጣሉ የሚል ግምት ስብሰባን ባዘጋጁ የኢህአፓ ተወካዮዎች (በጓድ ገረይና እኔ) በኩልም በተሰብሳቢውም በኩል አልነበረም። ስለሆነም ከእኩለ ቀን በኋላ በግምት ወደ ሰባት ሰዓት አከባቢ ላይ ሁለት የተሓህት ታጋዮች ወደ ስብሰባው ሲመጡ ማየት ለሁሉም እንግዳ ነገር ነበር። በመሆኑም ሁለቱ ወደ ስብሰባው ቦታ ሲጠጉ የተሰብሳቢው ዓይንና ልብ ወደነሱ ሆነ። ይህ መሆኑ በሚገባ የተመለከቱት በስዓቱ ቆመው በመናገር ላይ የነበሩት ልጅ ብስራት ገብራይ፤ ንግግራቸውን አቁመው እሳቸውም የሁለቱን እንቅስቃሴ መከታተል ጀመሩ። የተሰብሳቢው ቀልብ በሙሉ ወደነሱ መሆኑን የተመለከቱ የተሓህት ታጋዮችም ዝም ብለው ወደ ስብሰባው መቀላቀልን ትተው ተጠግተው ቆሙ። ይህን በመታዘባቸው ልጅ ብስራት ገብራይ “ታይ የመተ ገዳክ ዲፈያ አከያ” (ለመጡ እንግዶች ተቀመጡ በሉዋቸው) አሉና ጓድ ገረይ የሳቸውን ሃሳብ ተቀብሎ የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች በተቀመጡበት በኩል እንዲቀመጡ ቦታ ሰጥቶኣቸው እነሱም ተቀምጠው ስብሰባው በልጅ ብስራት ንግግር ቀጠለ።
የቦካለማኮ ስብሰባ ለማዘጋጀት ወደ ሶስት ወር የፈጀ ዝግጅትና ብዙ ጥሪዎችም በተለያየ ጊዜ ይተላለፉ ስለነበረ፤ የተሓህት አባላትም ስለ ስብሰባው የመስማት ዕድል ክፍተኛ መሆኑ ምንም የማያጠራጠር ቢሆንም ለኛ ሳያሳውቁ ለምን በድንገት እኛ በጠራነው ስብሰባ ለመገኘት ፈለጉ የሚል ጥያቄ ግን ለሁላችን (ለኔ፣ ለጓድ ገረይ፣ ለተሰብሳቢውም) እንቆቁልሽ ስለነበረ ራሴን ጠይቄ መልስ ማፈላለግ ጀመርኩ። ወደያውኑ የመጡልኝ መልሶችም፣ አንደኛ በኛ በኩል የምናሳየው ሪአክሽንና (reaction) የምንወስደውን እርምጃ ለማየት/ለመለካት ሊሆን ይችላል፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢሮብ ህዝብ በዚህ ዓይነት የተሟላ የሶስቱ ኢሮብ (አድጋዲ-ዓረ፣ ቡክናይቲ-ዓረ፣ ሓሳባላ) ውክልና ያለው ስብሰባ ራሳቸው መጥራት ስለማይችሉ ዕድሉን ተጠቅመው ከኢሮብ ህዝብ ለመተዋወቅና የህዝቡን ስሜት ለማወቅ/ለመለካት ይሆናል የሚሉ ነበር። ከስብሰባው በኋላ ለጓድ ገረይ ይህን የኔ ግምቶች አንስቼለት እሱም ተመሳሳይ ግምት እንደነበረው፣ እስከመጡና ልጅ ብስራት እንዲቀመጡ እስከጋበዙዋቸውና ተስብሳቢውም በሃሳቡ እስከተስማማ ድረስ ህዝቡ እንዲወስን መተዉ ነው የሚሻለው በሚል ነው እንዲቀመጡ ያደረግኩት ብሎ ነገረኝ።
የዕለቱ ብቸኛ አጀንዳ የነበረው (የመሬት ስሪት ማሻሻል) ጉዳይ በግምት ወደ 9 ሰዓት አከባቢ ላይ እንዳለቀ ጓድ ገረይ የዕለቱ ስብሰባ መደምደሚያ ንግግር አደረግ። የመጡለት ጉዳይ ማለቁን ካወቁ ተሰብሳቢዎች የተወስኑትም ለመሄድ ተነሳሱ፡፡ ይህን ጊዜ ከተሓህት ታጋዮች አንዱ ከተቀመጠበት ተንስቶ በትግርኛ ለአጭር ጊዜ የመጣንበት ጉዳይ ለመግለጽ እባካችሁ አንዴ አድምጡን ብሎ ጠየቀ። ትግርኛ ይሰሙ ከነበሩት አንዳንዶቹ አሁን መሽቶብናልና ከፈለጋችሁ የራሳችሁ ስብሰባ ጥሩና ሌላ ጊዜ አነጋግሩን ብሎዋቸው ስሉ፤ ተቀምጠው የነበሩ ቀሪ ተሰብሳቢዎችም ለመሄድ መነሳት ጀመሩ። የህወሓት ተወካይ ለመሄድ የተነሳውን ተሰብሳቢ በራሱ ለማስቆም የምችልበት ዕድል እንደሌለው ሲያውቅ ለጓድ ገረይ ተሰባሳቢውን አንዴ እንዲያደምጠን አግባባልን ብሎ ጠየቀው። ጓድ ገረይም ለተናጋሪው እየመሸ ስለሆነ ንግግሩን እንዲያሳጥር ነግሮት፣ ለተስብሳቢው በሳሆ አንዴ አድምጡኝ ለሚል እንግዳ ዝም ብሎ ጥሎ መሄድ ባህላችን ስላልሆነ፣ ለመሄድ የጀመራችሁም የቆማችሁም አንዴ ቁጭ በሉና ላጭር ደቂቃ አድምጡት ብሎ ተናገረ፡፡ ለመሄድ መንገድ ጀምረው የነበሩ ተመልሰው፣ የቆሙትም ቁጭ ብለው የተሓህት ተወካይ ለተሰብሳቢው በትግርኛ ስለ ድርጅቱ (ተሓህት) የማስተዋወቅ ገለጻ ለመስጠት በተሰብሳቢው ማይኸ (mic) ቆመ።
የተሓህት ተወካይ ስለ ድርጅቱ ገለጻ ሲጀምር ከተሰብሳቢው የሚበዛው ትግርኛ የማይሰማ ስለነበረ አንዳንዶች በሳሆ “ታይ ኣምሓርቲ ኣይም ኪኒ ኣያነም” (ይህ ትግራዋይ ምን ነው እያለ ያለው) ብለው መጠየቅ ጀመሩ፣ ለነዚህ ጠያቂዎች ሌሎች ደግሞ “ኣምሓራ ዲዕታም መልሲ ኣካህ ኣሓየ ለክ ቲዕግስቲ ኣብኖይ” (ትግርኛ የሚችሉ መልስ ይሰጡታልና ትንሽ ትዕግስት እናድርግ) በማለት መለሱ።፣ ብዙዎችም ትግርኛ ስለማይሰሙም ትግርኛ የሚሰሙትም ገለጻው ስላልጣማቸውም በዚያ በተለመደው የኢሮብ ባህል መሰረት የተናጋሪው ሃሳብ ሳይጥማቸው ሲቀር የሚያደርጉት ትንንሽ ጠጠሮችን በመሰብሰብ ካንዱ እጅ ወደ አንዱ በማገላበጥ ከጠጠሮቹ ጋራ መጫወት ጀመሩ፣ ሌሎችም እርስ በርስ መንሾካሸክ ጀመሩ።

2. የተሓህት ተወካይ ድርጅቱን ለማስተዋወቅ የሰጠው አጭር ገለጻ፣

የተሓህት ተወካይ ተሰብሳቢው ልብ ብሎ እያዳመጠው እንዳልሆነ በተሰብሳቢው መካከል ከነበረው ሽኩሹክታ፣ የኢሮብ ህዝብ የተናጋሪው ንግግር ሳይጥመው ሲቀር በሚያሳየው/በሚሰጠው ግብረመልስ (ከጠጠሮቹ ጋራ መጫወት፣ ዓይኑንም ቀልቡንም ከታናጋሪው ማራቅ. . .ወዘተ) በግልጽ ቢገንዘብም/ብያይም፤ ይዞት የመጣው ድርጅቱን የማስተዋወቅ መልእክቱን ማስተላለፍና የተሰብሳቢው መልስ ማየት/መስማት ስለነበረበት መልእክቱን እንደሚከተለው ባጭሩ ገለጸ።
አንኳር አንኳር የተናጋሪው ነጥቦች፣

 ስማችን ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ይባላል፣
 ዓላማችን፣ ትግራዋይ ማንነት፣ ባህል፣ በአማራ ማንነትና ባህል እንዲዋጥ እየተደረገ ስለሆነ፣ ማንነታችን፣ ቋንቋችን እየተንቋሸሽና እየተናቀ ስለሆነ፣ ትግርኛ ቋንቋችን የዳበረና በስነጽሁፍ ደረጃም ሊጻፍና ይበልጥ ሊዳብር የሚችል ቋንቋ ሆኖ እያለ በቋንቋችን እንዳንጽፍ፣ እንዳንማርና እንዳንሰራበት በአማራ ገዢ መደብ እየተከለከልን ስለሆነ፣ አጠቃላይ ፖለቲካውም ኢኮኖሚውም በአማራ ገዢ መደብ ቁጥጥር ስር ስለሆነ ተጋሩ ከፖለቲካውም ከአኮኖሚውም እኩል ተጠቃሚነት ወደ ጠርዝ እየተገፋን ስለሆነ. . . ወዘተ. ከዚህ ሁሉ በአማራ ገዢ መደብ እየደረሰብን ካለው ብሄራዊ ጭቆና ለመላቀቅና የራሳችን ዕድል በራሳችን ለመወሰን በተሓህት የሚመራ ሁለገብ ብሄራው ትግል ማካሄድ እንደሆነ ገለጸ።
 በጥሪ ደረጃ፣ በአማራ ገዢ መደብ መሪነት በአማራ እየደረሰብን ካለው ብሄራዊ ጭቆና ነጻ ወጥተን የራሳችን ዕድል በራሳችን ለመወሰን ከፈልግን ያለን ብቸኛ አማራጭ ለነጻነታችን ራሳችን መታገል ብቻ ስለሆነ እናንተ (የኢሮብ ህዝብ) በተሓህት ስር ተደራጅታችሁ፣ ወጣቶች በቀጥታ ወደ ትጥቅ ትግሉ እንድትሳትፉ፣ አባቶችም በምክርም በሃሳብም የተሓህት ትግል እንድትደግፉ ጥሪ እናደርጋለን በማለት ንግግሩን ባጭሩ ጨረሰ።

አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ተሰብሳውን በመወከል ለተሓህት ተወካይ የሰጡት መልስ፣

