07/09/2022
በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአመራር አካላት የዉይይት መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
ጳጉሜ፦ 02/13/ 2014 ዓ/ም የኢሠራ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
በዳውሮ ዞን ኢሠራ ወረዳ አጠቃላይ የወረዳው አመራር አካላትን ያካተተ በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የዉይይት መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
በዉይይት መድረኩ በሀገሪቱ ለ3ተኛዉ ጊዜ የተከፈተውን ጦርነት ሕዝቡ በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ የተመሠረተ የአሸናፊነት መንፈስ በመላበስ ሊመክት ይገባል ተብሏል።
በተያያዘም ሁሉም ዜጋ በሀገር ሉዓላዊነትና በህዝብ ክብር ላይ የተቃጣውን ጦርነት በኢትዮጵያዊ አንድነትና ጀግንነት ማስቆምና ድልም መቀናጀት በሚያስችል ሁኔታ እንደሚመክር ይጠበቃል።
ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይን በማስመልከት የሚደረግ ውይይትና የጋራ ትግል ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቅሷል።
በሀገር የተጀመረውን ለዉጥ በማደናቀፍ ሀገሪቱን የማፍረስ ዓላማ ያነገቡ አካላት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ጥፋቶችን ሲፈጽሙ እንደ ነበርም ከመድረኩ ተጠቁሟል።
ይኼዉ የጥፋት አጀንዳ መያዛቸዉ ለሠላም የተዘረጋውን ዕድል በማምከን ወደ 3ኛዉ ዙር ጦርነት እንዳስገባቸዉ ያስታወሱት የኢሠራ ወረዳ/ዋ