የተሓህት ተወካይ ገለጻውን ከጨረሰ በኋላ ጓድ ገረይ ተናጋሪው በቀጥታ የተናገረው ለናንተ/ለተስብሳቢዎች ስለሆነ፣ በርግጥ ብዙዎች የቋንቋ ችግር እንዳለባችሁ ባውቅም ጥቂት ብትሆኑም ትግርኛ የምትሰሙ ስላላችሁ፤ ወንድሜ በተናገረው ላይ ሃሳብ/አስተያየት ያላችሁ አጠር አጠር እያደረጋችሁ ሃሳብ/አስተያየት ብትሰጡበትና ስብሰባውን ብንጨርስ ብሎ ሃሳብ/አስተያየት ያለው እንዲናገር ጠየቀ። በጥያቄው መሰረት ትግርኛ በሚገባ ያውቁ የነበሩት አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ በተቀመጡበት ሆነው ዋና ዋና መልስ የሚሰጥባቸው ነጥቦችን በማስታወሻው ጽፎ ነጥብ በነጥብ ከተሓህቱ ተወካይ ንግግር እየጠቀሱ ቀጥሎ የተቀመጠውን መልስ ሰጡ።
1. ሁሉም ነገር ከስም ስለሆነ የሚጀምረው፣ ስማችሁ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ከሚባል ተጋድሎ ሓርነት ህዝብታት ኢትዮዽያ ቢባል ጥሩ ነበር።
2. አንተ በግልጽ እንዳስቀመጥከው እናንተ/ተሓህት ይዞት የተነሳው ዓላማ የቆመው በትግራይ ጠቅላይ ግዛት ለምንኖር ህዝቦች ባጠቃላይ ሳይሆነ ለታጋሩ ብቻ ነው። የትግራይ ጠቅላይ ግዛት፣ የተጋሩ፣ የኢሮብ፣ አፋር፣ አገው፣ ኩናማ. . . ብሄረሰቦች የጋራችን መኖሪያ ሆኖ እያለ ፣ ከተጋሩ ውጭ ያለን ብሄረሰቦች በዚች ጠቅላይ ግዛት እንደምንኖር በንግግርህ አንድም ቦታ ላይ እንኳን አልጠቀስክም።
3. ሌላም በግልጽ እንዳስቀመጥከው ዓላማችሁ የተጋሩ ባህል፣ ማንነት፣ ቋንቋ (ትግርኛ) በአማራ ባህል ማነትና ቋንቋ ስለተረገጠ ማንነታችሁና ባህላችሁን አስከብራችሁ በቋንቋችሁ ለመናገርም ለመፃፍም እንድትችሉ ነው። ስለ ሌሎቹ ለጊዜው ልተውና በትግራይ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ኢሮብ የሚባል ልክ እንደ ተጋሩ የራሱ የሆነ ታሪክ፣ ቋንቋ (ሳሆ)፣ ማንነት፣ ባህል፣ ስነልቦና፣ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ህዝብ መኖሩን ለመሆኑ ታውቀዋለህ? ከንግግርህ እንዳዳመጥኩት የምታውቅ አይመስለኝም።
4. ከጥንት ጀምሮ አዎ የኢሮብ ብሄረስብ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት የምንኖር ህዝብ ነን። ትግራይ የኛ የኢሮቦች፣ የአፋር፣ የአገው፣ የኩናማና የተጋሩም የጋራ መሬታችን ነው። የማንነት ጉዳይ/ጥያቄ ከተነሳ ግን ልክ ተጋሩ የምትኮሩበት የራሳችሁ ትግራዋይ ማነነት እንዳላችሁ ሁሉ እኛ ኢሮብም የራሳችን በጣም የምንኮራበት ኢሮባዊ የራሳችን ማንነት አለን። ስለሆነም ማንነት ከተነሳ እኛ ኢሮብ እንጂ ተጋሩ አይደለንም ለወደፊትም አንሆንም።
5. ሌላ ስለ በቋንቋችሁ መናገርና መጻፍ አለመቻል፣ ባህላዊ ጭቆና በአማራ እንደሚደርስባችሁ ተናግረሃል። በቋንቋህ መናገር/መጻፍ አለመቻል ከተነሳ፣ የባህልና የማንነት ጭቆና ከተነሳ የኛ የኢሮብ ህዝብ ቋንቋ (ሳሆ) የሚረገጠው ገና “ቃላይ በዓንቱራ” እንደተሻገርን በትግርኛ ቋንቋ ነው። ባህላችንና ማንነታችን መንቋሸሽና መናቅ የሚጀምርውም ልክ የወረዳችን ጫፍ አልፈን ወደ ትግርኛ ተናጋሪው አከባቢ እንደደረስን ነው።
6. በግልጽ ቋንቋ አንተ ስለ ተጋሩ ማንነትና በተጋሩ በአማራ የሚደርሰው ጭቆና ነግረኸናል። ስለ በትግራይ የሚኖሩ ሌሎች ብሄረሰቦች እኛን ጨምሮ በተጋሩ ስለሚፈጸመው የማንነትና ባህል ጭቆና ግን ምንም ነገር አላነሳህም። በብሄር/በማንነት ደረጃ ከታሰበና በማንነት ደረጃ የሚደርስብን ጭቆና ለማስወገድ እንታገል ከተባለ እኛ ኢሮቦች ማንነታችንን ለማስከበር መታገል ያለብን ሩቅ ካሉት አማሮች ጋራ ሳይሆን በተግባር ጭቆናውን እዚህ እያደረሳችሁብን ካላችሁ ከናንተ ከተጋሩ ጋራ ነው መሆን ያለበት።
7. ስለሆነም እኛ ኢሮብች የናንተ ዓላማ መቀበል ማለት ኢሮባዊ ማንነታችን ራሳችን ደፍጥጠን አጥፍተን የተጋሩ ማንነት ተቀብለን ተጋሩ እንሁን እንደማለት ስለሆነ፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እንደ ኢሮብ ህዝብ ዛሬ ገብተንበት ካለነው ድህነት ለመውጣት ራሱ የቻለ ትግል ውስጥ ስለሆን፤ የናንተ ዓላማም ለዚህ ትግላችን ምንም እርባናም ስለሌለው ዓላማችሁ የምንቀበለው አይደልም በማለት መልስ ሰጡ።
እንደ ቆመ ሲያዳምጣቸው የነበረ የተሓህት ታጋይ “ኣቦይ ዓቢዪ እዙይ ናይ ውልቅኹም ሓሳብ ስለዝኾነ ናይ ካሎት ሓሳብ/ርእቶ ንስማዕ” (አባት ይህ የግልዎ ሃሳብ/አስተያየት ስለሆነ የሌሎች ሃሳብ እንስማ) ብሎ እንደተናገረ አቤቶ ዓዶዑማር በሳሆ “ኢኒ ዲኪህ አራዎክ ባቅሊ ዮህ ባሃ” (ቤቴ ልግባ በቅሎየን አምጡልኝ) ብለው ጠየቁ። ልክ ይህ የአቤቶ ዓዶዑማር ወደ ቤተ ልሂድ በቅሎየን አምጡልኝ እንዳሉ ጠጠር ይዞ ከጠጠሮቹ ጋራ ሲጫወት የነበረ ሁሉ ጠጠሮቹን በትኖ፣ ብዙዎችም ደግሞ የኢሮብ ህዝብ ድምጽ አልባ የተቃውሞዉ ማሳያ/መግለጫ ዜዴዎች አንዱ የሆነው ነጠላን ማራገፍ ዘዴን በመጠቀም፤ ነጠላቸውን እያራገፉ፣ “ደህና እደሩ” በመባባል ተሰብሳቢው ወደየ አከባቢው ተበተነ፡፡ የተሓህት 2ቱ ተወካዮች ወደ ሰበያ አቅጣጫ አቀኑ፡፡ ጓድ ገረይና እኔም ለአዳራችን ወደ ጊቢዳዎ ቀበሌ አቀናን።
ስለሆነም ለማጠቃለል ያህል የ1968ቱ የቦካለ-ማኮ ስብሰባ፤
 የኢሮብ ህዝብ በቆየ የዳበረ የውይይት ባህል መሰረት የቆየውን የመሬት ስሪት በአዲሱ የመሬት አዋጅ መሰረት ያሻሻለበት
 በኣዲሱ በተሻሻለው ስሪት መሰረት መሬት መቼ መክፋፈል እንዳለበት የተወሰነበት፣
 ለወደፊቱ አዲስ የእርሻ መሬት በተመለከተ አዲስ ህግ ያወጣበት (አዲስ የእርሻ ወንዞችን በመገደብ እንጂ ጋራዎችን በመመንጠር መሆን የለበትም የሚል ህግ)፣
 በኦና ስርዓት ዘመን የነበረው የዳበረ ዴሞክራሲያዊ የስብሰባ አካሄድ ባህልና ስነስርዓት የታየበት፣
 በዕለቱ በድንገት ወደ ስብሰባው ለመጡ የተሓህት ተወካዮች የቆየ የኢሮብ እንግዳ የመቀበልና የማክበር ባህል በግልጽ የታየበት፣
 የማንነት ጥያቄ ከተነሳ የኢሮብ ህዝብ ኢሮብዊ ማንነቱ ላይ ያለው የጸና አቋም በግልጸ ቋንቋ ለተሓህት ተወካዮች የተናገረበት፣
 በዚሁ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ በኢሮባዊ ማንነት ላይ በነበረው የጸና አቋሙ ምክንያትም በተሓህት ጥርስ ውስጥ የገባበት ታሪካዊ ስብሰባ ነበር።

ማሳሰቢያ ለአንባቢዎቼ፣
ሀ) ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ በሚል ርእስ በተከታታይ ከቁጥር አንድ እስከ አራት ያቀርብኩዋቸው መጣጥፎቼ በታሪካዊ ጭብቶች የተደገፉ ናቸው። እስካሁን ከተለመደው ስድብ ከተቀላቀለው የህወሓት ደጋፊዎች ስሜታዊ ሃሳቦች የዘለለ፤ ለጽሁፎቼ አንድም እዚህ ቦታ ያልከው ትክክል አይደልም ብሎ በጭብጥ የሞገተኝ የለም። ይህ ታሪክ እንጂ የግሌ ፖለቲካ አቋም ፕሮፓገይት ለማግረግ ስላይደለ ታሪካው መረጃ ይዞ ለሚቀርብ ትችት ሆነ ነቀፌታ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
ለ) በኔ እምነት የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ዛሬ ገብቶበት ላለው የህልውና አደጋ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም፤ በዋናነት ግን በ1968ቱ የቦካለማኮ ስብሰባ ላይ የኢሮብ ህዝብ በማንነት ጥያቄ የነበረው ግልጽ አቋም በህወሓት አመራር ከታወቀ ጀምሮ፤ የህወሓት አመራር የኢሮብ ህዝብ ኢሮባዊ ማንነትን በሂደት በማመናመን በተጋሩ እንድዋጥ (Assimilate) እንዲደረግ በተለያየ ጊዜ የሸረቡት ሴራዎችና የፈጸሙት ድርጊቶች ዋነኞቹ ናቸው የሚል ነው።
ሐ) ለዚህ እምነቴ እንደ ማስረጃ የምላቸው ማን ያርዳ. . . በሚል ርእስ በተከታታይ የጻፍኩዋቸው መጣጥፎቼና በዮሴፍ ዓዳዩ “ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃሮኖ” በሚል ርእስ በተከታታይ የተጻፉ መጣጥፎች የመልከቱ፡፡ እንዲሁም በአጠቃላይ ስለ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ይበልጥ ማወቅ ለምትፈልጉ፣ የኢሮብ አድቮካሲ አሶሴሽን ድረ-ገጽን እንድትጎበኙ በትህትና አሳስባለሁ።

የነገ ሰው ይበለን! በየነ ገብራይ/ደንማርክ

ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃሮኖ!! ክፍል አንድ፤ "የትግራይ የነፃነት ትግል" እና የኢሮብ ህዝብ ተቃርኖ አጀማመር ከዮሴፍ አዳዩ ጥቅምት 2014

13/11/2021

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር ሶስት፣

የ1968 ዓ.ም. የቦካለ ማኮ/ዓሊተና ታሪካዊ ስብሰባ አካሄድና ውጤቱ፣

ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ፣ ሕዳር 2014 ዓ.ም.

የስብሰባው አካሄድ፣

ከሶስት ኢሮብ (ኣድጋዲ-ዓረ፣ ቡክናይቲ-ዓረ፣ ሓሳባላ) ከ300 በላይ ተወካዮች የተገኙበት ታሪካዊው የቦካለ ማኮ ስብሰባ የተካሄደው በየካቲት የመጀመሪያ ሰሙን በ1968 ዓ.ም. ነበር። በኦና ስርዓት ወቅት ህዝባዊ ስብሰባዎች የሚመሩት በህዝብ በተመተረጠው ኦና ነበር። የኦና ስርዓት ከጣሊያን የሁለተኛ ወረራ በኋላ፣ በአፄ ኃ/ስላሴ በሃይል ፈርሶ ወረዳው በቀጥታ ከላይ በሚመደብ አስተዳዳሪ መተዳደር ከጀመረ በኋላ ደግሞ በዛው በመንግስት በሚመደብ አስተዳዳሪ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ ከ1966ቱ አቢዮት በኋላ በኢሮብ ከመንግስት የተመደበ አስተዳዳሪ በቦታው ስላልነበር ስብሰባው በቀጥታ ስብሰባውን በጠራው በኢህአፓ ተወካይ በጓድ ገብረስላሰ ተስፋይ/ገረይ መመራት ወይም ተሰብሳቢው የራሱ መሪ እንዲመርጥ ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ጓድ ገረይ የኢሮብ ህዝብ ከዘመኑ እድገት ጋራ መሄድ የምችል የኦና ስርዓት በኢሮብ መቀጠል አለበት የሚል ፅኑ እምነትና አቋም ስለነበረውና ይህ ደግሞ ከዚህ ስበስባ መጀመር አለበት ብሎ ስላመነና ስለወሰነ ስብሰባውን ራሱ መምራት ትቶ ተሰብሳቢው የራሱ ሊቀመንበር እንዲመርጥ ወሰነ። ስለሆነም በዙሪያው በነበሩ ዛፎች በትንንሽ ቡድኖች ተበታትኖ ተቀምጦ የነበረው ተሰብሳቢ ወደ አንድ አክባቢ እንዲሰበሰብ ጠይቆ ማኽል ላይ ቁሞ ለተሰብሳቢው ወደ ሁሉ አቅጣጫ በመዞር ሰላምታ ሰጥቶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፈ በኋላ ከኦና ስርዓት እስከ የአፄ ኃ/ስላሴ ስርዓት የነበረው የስብሰባ አካሄድ ምን ይመስል እንደነበረ ባጭሩ ጠቅሶ፣ የኦና ስርዓቱ ባህላችን መልሶ መገንባትና መዳበር እንዳለበት በመጥቀስ ለዕለቱ ስብሰባ ተሰብሳቢው የራሱ ሊቀመንበር እንዲመርጥ ጠየቀ።
በቆየው የኢሮብ ባህል መሰረት የዕድሜ ባለፀጋ፣ አዋቂና ልምድ ያለው ሰው ከሁሉም አስቀድሞ መናገር/ሃሳብ መስጠት የተለመደ አካሄድ ስለነበረ ተሰብሳቢው በዕለቱ በስብሰባው ተገኝተው በአንድ አካባቢ በተሻለ የዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠው ወደነበሩት እነ አቤቶ ዓዶዑማር ሓሊቦ ወልደገርጊስ (ዓዶዑማር ጎዒስ) ዓሊተና፣ ኦና ወልደገርጊስ ዎልዱ/ዓይጋ፣ ልጅ ንጉሰ ወልደጊዮርጊስ/ማጋዑማ፣ ልጅ አብራሃ ሓጎስ /አድጋዲ ዓረ፣ አቤቶ ተስፋይ ወልደሓንስ /ኮኮሖ/ሳብዓታ፣ ልጅ ብስራት ገብራይ ዒንዳይ/ሳራይቲ አራሕ. . .ወዘተ. አባቶች በምልክት አመላክቶ ከነሱ ውስጥ አንዳቸው እንዲናገሩ ተጠቆመ። በወቅቱ በቦታው ከነበሩ የዕድሜና የእውቀት ባለፀጎች፣ በዕድሜ፣ በእውቀትና ልምድም የላቁ የነበሩ አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ስለነበሩ አባቶችም እሳቸው እንዲናገሩ/ሃሳብ እንዲሰጡ ጠየቋዋቸው። አቤቶ ዓዶዑማር እርጅና በጣም ተጫጭኖአቸው፣ ዓይናቸው ታውረው ስለነበረ ቆመው መናገር ስላልቻሉ በተቀመጡበት ሆነው መናገር ጀመሩ።
አቤቶ ዓዶዑማር ወደ ዋናው ነጥብ ከመግባታቸው በፊት፣ በመጀመሪያ ከብዙ ዓመታት በኋላ እንዲህ ዓይነት የሶስቱ ኢሮብ በርካታ ተወካዮች የተገኙበት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ለዚች ዕለት ላደረሰኝ ቸሩ መድሃኔዓለም አመስግናለሁ፣ በመቀጠል በዚህ መንገድ እንደ ድሮአችን (የኦና ስርዓት ዘመን) ተሰብስበን በጉዳያችን ለመምከር፣ ይህን ስብሰባ ላዘጋጀልን ለልጃችን መምህር ገረይ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ ካሉ በኋላ፣ አዎ መምህር ገረይ እንዳስቀመጠው አሁን የመረጥነው ኦና የለንም። ነገር ግን በቅርብ ጊዜ የራስችን የመረጥነው ኦና እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ። እስከዛው በርግጥ መምህር ገረይን በባህላችን መሰረት ኦና ብለን ባንመርጠውም አንድ ኦና የሚሰራው የነበረ ስራ እየሰራ ስለሆነ ይህ ስብሰባንም ሆነ ለወደፊት የሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎች እሱ ቢመራልን፣ የራሳችን ኦና እስክንመርጥ ድረስም እኛን/ኢሮብን ወክሎ ከሚመለከታቸው ጋራ እንዲገናኝልንና እንዲመራን መስማማት አለብን በማለት ሃሳብ አቀረቡ።

የስብሰባው አመራርና ተሳትፎ፣

የኢሮብ ህዝብ በስብሰባ ላይ አንድ ተናጋሪ ሲናገር ልብ ብሎ ሊያደምጠው ከፈለገ ሁሉም ነገር ትቶ ሙሉ ቱክረቱን ተናጋሪው ላይ አድርጎ ያደምጣል። ተናጋሪው የሚናገረው ካልጣመው ግን ጠጠሮች በእጁ አስባስቦ ከጠጠሮቹ ጋራ ይጫወታል ወይም በትንንሽ ድንጋዮች መንደቅ ይነድቃል። በመጨረሻም ስብሰባው ካልተመቸው ተቃውሞን ለመግለፅ ጠጠሮቹን ይበትናል፣ ወይም የገነባውን መንደቅ ነገር ያፈርሳል። ይህ የኢሮብ ህዝብ የስብሰባ ባህል ጓድ ገረይ ከስብሰባው በፊት ነግሮኝ በዕለቱም የተሳታፊዎች ሁኔታ በደንብ እንድከታተል ነግሮኝ ስለነበረ፣ እሱም አቤቶ ዓዶዑማርም ሲናገሩ ልብ ብዬ ወደ ሁሉም አቅጣጫ እየተመለከትኩ እከታተል ነበር። ገና ጓድ ገረይ በማኸል ቆሞ መናገር ስጀምር ሆነ አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ሃሳብ ሲሰጡ በነበረት ጊዜ ዙሪያውን ተሰብሳቢውን ስቃኝ አንድም ሰው ከጠጠሮቹ ጋራ የሚጫወት ወይም የሚነድቅ አልነበረም። ሁሉም ሙሉ ቱክረቱን ወደ ተናጋሪዎቹ አድርጎ በፅሞና ያዳምጥ ነበር። ሌላ ጓድ ገረይ ከስብሰባው ዕለት በፊት የኢሮብ ህዝብ በስብሰባ ተሳትፎን በተመለከተ የነገረኝ ኢሮቦች በራሳቸው ስብሰባ አስቀድመው የዕድሜ ባለፀጎችና አዋቂዎች አስቀድመው እንዲናገሩ እንደሚያደርጉ፣ ብዙዉን ጊዜ እነዚህ አዋቂዎችም የህዝቡን ፍላጎት በሚገባ ወክለው ሃሳብ/ውሳኔ ስለሚያስቀምጡ ስብሰባ ባጭሩ ውሱን አባቶች በሰጡት የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ስምምነት እንደሚጠናቀቅ፣ ይህ ካልሆነ ግን የኢሮብ ህዝብ የማያምንበት ነገር በቀላሉ የማይቀበል ህዝብ ስለሆነ ስብሰባው ሊራዘም እንደምችልና ባንድ ቀን ሊያልቅ የማይችልበት ዕድል ሊጋጥመን እንደምችል አስቀድሞ ነገሮኝ ስለነበረ ይህም በቅርበት እከታተል ነበር። ስለሆነም አቤቶ ዓዶዑማር ስብሰባውን ጓድ ገረይ ይምራው ብለው ምክንያታቸውን ዘርዝረው የሰጡት ሃሳብ ተሰብሳቢው በየአከባቢው በጥቅሻም በመነጋገርም ትንሽ ካብላላ በኋላ በአንድ ድምፅ “ኤድ፟ኦሮብና” ሲተረጎም፣ በሃሳብዎ ተስማምተናል ብሎ ማፅደቁ ጓድ ገረይ አስቀድሞ የነገረኝን የኢሮቦች የስብሰባ አካሄድ ባህል አረጋግጦልኝ በጣም ተደሰትኩ፣ የኢሮብ አባቶች አርአያነትና የወጣቱ ለነሱ የነበረው ክብርና አርአያነታቸው መከተልን አደነቅኩ። በዚህ የተሰብሳቢው በአንድ ድምፅ ኤድ፟ኦሮብና ውሳኔ መሰረትም ጓድ ገረይ ውሳኔውን ተቀብሎ ስብስባውን መምራት ቀጠለ።
የዕለቱ አጀንዳና ለአዲሱ የመሬት ስሪት/ህግ በአቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ የቀረቡ ነጥቦች፣
የዕለቱ ብቸኛ አጀንዳ የቆየውን የመሬት ስሪት (ርስትና ሰሐና ስሪት) በመሬት ለአራሹ አዋጅ መሰረት፣ በመላው ኢሮብ ወጥ በሆነ መንገድ መሬት እንዴት ይከፋፈል ለሚለው የነበረውን ስሪት የሚተካ አዲስ ስሪት ማውጣት ስለሆነ በአዲሱ ስሪት መካተት ያለባቸው ነጥቦች ምን መሆን አለባቸው በሚለው እያተኮራችሁ ሃሳብ እንድትሰጡ መድረኩ ለውውይት ክፍት ነው በማለት ጓድ ገረይ መድረኩን ከፈተ። ያኔ በነበረው የኢሮብ ባህል ከዕድሜ ባለፀጋ፣ አዋቂ በፊት መናገር/ሃሳብ መስጠት እንደ ነውር ይቆጠር ስለነበረ ወጣቶቹ በሙሉ አሁንም ወደ ትልልቆቹ ቀድመው መንደርደሪያ ሃሳብ እንዲሰጡ ሃሳብ አቀረቡ። በዚህ መሰረትም ኦና ወልደገርጊስ/ዓይጋ ቆመው፣ በአጠቃላይ ኢሮብ የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሁላችን በላቀ ደረጃ ከወጣትነት ዕድሜው እስከ ዛሬ ድረስ እየሰራ ያለ፣ ዛሬ እዚህ ከተገኘነው በዕድሜ፣ በእውቀትና ልምድ የሚበልጥ ስለሆነ፣ ይህ ዛሬ የተሰበሰብንለት ጉዳይ (በርስት ተይዞ ያለው መሬት ጉዳይ) ርስት ቀርቶ መሬት ለሁሉም እኩል እንዲከፋፈል ሲወተውት የነበረ ስለሆነ፣ አሁንም አቤቶ ዓዶዑማር አዲሱ የመሬት ስሪት ማካታተ ያለባቸው ነጥቦች በተመለከተ መንደርደሪያ ቢሰጠንና በሱ መንደርደሪያ መሰረት ውይይቱ ቢቀጥል በማለት ሃሳብ አቀረቡ። ተሰብሳቢውም እንደ ቅድሙ ኤድ፟ኦሮብና (እንስማማለን) በማለት በአንድ ድምፅ በሃሳቡ መስማማቱን አረጋገጠ።
በተሰብሳቢው ውሳኔ መሰረት ጓድ ገረይ ኦና ወልደገርጊስ ያቀረቡት ንድፈ ሃሳብ/Proposal አድንቆና አመስግኖ አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ሃሳብ እንዲሰጡ ጋበዘ። አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ከ1950ዎቹ በፊት የነበረው የኢሮብ ህዝብ ብዛት፣ የነበረው የመሬቱ በደን መሸፈን፣ ከዛ በፊት የነበረው የኢሮብ ህዝብ የኢኮኖሚ መሰረት በዋናነት የእንስሳ ርቢ መኖሩን. . . ጠቅሰው፣ ከ1960ዎች በኋላ ግን ሁኔታው በጣም መቀየሩ፣ በየቀበሌው ብዙ አዲስ ነዋሪ መጨመሩ፣ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭነት ከእንስሳ ሪብነት ወደ እርሻ እየተቀየረ መምጣቱ፣ የሚታረስ ያለው አንስተኛ የእርሻ መሬት በጥቂቶች በርስት ስለተያዘ አዲሶቹ የሚታረስ መሬት ፈላጊ ወጣቶች በየተራራውና ጥጋጥጉ ያለውን ጫካ እየመነጠሩ ለእርሻ እያዋሉት መሆናቸውና የዚህ ውጤት ነገ ምን ሊሆን እንደምችል እየታያቸው እንዳልሆነ . . . በመዘርዘር ለዚህ ለወደፊቱ በስፋት በህዝብም በመንግስትም ደረጃ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ለጊዜው የጫካ ምንጠራውን ለመቀነስ እንዲረዳ በርስት የተያዘው የእርሻ መሬት ለሁሉም በእኩል መከፋፈል እንዳለበት በአፅንዖት ገለፁ። ሌላውም በኢሮብ አሁን እየተደረገ ያለው የደን ብርሰት እንዲህ ከቀጠለ ባጭር ጊዜ ውስጥ የኢሮብ መሬት እርቃኑን ቀርቶ ምድረበዳ ወደመሆን ሊቀየር እንደምችል በግልፅ ቋንቋ አስቀምጠው እንደ መፍትሄም፣ ዋናው መፍትሄ የሚመጣው ህዝቡን ከሚያስተዳድረው መንግስት ቢሆንም ያ እስከሚገኝ በኛ ደረጃም በሰዓቱ መውሰድ ያለብን እርምጃ መውሰድ አለብን አሉ። አሁን መውሰድ ካለብን እርምጃዎች ዋነኞቹ ደግሞ ለእርሻ መሬት ተብሎ እየወደመ ያለውን ደን ባስቸኳይ ማስቆም፣ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ ወጣቶቻችን የሚጠይቁት የእርሻ መሬት ጥያቄ ለመመለስ እስካሁ በርስት የተያዘው መሬት ለሁሉም እኩል እንዲከፋፈል ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የቆየውን የመሬት ስሪት የሚተካ አዲስ ስሪት አውጥተን በስሪቱ መሰረት መሬት ለሁሉም እንዲከፋፈል ማድረግ ነው። በኔ እምነትና ፍላጎትም አዲሱ የመሬት ስሪታችን ቀጥለው የተቀመጡ ነጥቦች ማካተት አለበት በማለት ወደ ነጥቦቹ አንድ በአንድ መዘርዘር ገቡ።
1. የኢሮብ መሬት ቆላና ደጋ እንደመሆኑ፣ በቆላው ክፍል ያለው የእርሻ መሬት ደጋ ካለው ጋራ ሲነፃፀር ረቃቃና ዝናብ አንዴ ካቆመ ቶሎ ለድርቅ የሚጋለጥ ስለሆነ፣ የደጋውም የቆላዉም መሬት ለሁሉም ነዋሪ በእኩል መከፋፈል አለበት።
2. በትክክል መሬት ለአራሹ መሆን ስላለበት ባለ ርስት ነን በማለት ከኢሮብ ውጭ እየኖሩ ርስት የነበራቸው ሰዎች በቦታው እስካልኖሩ በርስት ይዘዉት የነበረ መሬት በኢሮብ ወረዳ ለሚኖሩ ይከፋፈላል፣ በወረዳው ለመኖር ከፈለጉና በቦታው መኖራቸው ከተረጋገጠ ግን እንደ ሁሉ መሬት የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ይሆናል።
3. በኢሮብ ወረዳ የሚኖሩ በርስት ይዘዉት የነበረ መሬት በአዲሱ የመሬት አዋጅ መሰረት መሻሩ ታውቆ በርስት የያዙት መሬት ከሌሎች ጋራ እኩል ተካፍለው ድርሻቸውን ያገኛሉ።
4. መሬት ለሁሉም በእኩል መከፋፈሉ የሚረጋገጠው በየቀበሌው በህዝብ በተመረጠ ኮሚቴ አማካይነት ሲከፋፈል ስለሆነ በሁሉም ቀበሌዎች መሬት ማከፋፈል የሚካሄደው በነዚህ በህዝብ በተመረጡ ኮሚቴዎች ብቻ ይሆናል።
5. የህዝቡ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ስለሆነ፣ በየጊዜው አዲስ መሬት ፈላጊ ወጣቶች ስለሚኖሩ በወረዳ ደረጃ በየአራት ዓመቱ የዓመቱ ምርት እንደተሰበሰ አዲስ መሬት ማከፋፈል በህዝብ በተመረጠ ኮሚቴ አማካይነት እንዲካሄድ።
6. በኢሮብ አሁን በያዝነው ተራራውና ጫካውን እየመነጠሩ ለእርሻ መሬት ማዋል አሁን ባለው ፍጥነትና ስፋት ከቀጠል ባጭር ጊዜ ውስጥ አከባቢው ወደ ምድረበዳነት ስለሚቀየር ይህ በህግ ቆሞ፣ ከንገዲህ አዲስ ለእርሻ የሚሆን መሬት ፍለጋ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን በየአከባቢው ያሉትን አነስተኛ ወንዞች ሆነ ሸለቆዎችን መገደብ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፣ ተራሮችን ለእርሻ መሬት ብሎ መመንጠር ሳይሆን ዛፎችን በመትክል እንዳ አዲስ እንዲለሙ መንከባክብ አለብን በማለት ሃሳባቸውን አጠናቀቁ።

አቤቶ ዓዶዑማር የመሬት ስሪት ነጥቦቹን ሲያቀርቡ ልክ እንደ አንድ ነጥቦቹን በፅሁፍ ያዘጋጀ አቅራቢ የፃፈውን እንደሚያቅርብ ዓይነት ሆኖ በቃላቸው ነበር ያቀረቡት፣ የአቀራረባቸው ቀደምተከተልና ላዛ እጅግ የሚደነቅና የአድማጭ ጆሮና ልብ ሳቢ ነበር። በመሆኑም ተሰብሳቢዉ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው በፅሞና አዳኣምጦ እርካታውና በነጥቦቹ ላይ የነበረው ሙሉ ስምምነት በፊቱ ይነበብ ነበር።

ለውሳኔ በቀረቡ ነጥቦች ላይ የቀረቡ ሃሳቦች/አስተያየቶችና ውሳኔ፣
አቤቶ ዓዶዑማር የአዲሱ የመሬት ስሪት/ህግን በተመለከተ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ካስቀመጡ በኋላ ስብሰባውን ሲመራ የነበረው ጓድ ገረይ በነጥቦቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥቶ፣ ጥያቄ፣ ሃሳብ/አስተያየት፣ ተጨማሪ፣ ተቃውሞ ካለ በማለት መድረኩን ለተሰብሳቢው ከፈተ። እንደተለመደው ተሰብሳቢው የመጅመሪያ ሃሳብ ሰጭ ከትልልቆቹ እንዲቀድም “ናባማራኮ ጋሮክ ኡኩማ” (ሲተረጎም ከትልልቆቹ አንዳችሁ ቅደሙ) በማለት ሃሳብ አቀረበ። ልጅ ብስራት ገብራይ (ከጣሊያን 2ኛ ወረራ በፊት በቡክናይቲ ዓረ የተመረጡ የመጨረሻ ኦና ገብራይ ዕንዳይ ልጅ) ተነስተው ስለ አቤቶ ዓዶዑማር ማንነት፣ ለኢሮብ ህዝብ አንድነትና ህልውና መቀጠል ያበረከቱትን አስተዋፅዖ፣ በኢሮብ በርስት የተያዘው መሬት እንደ ሰሓናው ለሁሉም እኩል መከፋፈል አለበት ብለው ከድሮ ጀምሮ ሲናገሩና ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ የኢሮብ ህዝብ ህልውና የኢኮኖሚ መሰረት መሆን ያለበት በተራሮች ላይ የበቀለውን ጫካ በመመንጠር የእርሻ መሬት ለማድረግ መሞከር ሳይሆን የእንስሳ ርቢና በዋናነት የተማረ ትውልድ መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆን አለበት በምሳሌ ደረጃ “ኢሮ ሚህሮድ ላኣ፟ ጊርቦድ” (ሲተረጎም፤ ልጆች ወደ ትምህርት ከብትን ወደ አቁማዳ/ከብት ይሸጥ ለማለት) ይሉ እንደነበረ፣ . . . በመዘርዘር፣ እሳቸው ያስቀመጡዋቸው ነጥቦች እንደ ህጋችን ተቀብለን እናፅድቃቸው፣ ይህ ስብሰባም አሁን መሬት እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ያሉ ልጆቻችን ለዘንደሮው (1968ቱ) የአዝመራ ወቅት ከራሳቸው መሬት የመጀመሪያ ምርት እንዲያገኙ መሬቱ መጋቢት ከመጠናቀቁ በፊት በአዲሱ ስሪት መሰረት መከፋፈል እንዳለበት እንወስን በማለት ሃሳባቸውን አጠናቀቁ።

በመቀጠል ልጅ አብራሃ ከአድጋዲ ዓረ፣ የነበረው የርስት ስርዓት እንዳበቃ መንግስት (ደርግ) አውጇል፣ አሁን ኢሮብን እያስተዳደረ ያለው ኢህአፓም መሬት ለአራሹ እንደሚሉና የርስት ስርዓት/የመሳፍንት ስርዓት መቅረት ብሎ እንደሚያምና ለዚህም እንደሚታገል ልጃችን መምህር ገረይ በግልፅ ቋንቋ ወደዚህ ስብሰባ ከመምጣታችን በፊት በማይፂዓ/አድጋዲ ዓረ ባደረግነው ስብሰባ በግልፅ ነግሮናል። አሁን መሬት ከሚፈልጉ ልጆቻችን በፍቅር አንድነታችን ተጠብቆ መኖር ከፈለግን መሬቱን በርስት የያዝን ወላጆች መሬቱን ከልጆቻችን ጋራ እኩል ተካፍለን መኖር የግድ ስለሆነ በአዲሱ ስሪት መሰረት መሬቱ ይከፋፈል የሚለው የጋራ ውሳኔያችን ይሁን። ስለሆነም ወንድሜ ልጅ ብስራት ያቀረቡት ሃሳብ ተቀብለን የዛሬው ስብሰባችን እንጨርስ በማለት የልጅ ብስራት ሃሳብ ደገፉ። ከልጅ አብራሃ/አድጋዲ ዓረ በመቀጠል ኦና ወልደገርጊስ/ዓይጋ በአፄ ኃ/ስላሴ ስርዓት ጊዜ ኢሮብ ወረዳ እንዲያስተዳድሩ የተመደቡት ባሻይ ቢሻኡ በቦታው ሆነው ሊያስተዳድሩን ስላልቻሉ የአስተዳዳሪ ችግር ሲገጥመን ችግሩን የተረዱት ሰለቃ ወልዱ ገብራይ መጥተው ያስተዳደር ችግራችንን ፈተው አንድነታችን አስጠብቀው እስከ ዕለተ ሞታቸው አስተዳደሩን፣ ከሳቸው ሞት በኋላ የአስተዳዳሪ አለመኖር ችግር ቀጥሎ ወደ አንድነታችን ንፋስ መግባት ጀምሮ ነበር። አሁን ኢህአፓ በአከባቢያችን ከመጣ በኋላ ልክ እንደ ሰለቃ ወልዱ ልጃችን መምህር ገረይ መጥቶ የኸው በሱ አስተዳዳሪነት ለዚህ ስብሰባ ደርሰናል። ይህ ስብሰባ የድሮ ኦና ስርዓት ጊዜ “ሓዳሎብቲ” ትርጉም (አጠቃላይ ስብሰባ) ዓይነት ስብሰባ ነው። ዛሬ ራሳችን የመረጥነው ኦና ባይሆንም የመረጥነው ኦና ማሟላት የሚገባውን አካሄድና አሰራር አሟልቶ በልጃችን በመምህር ገርይ የተጠራ ሓዳሎብቲ (አጠቃላይ ስብሰባ) ስለሆነ የቆየውን የርስትና ሰሐና የመሬት ስሪት ወደ አዲሱ በአቤቶ ዓዶዑማር ያስቀመጡት አዲስ ስሪት የምንቀይርበት፣ እንደ ኢሮብ መወሰን ያለብን ጉዳዮች ለወደፊትም በዚህ መልክ ማድረግ እንዳለብን የምንወስንበት ውሳኝና ታሪካዊ ስብሰባ ነው። አዲሱ የመሬት ስሪት ምን መምሰል እንዳለበት አቤቶ ዓዶዑማር በግልፅና በዝርዝር አስቀምጠውልናልና ልክ ወንድሞቼ ልጅ ብስራትና ልጅ አብራሃ እንዳሉት ስሪቱን እንዳለ ተቀብለን፣ መሬቱ ከመጋቢት መጨረሻ በፊት በአዲሱ ስሪት መሰረት በመላው ኢሮብ መከፋፈል እንዳለበት ወስነን ስብሰባችን እንጨርስ በማለት ሃሳብ አቀረቡ።
የቦካለ ማኮ የ1968 ስብሰባ እዉነተኛ የኢሮብ ህዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው የዕድሜ ባለፀጎችና አዋቂዎች በወጣቶቹ መከበር፣ መደመጠ፣ አርአያቸውን መከተል በትክክል የታዘብኩበት፣ የዕድሜ ባለፀጎችም ለወጣቶቹ የነበራቸው አሳቢነትና በንግግራቸው ሆነ በተግባራቸው የነሱን አርአያ እንዲከተሉ የማድረግ ችሎታና ዘዴ በተግባር ያየሁበት፣ የኢሮብ ህዝብ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም በኢሮባዊ ማንነቱ የሚኮራና ፈፅሞ የማይደራደር መሆኑ በግልፅ የተገነዘብኩበት፣ ያ ጓድ ገረይ ሲነግረኝ የነበረ የኢሮብ ህዝብ ማንነት በትክክል በተግባር ያየሁበት እስከ ዛሬ ድረስ የቦታውና የተሰብሳቢው ስዕል በአእምሮዬ ተቀርፅ ያለ ስብሰባ ነበር። ጓድ ገረይ አስቀድሞ እንደነገረኝ የኢሮብ ህዝብ የልቡን የሚናግርለት ሰው ካየ የግድ እኔም ልናገር የሚል ባህል እንደሌለው በዕለቱ ከ300 ሰው በላይ በተሳተፈበት ስብሰባ ተናጋሪዎች ከ5 ሰዎች የማይበልጡ የዕድሜና የእውቀት ባለፀጎች ብቻ ነበሩ። በዚህ መሰረት አቤቶ ዓዶዑማር ያቀረቡት አዲሱ የመሬት ስሪት በሶስቱ ጉምቱ ኢሮቦች ንግግር ተደግፎ፣ 300 በላይ ተሳታፊ ሳይናገር “ኤድ፟፟ ኦሮብና” (ሙሉ በሙሉ በሃሳቡ እንስማማለን) በማለት የጥቂት አዋቂ አባቶች ሃሳብ በመቀበል አዲሱ የመሬት ስሪቱ ፀድቆ፣ በስሪቱ መሰረት መሬቱ ከ1968 የአዝመራ ወቅት በፊት እንዲከፋፈል ተወስኖ በግምት ከቀኑ ወደ 9 ሰዓት አከባቢ ስብሰባው ተጠናቀቀ።

ለዕለቱ የተጠራው ስብሰባ በዚህ መልክ ቢያልቅም ወደ ስብሰባው ማጠቃለያ አከባቢ ወደ ቦታው የመጡ የተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ተወካዮች ለተሰብሳቢው ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ ከተወሰነ ክርክር በኋላ በጓድ ገረይ ተሰብሳቢው ላጭር ደቂቃዎች እንዲያደምጣቸው በጠየቀው መሰረት ተሰብሳቢው ተስማምቶ፣ ለመሄድ ተነስቶ የነበረውም መልሶ ተቀምጦ ከተወካዩቹ አንዱ ለተሰብሳቢው በትግርኛ ያደረገ አጭር ገለፃና ለገለፃው ተሰብሳቢው የሰጠው ምላሽ ምን ይመስል እንደነበረ በዝርዝ በቁጥር አራት ይዤላችሁ እቀርባለሁ።

እስከዛር በቸር ሰንብቱ፣ የነገ ሰው ይበለን።

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር ሁለት፤ የ1968ቱ የቦካለ፟ማኮ/ዓሊተና ስብሰባ መጠራት ለምን አስፈለገ፣ የጠራውስ ማን ነበር፣ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ፣ጥቅምት 2014መጣጥፉን...
31/10/2021

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር ሁለት፤
የ1968ቱ የቦካለ፟ማኮ/ዓሊተና ስብሰባ መጠራት ለምን አስፈለገ፣ የጠራውስ ማን ነበር፣

ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ፣
ጥቅምት 2014

መጣጥፉን ለመፃፍ መነሻ ምክንያት፣

ተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs በሚል የፈስቡክ ስም፣ ኢሮብ ከ19ኛ -21ኛ ክፍለዘመን የቁልቁለት ጉዞ በሚል ርእስ (https://www.facebook.com/Concerned.Irobs/posts/116220184122090) ሰፕተምበር 19 በቀረበው መጣጥፍ ውስጥ ከሶስቱ ኢሮብ (አድጋዲ ዓረ፣ ቡክናይቲ ዓረ፣ ሓሳባላ ዓረ) ከ300 በላይ ተወካዮች የተገኙበት ስብሰባ በቦካለ፟ማኮ/ዓሊተና መደረጉ፣ ለስብሰባው መጠራት ዋና ዓላማ የመሬት ማከፋፈል የጋራ ስሪት/ህግ ለማውጣት መኖሩና ስብሰባውን የጠራው ደግሞ ኢህአፓ/ሰ እንደነበረ ባጭሩ ተጠቅሷል። ሆኖም ግን ለመሬት ማከፋፈሉ በህዝበ ውሳኔ የሚፀድቅ አዲስ ስሪት/ህግ ማውጣት ለምን አስፈለገ፣ ለምን ኢህአፓ/ሰ በራሱ ውሳኔና አሰራር መሬቱን አላከፋፈለም፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች እነማን ነበሩ፣በማንና እንዴትስ ተመረጡ፣ የስብሰባው አካሄድ ምን ይመስል ነበር፣ የስብሰባው ውጤትስ ምን ሆነ፣ ለዚህ ስብሰባ መጠራት ሆነ የኢሮብ ህዝብ ማንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ማን ነበር. . . ወዘተ. በሚለው የቀረበ ዝርዝር የለም።

በቁጥር አንድ በወቅቱ በአከባቢው (ምስራቅ ዓጋመ አውራጃ) ገጠርማ አከባቢ የነበረ ሁኔታና በአከባቢው እየተጀመረ ስለነበረው የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ባጭሩ ያስቀመጥኩት እዝህ ታገኙታላችሁ (https://www.facebook.com/Concerned.Irobs/posts/122162466861195)፡፡

ይህ ስብሰባ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጠው የኢሮብ ብሄረሰብ የቅራኔ/ችግር በውይይትና በዴሞክራሲያዊ ውሳኔ አፈታት ባህልና ስነልቦና በግልፅ የታየበት፣ በስብሰባው መጨረሻ የተሓህት ተወካዮች ስለ ድርጅታቸው ማንነትና ዓላማ ገለፃ ባደረጉበት ጊዜ የኢሮብ ህዝብ በኢሮባዊ ማንነቱ ፈፅሞ የማየደራደር መሆኑ፣ የኢሮብ ብሄረሰብ ተጋሩ ብለው ራሳቸውን ከሚጠሩ የትግራይ ብሄረሰብ የተለየ ራሱን የቻለ ብሄረስብ መሆኑ በግልፅ ቋንቋ ያስቀመጠበት ታሪካዊ ስብሰባ ስለነበረ እኔም በስብሰባው በአካል ስለነበርኩ፣ ያኔ (46 ዓመት) በፊት የነበረው የኢሮብ ብሄረሰብ ምን ይመስል እንደነበረ በመጠኑም ቢሆን ስለማውቅ፣ ዛሬ ወደ መጥፋት አፋፍ ላይ ደርሶ ያለው የኢሮብ ብሄረሰብ የዛሬ 46 ዓመት በፊት ምን ይመስል እንደነበረ ለዛሬ ወጣት ትውልድ ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ሃቁን ማወቅ ለሚፈልግ የኢሮብ ወጣት ትውልድ ታሪኩን የማሳወቅ ግዴታ ስላለብኝ ስለ ስብሰባውና ስብሰባውን ያዘጋጀው ያኔ ኢሮብን ዋና ቤይዙን አድርጎ ይንቀሳቀስ ስለነበረው የኢህአፓ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በኢሮብ ባጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ። ስለ ቦካለ-ማኮ ስብሰባ ዝርዝር መፃፍ ከመግባቴ በፊት ግን ይህን ስብሰባ የጠራውና ከ1967- 1970 ግንቦት ድረስ አከባቢው በቁጥጥሩ ስር ስለ ነበረው ኢህአፓ/ሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን የመጀመሪያ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበረ ባጭሩ በመግለፅ ልጀምር።

አከባቢውንና ህዝቡን ለማወቅ በኢህአፓ/ሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን የተደረገ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ፤

የኢህአሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ኢሮብ/ዓሲምባ 1967 እንደገባ ከእናት ድርጅቱ ኢህአፓ ጋራ እስከሚገናኝ ወደ 2 ወር ያህል ጊዜ በዓሲምባ ተራራ ዙሪያ ተወስኖ ኣከባቢው ጋር እየተዋወቀ ነበር የቆየው። ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይና ፀጋዬ ገ/መድህን/ደብተራው ከከተማ መጥው ከቡድኑ ጋራ ተገናኝተው ቡድኑ በአከባቢው ራሱንና እናት ድርጅቱን (ኢህአፓን) ማስተዋወቅ በተመለከተ መመሪያ ሰጥተው፣ ዶክተር ተስፋይና ብርሃነመስቀል ረዳ ወደ ከተማ ሲሄዱ፤ ፀጋዬ ገ/መድህን (ያኔ አማሃ በሚል የትግል ስም ይታወቅ የነበረ) የቡድኑ የፖለቲካ መሪ ሮባ/ኣብዲሳ አያና ብርሃነመስቀልን ተክቶ የቡድኑ ወታደራዊ መሪ ሆኖ ቡድኑ ራሱንና እናት ድርጅቱን የማስተዋወቅ ስራ ለመጀመር ክረምት ላይ በህዝቡ መካከል ግልፅ እንቅስቃሴ ጀመረ። የመጀመሪያ ፈጣንና አሳሳች እንቅስቃሴውን ከኢሮብ ወረዳ ወጥቶ፣ በጉለማካዳ፣ ዳሞ፣ ብዘት፣ ሓውዘን፣ ክልተአውላዕሎ፣እስከ እንደርታ ጫፍ በማድረግ ራሱንና እናት ድርጅቱን ከህዝቡና በተለይ በወቅቱ በአከባቢው ዘምተው ከነበሩ የእድገት በህብረት ዘማች ተማሪዎች ጋራ አስተዋውቆ ወደ ኢሮብ ወረዳ ተመለሰ።

ኢህአፓ/ሰ በትግራይ ለሚያካሄደው የትጥቅ ትግል የመጀመሪያ መናገሻ (ቤዙ) በኢሮብ መሆን አለበት ብሎ ስላመነ፣ የመሬቱ አቀማመጥና ህዝቡን በሚገባ ማወቅ ነበረበት። በመሆኑም በወቅቱ የነበረው በሁለት ጋንታ የተደራጀው (ወደ 50 ሰው) ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን በ1968 ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ሞላው የኢሮብ ወረዳ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚያዳርስ ዓላማው ከህዝቡና ከመሬቱ ጋራ መተዋወቅ ያደረገ እንቅስቃሴ ተደረገ። በዚህ እንቅስቃሴ ወቅት የመላው የቡድኑ አባላት ከህዝቡ ጋራ የመተዋወቅና ስለ ኢህአፓ ዓላማ ማሳውቅ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ ችግሮች፣ ሃሳቦች/አስተያየቶች. . . በሚገባ በፅሁፍ ማሰባሰብ፣ በቦታው መመለስ የነበረባቸው ቀላል ጉዳዮች በቦታው ለመመልስ ጓድ ገረይ በዋነነት እኔ ደግሞ በረዳትነት ተመደብን። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ሁለታችን የአከባቢው ተወላጆች ስለሆንና ቋንቋዉን/ሳሆ የምንናገር በተለይ ጓድ ገረይ በአብዛኛው የኢሮብ አከባቢ በሚገባ ይታወቅ ስለነበረም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ጓድ ገረይ የኢሮብ ህዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ስነልቦና በሚገባ ከሚያውቁና በህዝቡ ተቀባይነት ከነበራቸው በኢህአፓ ውስጥ ከነበሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች አንዱ ስለነበረም ነበር። እኔ ቋንቋውን ከመናገር ውጭ ስለ ህዝቡ ባህል፣ስነልቦና፣ ታሪክ በጣም ቁንጹል የሆነ እውቀት የነበረኝ ሲሆን፣ ጓድ ገረይን የመሰለ አስተማሪና አርአያ የሚሆን ጓድ ከፊቴ መኖር ስለ ኢሮብ ህዝብ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህልና ስነልቦና በቀላሉና ቶሎ ለማወቅ ዕድል አገኘሁ። ገና እንቅስቃሴው ከመጀመሩ በፊት ጓድ ገረይ ስለ ኢሮብ ህዝብ ባህል፣ ስነልቦና በሚገባ ትምህርት ሰጥቶኝ፣ እንዴት ወደ ህዝቡ መቅረብ እንዳለብኝ፣ በየቁሸቱ ከነበሩ የዕድሜ ባለፀጎች ጋራ እንዴት መቅረብና ከነሱ ምክር መጠየቅ እንዳለብኝ፣ ዋናዋ የአከባቢው ኢንፎርመሽንና መረጃ ምንጭነት እንዴት እነሱን መጠቀም እንደነበረብኝ፣ እንዴት ምክራቸውን መከተል እንዳለብኝ. . . በዝርዝር ትምህርትና መመሪያ ሰጠኝ። ያኔ ገና በ20 ዓመት ዕድሜ ላይ ለነበርኩና ስለ ኢሮብ ምንም እውቀት ላልነበረኝ ወጣት ጓድ ገረይን የመሰለ እንደ አርአያ ልከተለው የምችል አስተማሪም ጓድም ማግኘት የማላወቅ የነበረ ማንነቴን/ኢሮብነት እንዳውቅ፣ የኢሮብ ህዝብን ይብልጥ እንዳውቅ ትልቅ የረዳኝ ትልቅ ዕድል ስለነበር እሱ የሚሰጠኝ ትምህርት፣ ምክርና መመሪያም በጥብቅ እከተል ነበር፣ የሆነ ጥያቄ/ሃሳብ ሲኖረኝም ወዲያውኑ እያቀረብኩለት ወዲያውኑ መልስ ይሰጠኝ ነበር።

ለቦካለ፟ማኮ ስብሰባ ግብአት የሆነውና በጓድ ገረይ መሪነት የተካሄደው የዳሰሳ ጥናትና ውጤቱ፡

ይህ ኢሮብን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያዳረሰ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በምስራቃዊ ቡክናይቲ ዓረ ኣበ በሚባል ቀበሌ ተጀምሮ በዋርዓትለ በኩል ወደ ካፍና በመውጣት ሞላው አድጋዲ ዓረ ያዳረሰ፣ ከአድጋዲ ዓረ ወደ ቡክናይቲ ዓረ ምዕራባዊ ደጋ በመመለስ ዋና ዋና ቀበሌዎችን በማዳረስ ወደ ቆላው ቡክናይቲ-ዓረ በመቀጠል ከዛ ወደ ምዕራባዊ ኢሮብ ዓጋራለኮማ በመቀጠል ዋናዋና ቀበሌዎችን ያዳረሰ፣ በመቀጠል በዓሰፋት ወደ ሓሳባላ በመግባት የሓሳባላ ዋና ዋና ቀበሌዎችን በማዳረስ የሓሳባላ የመጨረሻ ሰው የሰፈረበት ደቡባዊ ጫፍ የሆነው ጉንዳጉንደ ገዳም ላይ የተጠናቀቀ ነበር።

በዚህ እንቅስቃሴ ጓድ ገረይ እንቅስቃሴው ከመጀመሩ በፊት በሰጠኝ ትምህርትና መመሪያ መሰረት ተልእኮዬን ለመፈፀም ህዝቡን መገናኘት ስጀምር አንድ ነገር ታዘብኩ። በቆየው የኢሮብ ባህል መሰረት በሳሆ “ዋሪስም” (ዜና መለዋወጥ) እና በኢሮብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ኢሮቦች ብቻ በሚተዋወቁበት የራሳቸው ኮድ መሰረት በጥሪ በሚተላለፈው መልእክት ህዝቡ በያረፍንበት ቀበሌ ያልነው፣ የስራነው ቀጥሎ በምንርፍበት ቀበሌ ቀድሞ ደርሶ አውቆ፣ ማንነቴም ገና እኔ ራሴን ከማስተዋውቄ በፊት ብዙዎቹ አውቀው በኢህአፓነቴ ሳይሆን በኢሮብነቴ ቀርበው ስለሁኔታው በግልፅና በዝርዝር ይነገሩኝ ነበር። እኔም በጓድ ገረይ በተሰጠኝ መመሪያ መሰረት እቦታው መፈታት ያለበት ከቀበሌው ሽማግሌዎች ጋራ በመሆን እየፈታን በቦታት መፈታት የማችሉትን ጥያቄዎች፣ ሃሳቦች ሆነ ችግሮች ለይቼ እየመዘገብኩ እስከ እንቅስቃሴው ፍፃሜ ድረስ ቀጠልኩ፣ በጓድ ገረይ በኩልም እንደዚሁ ተደረገ።
ከዚህ መላው ኢሮብን ያዳረሰ እንቅስቃሴ ፍፃሜ በኋላ አጠቃላይ የእንቅስቃሴው ውጤት ገምግመን በየግላችን ያሰባሰብነው አንድ ላይ ለማቀናጀት ማጋዑማ በሚባል ቀበሌ ተገናኘን። ህዝቡ ለኢህአፓ የነበረው ድጋፍ ሆነ ተቃውሞ በተመለከተ የኢሮብ ህዝብ በባህሪዩ ቶሎ ብሎ ድጋፍ ወይ ተቃውሞ የማያሳይ ህዝብ ቢሆንም በአመዛኙ ኢህአፓ ይዞት የነበረው ዓላማና ድርጅቱ ውስጥ ከዋና አመራር እስከ ተራ አባላት በህብረተስቡ የሚከበሩ የራሱ ልጆች ስለነበሩ ለድርጅቱ ድጋፍ እንደነበረው አወቅን፣ ከየአከባቢዉም አብረን ለመታገል እንፈልጋለን የሚሉ ወጣት አርሶ አደሮች ገና ከጅምሩ ለማየት ቻልን። በተለይ ሁለታችን ተመድበንለት የነበረው የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች/ችግሮች ለይቶ የማወቅ ስራ በተመለከተም፣ ጥያቄዎቹ/ችግሮቹ በሁለት ደረጃ ሊታዩ የሚገባቸው መሆኑ ለየን።
ሀ. አከባቢውን ብቻ የሚመለከቱ አከባቢያዊ መፍትሄ የሚፈልጉ ጥያቄዎች/ችግሮብ በተለያዩ ቀበሌዎች መኖራቸው፣
ለ. መላው ኢሮብን የሚመለክቱና አስቸኳይ መፍትሄ የሚሹ፣

የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ይዘት ባጭሩ፥

ሪፖርቱ ወደ 30 ወርቀት (60 ገፅ) የነበረው ደብተር ላይ የተፃፈ ሆኖ፣ በመግቢያ ደረጃ ስለ ኢሮብ ህዝብ ታሪክ፣ ማንነት፣ ባህልና ስነልቦና ሰፋ ያለ ዝርዝር የያዘ፣ በመቀጠል የኢሮብ ህዝብ ለብዙ ዘመናት ስለነበረው ራስ ገዝ የኦና ስርዓት የሚገልፅ፣ የኢሮብ ህዝብ በፅሁፍ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በቃል ደረጃ ለሁሉም ችግሮች ሆነ ወንጀሎች መፍቻ በህዝባዊ ሽንጎ አማካይነት የተደነገጉ ህጎች እንደነበሩት፣ የራስ ገዝ የኦና ስርዓት እንዴት በአፄ ኃ/ስላሴ ስርዓት እንደፈረሰና የኢሮብ ህዝብ አፄ ኃ/ስላሴ ኢትዮጵያን አንድ ማድረጋቸው የሚደግፍ ሆኖ ያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ራስ ገዝ የኦና ስርዓቱን በሃይል ማፍረሳቸው የሚኮንነው መሆኑ፣ ከኦና ስርዓት መፍረስ እስከ 1966ቱ አቢዮት እንዴት ሲተዳደር እንደቆየ፣ አሁንም ያ ራስ ገዝ የኦና ስርዓቱ እንዲመለስለት የሚፈልግ መሆኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ተቀምጦ ነበር። ያ ሪፖርት የኢሮብ ህዝብን ለማያውቅ የውጭ ሰው የኢሮብ ህዝብን ማንነት፣ ባህልና ስነልቦና በትክክል የሚያሳይ ሪፖርት ሆኖ ለሁለታችን በተሰጠው ተልእኮ መሰረት የኢሮብ የወቅቱ መሰረታዊና አስቸኳይ መፍትሄ የሚሹ ጥያቄዎች/ችግሮችም በቀደም ተከተል ከነ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦችም የተቀመጡበት የተሟላ ሪፖርት ነበር።

የየአከባቢው ጥያቄዎች/ችግሮች ህዝባዊ አስተዳደር ሲመሰረት ከአስተዳደሩ ጋራ በመሆን የሚፈቱ መሆናቸው በማመን አጠቃላይ ኢሮብን በሚመለከቱት ላይ ብቻ በማተኮር በድርጅት ደረጃ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኙ ያልናቸው ለይተን አስቀምጠን ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንሰጥ እንዲሁም አመራሩ ስለ ኢሮብ ህዝብ ትክክለኛ ስዕል እንዲያገኝ የሚያስችል ዝርዝር ሪፖርት ማቅረብ አለብን በሚለው ተስማምተን ቀጥለው የተቀመጡ ሶስት ጥያቄዎች/ችግሮች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኙ በሚል ለይተን አስቀመጥን።
1. በወቅቱ መሬት አልባ የነበሩ ወጣት አርሶ አደሮች መሬት የማግኘት ጥያቄ፣
2. የራስ ገዝ (Autonomous) ክልልና የኦና ስርዓት የመመለስ ጥያቄ
3. ኢህአፓ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡን ከከተማ ግኑኝነት የማይነጥል፣ በተለይ ከደርግ ስርዓት የሚያገኘው አገልግሎት በማይቋረጥበት መንገድ በጥንቃቄ እንዲሆን የሚሉት ዋነኞቹ ነበሩ።

ጓድ ገረይ በሙያው አስተማሪ የነበረና የሪፖርት ማዘጋጀት ልምድ የነበረው ስለነበረ፣ ከኔ የሚፈልገውን ሃሳብ/አስተያየት ወስዶ ስለ አጠቃላይ እንቅስቃሴውና በተለይ ለሁለታችን የተሰጠው ተልእኮ በተመለከተ ለአመራሩ የሚቀርብ ዝርዝር ሪፖርት ከነ የመፍትሄ ንድፈሃሳቦች/Proposals በሶስት ቀን ውስጥ በጽሁፍ አዘጋጀ። ጓድ ገረይ በጣም ዴሞክራትና በጋራ ስራ የሚያምን ጓድ ስለነበረ ያዘጋጀው ሪፖርት የጋራችን ለማድረግ እኔም እንዳነበውና ሃሳብ እንድሰጥበት አድርጎ፣ እኔም ብዙ ተምሬበት፣ ሙሉ በሙሉ ተስማምቼበት ሁለታችን ሪፖርቱን ለአመራር ቀረብን።

ከኢህአፓ አስቸኳይ መልስ የሚሹ ተብለው በተቀመጡ ጥያቄዎች/ችግሮችና የቀረቡ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦች፣

እላይ የተጠቀሱት ሶስቱ ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት የቀረቡት የመፍትሄ እርምጃዎች ክዝህ ስር በቅደምተከተል ተቀምጠዋል፡፡

መሬት ለወጣት አርሶ አደሮች ማከፋፈልን በተመለከተ፣

የመሬት ጥያቄ ሁሉንም በሚያስማማ መንገደ በአገባቡ ካልተፈታ፣ መሬት አልባ በነበሩ አብዝሃ ወጣት አርሶ አደሮችና የነበረው ጠባብ ለም መሬት በርስት ይዘው በነበሩ ውሁዳን ባለርስቶች መካከል የሚጀመረውና ወደ ጎሳዎች/መላ አድጎ የኢሮብ አናሳ ብሄረስብን አንድነት ሊያናጋ ይችላል የሚል ስጋት በጓድ ገረይ በኩል ነበር። በኢህአፓ በኩል ደግሞ መሬት ለአራሹ ከሚለው አቋሙ በመነሳት መሬቱ ከባለ ርስቶች በሃይልም ቢሆን ተወስዶ ለውጣቶቹ መሰጠት አለበት የሚል የጸና አቋም እንደነበረም ይታወቅ ነበር። ነገሮችን አርቆ ለማየት ልዩ ተስጥኦ የነበረው ጓድ ገረይም በኢሮብ የመሬት አከፋፈል በተመለከተ አቋሙን እንዲቀይር ከአሳማኝ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦች ጋራ መቅረብ እንዳለብን ቀድሞ ተረድቶ ለዚህ በጋራ እንድንገፋ መከረኝ እኔም በሃሳቡ ሙሉ በሙሉ ተስማማሁ። በዚህ መሰረትም ኢህአፓ በኢሮብ የመሬት መከፋፈል በመሬት ለአራሹ መርህ መሰረት መከፋፈሉን ከማረጋገጥ ውጭ በቀጥታ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብና ለኛ ለብሄረሰቡ ተወላጆች ከህብረተሰቡ (ከባለ ርስቶቹም ከመሬት ፈላጊ ወጣቶችም) ጋራ በኢሮብ ባህል መሰረት ተመካክረን በሁለቱም ስምምነት እንድንፈታው ዕድል እንዲሰጠን የሚጠይቅ ቀጥሎ የተቀመጡ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦች በሪፖርቱ ተካተቱ።
 ባለ ርስቶቹን በየግልም በቡድንም በማነጋገር በርስት የያዙት መሬት በፈቃደኝነት እንዲያከፋፍሉ ማግባባት/ማሳምን እንችላለን፣
 ለዚህም ከኛ በተጨማሪ ርስትና ሸሐና በመባል ይታወቅ የነበረው የቆየ የመሬት ስሪት እንዲሻሻል ሲጥይቁ የነበሩ ታዋቂ አባቶች መጠቀም፣ ከዚህ ከዘለለም ለረጅም ዓመታት የዳበረው የኢሮብ የሽምግልና ስርዓትም መጠቀም እንችላለን።
 በዚህ ሂደት፣ ድርጅቱ በመሬት ጥያቄ ላይ ባለው አቋም መሰረት መሬት ለሁሉም አራሽ በእኩል ተከፋፍሎ፣ የኢሮብ ህዝብ አንድነትም ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል፣ የሚሉ ነበሩ።

ራስ ገዝ የኦና ስርዓት እንዲመለስለት ህዝቡ የጠየቀውን በተመለከተ፣

 የኢሮብ ብሄረሰብ ለብዙ ዘመናት በዘለቀ ራስ ገዝ የኦና ስርዓቱ ምክንያት የዳበረ የውይይትና ጉዳዮችን በዴሞክራሲያዊ ውሳኔ መሰረት የመፍታት ሃብታም ባህልና ልምድ ያለው ማህበረሰብ ስለሆነ፣ ማንነቱ ጠንቅቆ የሚያውቅና በኢትዮጵያዊነቱም ፈፅሞ የማይደራደር ህዝብ ስለሆነ፣ የራሱ ቋንቋ/ሳሆ፣ ባህልና ስነልቦና ያለው ህዝብ ስለሆነ፣ ይህ አናሳ ብሄረስብም በእንክብካቤ መጠበቅ ያለበት ስለሆነ በጥያቄው መሰረት ኢህአፓ ይህን ተቀብሎ፣ የኦና ስርዓቱ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጋራ ሊሄድ በሚችልበት መንገደ እንዲቀጥል መርዳት የምችለውን ቢረዳ እንላለን።
 የኢሮብ ህዝብ የቆየ መሪዎቹን በዴሞክራሲያው መንገድ የመምረጥ የዳበረ ባህልና ልምድ ስላለው መሪዎቹን ራሱ እንዲመርጥ መድረክ ከማመቻቸት ውጭ ጣልቃ ባይገባበት፣ እንደ ድርጅትም ከህዝቡ ጋራ የሚደረጉ ግኑኝነቶች በነዚህ በህዝብ በተመረጡ መሪዎች በኩል ብቻ ቢደረጉ ኣንላለን።

ኢህአፓ/ሰ በአከባቢው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡን ከከተማና ከደርግ ስርዓት የሚያገኘው አገልግሎ ላይ ችግር በማይፈጥር መንገድ እንዲሆን የቀረብ ጥያቄን በተመለከተ፣

ያኔ መላው ምስራቃዊ ትግራይ ገጠርና ራሱ ዛላምበሳ የጉለማክዳ ወረዳ ዋና ከተማ ጨምሮ ከደርግ ስርዓት ቁጥጥር ውጭ ስለነበረ፣ ህዝቡ ከከተማ የሚፈልጋቸው ነገሮች የሚያገኘው በደርግ ቁጥጥር ስር ከነበረው ከዓዲግራት ከተማ ነበር። ስለሆነም ከአከባቢው ወደ ዓዲግራት ለተለያየ ቆሳቁስ ፍለጋ ለሚሄደው ህዝብ በደርግ ካድሬዎች በአከባቢው ይንቀሳቅሱ ስለነበሩ አማጺ ሃይሎች ብዙ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር፣ ምርመራም ይደረግበት ነበር። በተለይ የኢሮብ ወረዳ በተመለከተ በወቅቱ በወረዳዋ የነበረው ብቸኛ በካቶሊክ ቤተክርስትያን የሚካሄድ የነበረ የዓሊተና ክልንክና ብቸኛው የልደታ ት/ቤት በተመለከት የደርግ ካድሬዎች ለህዝቡ ኢህአፓ በነዚህ ተቋማት ላይ ይጠቀም እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ጥያቄ ያቀርቡ ስለነበረ፣ በዓሊተና ከነበሩ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጋራ ይገናኛል የሚል ጥርጣሬም ስለነበረ፣ በተቋማቱ አከባቢ የኢህአፓ ሰዎች ከመታየት እንዲቆጠቡ፣ ከካህናቱ ጋራ የሚደረግ ማንኛውም ግኑኝነት የተለየ ጥንቃቄ እንዲደረግለት የህዝቡ ፍላጎትና ጥያቄ ነበር። ምክንያቱም በሆነ ምክንያት በክልኒኩ፣ በት/ቤቱ፣ ከካቶሊክ መንኮሳት ጋራ ኢህአፓ ግኑኝነት እያደረገ መሆኑ ከታወቀ፣ ደርግ ት/ቤቱንም ክልንኩንም ከመንግስት ያገኙት የነበረው ማንኛውም አገልግሎት ሆነ ማተሪያል ሊዘጋው ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት ስለነበረ ማንኛው ከተባሉት ተቋማት ጋራ የሚደረግ ግኑኝነት በምስጥርና በተወሰኑ በጣም በሚታመኑ ግለሰቦች ብቻ ቢደረግ።

ከላይ የተቀመጡ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦችን የያዘ ዝርዝር ሪፖርቱ የቀረበለት አመራር ስለ ሁለቱ (ስለ ራስገዝ የኦና ስርዓትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስለሚደረገው ግኑኝነት መደረግ ያለበት ጥንቃቄ) በተመለከተ የቀረቡለትን የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦችን ተቀብሎ ስለ መሬት ለወጣቶቹ ማከፋፈል በተመለከተ የቀረቡትን ግን አልቀበልም አለ። ለዚህ የተቀመጠው መከራከሪያ ሃሳብ ደግሞ ኢህአፓ ውግንናው ለጭቁኑ የአርሶ አደር ክፍል እንደሆነ ድርጅት ከባለርስቶቹ ጋራ መነጋገር/መደራደር ሳይሆን እነሱን በሁሉም መንገድ አስገድዶ ማንበርከክና አስተሳሰቡም እንዲጠፋ ማድረግ የሚል ሆኖ በርስት የያዙት መሬት ካስፈለገ በሃይል ተነጥቀው ለመሬት ፈላጊ ወጣቶች በእኩል መካፈል አለበት በማለት ንድፈ ሃሳቡን ውድቅ አደረገ።

ጓድ ገረይ ይህ የአመራር ውሳኔ በመቃወም ይህ ተግባራዊ እናድርግ ማለት የኢሮብ ህዝብ እንዲከፋፈል በር መክፈት ነው፣ ኢህአፓ በርግጥ ጸረ መስፍናዊና ጸረ መሳፍንት ስርዓት የሆነ ድርጅት ቢሆንም ኢሮብ ውስጥ መሳፍንቶች የሉም፣ በአጼው ስርዓት በተደነገገው የመሬት ስሪት/ህግ መሰረት የተወሰነ መሬት በርስት ይዘው የቆዩ የኢሮብ አባቶች መሬቱን በርስት ብይዙትም በኢሮብ በቆየ ባህል መሰረት ከመሬቱ የተገኘውን ከሌሎች ጋራ ተካፍለው እየበሉ የነበሩ ናቸውም፣ አሁን የመሬት ስሪቱ መቀየሩን፣ አሁን በሃገር ደረጃ ያለው ስሪት/ህግ መሬት ለአራሹ የሚል መሆኑን፣ በሚገባ ካስረዳናቸው በኢሮብ የቆየ በውይይትና በሽምግልና ባህል መሰረት ቀርበን ካነጋገርናቸው እነዚህ ባለ ርስቶች በፈቃደኝነት መሬቱን እንደሚያካፍሉ ምንም ጥርጥር የለኝምና እነዚህ ሰዎች ከመጫን/ከማስገደድ በውይይት በማሳመን ችግሩን ለመፍታት አመራሩ ዕድሉን በድርጅቱ ውስጥ ላለን የኢሮብ ተወላጆች ሊሰጠን ይገባል ብሎ አጥብቆ ተከረከረ። ባጋጣሚ በወቅቱ ገና አዲስ ከከተማ መጥቶ ‘በኢንተልጅንስ’ ስራ ተመድቦ ሲሰራ የነበረ ጓድ ሓዲሽ በየነ/ማጋቢዳጋ በቦታው ስለነበረ፣ እሱም በጉዳዩ ገብቶበት ጓድ ገረይን በመደገፍ አመራሩን ለሁለት በመሆን ሞገቱ። ጓድ ሓዲሽ ሲጀምር፣ ጓድ ገረይ እንዳለው ኢሮብ ውስጥ እናንተ የምትገምቱት ዓይነት መስፍን/መሳፍንት የሉም። የኢሮብ ህዝብ ያለውን አብሮ ተካፍሎ የሚበላ፣ ከጥንት ጀምሮ የውስጥም ሆነ የውጭ ችግሮችን በውይይት የመፍታት የዳበረ ባህል ያለው፣ በሆነ ምክንያት አንድነቱን ሊያናጋ የሚችል ችግር በውስጡ ቢፈጠር እንኳን ይህን በውይይት ሲፈታ የኖረ፣ ይህን ቀላሉን በርስት መሬት የያዙ ጥቂቶች በቀላሉ በማሳመን መሬቱ ለሁሉም በእኩል እንዲካፈል ለማድረግ ስለምቻል የጓዱ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳብ ተቀባይነት ማግኘት አለበት በማለት ተከራከረ። ጓዶቹ በህዝባቸው አንድነት መጠበቅ ላይ አጥብቀው የሚያምኑና ለዚህም መከፈል የሚገባውን መስዋእትነት ለመክፈል የቆረጡ ስለነበሩ፣ አመራሩም በመረጃ የተደገፈው የጓዶቹ ሃሳብ ስለተቀበለ ከሰፊ ውይይትና ክርክር በኋላ አመራሩ የጓዶቹን ሃሳብ ተቀብሎ በኢሮብ መሬት በጓድ ገረይ በቀረበው የመፍትሄ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ኣንዲከፋፈል ተወሰነ፣ ይህ ንድፈ ሃሳብም ከኢሮብ ውጭ በመላው ምስራቃዊ ትግራይ ኢህአፓ መሬት ሲያከፋፍል እንደ ግብአት ተጠቀመበት።

አመራሩ ንድፈ ሃሳቦቹን ከተቀበለ በኋላ የመሬት ማከፋፈል ስራ ከመጀመሩ በፊት ጓድ ገረይ ባለ ረስቶቹን የማነጋገርና የማሳመን ስራ ወዲያውኑ ጀመረ። እኔም ከቦታ ወደ ቦታ እየዞርኩ ህዝቡን መሬት እንደሚከፋፈል በማሳወቅ እንዴት መሬት መከፋፈል እንደሚፈልግ የህዝቡን ሃሳብ ማሰባሰብ ጀመርኩ። ይህ ስራ ከሕዳር- ጥር 1968 በነበረው የ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተካሄደ። እንደተገመተውም ብዙዎቹ ባለ ርስቶች በቀላሉ ለማግባባት ተቻለ፣ በጣት የሚቆጥሩትን ደግሞ በቆየው የኢሮብ የዳበረ የውይይትና የሽምግልና ባህል መሰረት ማሳመን ተችሎ፣ ከህዝቡ መሰብሰብ የነበረበት ሃሳብም በሚገባ ተሰብስቦ የቆየው የመሬት ስሪት በአዲሱ መሬት ለአራሾች ስሪት መሰረት ለማሻሻል ህዝባዊ ስብሰባ መጥራት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ።
ከላይ በጭሩ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በኢሮብ በርግጥ በጽሁፍ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በቃል ደረጃ ሁሉም ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለበት ለሁሉም ችግር አፈታት የተቀመጠ ህግ ነበረ። ለመሬት ማከፋፈሉ በቃል ደረጃ የነበረ ህግ የነበረ ቢሆንም ይህ ህግ ከአዲሱ የመሬት ላአራሹ አዋጅና የኢህአፓ በመሬት ጥያቄ ላይ ከነበረው አቋም ጋራ ሊስማማ በምችል ደረጃ መሻሻል ነበረበት። በነገራችን ላይ ኢህአፓ መሬት ጥያቄ ላይ የነበረው አቋም ለማወቅ ለምትፈልጉ በያትልድ ድረ ገፅ በዴሞክራሲያ እትሞች ስር የጥቅምት 05፤1967ቱን ቁ_12ን መመልከት ትችላላችሁ።
http://www.yatewlid.org/images/PDF/Democracia/Demo_01/Demo_Vol_1_No_12_Tikmet05_1967.pdf

የቦካለ፟ማኮ ስብሰባ

በኢሮብ ከጥንት ጀምሮ መላው ኢሮብን የሚመለከቱ ጉዳዮች/ህጎች ማሻሻል ሆነ አዲስ ህግ ማውጣት ሲያስፈልግ በኢሮብ የቆየ ባህልና አሰራር መሰረት በህዝብ በተወከሉ የህዝብ ተወካዮች አማካይነት ነበር የሚሻሻሉት/የሚወጡት። የቦካለ-ማኮ ስብሰባ መጠራት ዋነኛው ምክንያትም በኢሮብ የቆየውን የመሬት ስሪት/ህግ ከመሬት ላራሹ አዋጅና የኢህአፓ የመሬት ጥያቄ አቋም ጋራ በሚያስማማ መንገድ ለማሻሻል የመላው ኢሮብ ተወካዮች መገኘት ያስፈልግ ስለነበረ ነበር። ለዚህ ስብሰባ ከመላው ኢሮብ በየቀበሌው በነበረው ህዝብ ብዛት መሰረት ከሁሉም ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች ከ300 በላይ ተወካዮች ተመርጠው የተሳተፉበት፣ ከሶስቱ ኢሮብ (አድጋዲ-ዓረ፣ ቡክናይቲ-ዓረ፣ ሓሳባላ) ከሁሉም የህ/ሰብ ክፍሎች (በዕድሜ የገፉ ሽማግሌዎ፣ ታዋቂና ተሰሚ የነበሩ ግለሰቦች፣ ባለርስቶቹ፣ መሬት ፈላጊ ወጣቶች በሚገባ የተወከሉበት በትክክል መላው ኢሮብ የሚወክል ስብሰባ ነበር። ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት የመላው ኢሮብ ተወካዮች ስብሰባዎች የሚካሄዱ የነበሩት በዓሊተና/አግለ ሓዳ በሚባል ዛፍ ስር የነበረ ቢሆንም የመሬት ስሪት ለማሻሻል ያኔ የተጠራው ስብሰባ ብዙ ሰው የሚሳተፍበት ስብሰባ እንደሚሆን አስቀድሞ ስለታወቀ ስብሰባው ከዓሊተና ወጣ ብሎ በሚገኝ በቦካለ፟ማኮ(ቦካለ-ማኮ) እንዲደረግ ተወሰነ። ቦካለ-ማኮ ለማታውቁት ከዓሊተና ከተማ በስተሰሜን ወደ 15 ደቂቃ የእግር ጉዞ ርቀት ላይ የሚገኝ ትላልቅ በዛ ያሉ የወይራ ዛፎች የነበረበት የወንዝ ዳርቻ ነው።

በክፍል ሶስት፣ የስብሰባው አካሄድ እንዴት ነበር፣ውጤቱስ ምን ሆነ በሚለው ዝርዝሩን ይዤላችሁ እቀርባለሁ፣
እስከዛው በቸር ሰንብቱ፣ የነገ ሰው ይበለን።

YATEWLID.ORG

Address


Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Concerned Irobs/ተቆርቋሪ ኢሮቦች posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Concerned Irobs/ተቆርቋሪ ኢሮቦች:

  • Want your organization to be the top-listed Government Service?

Share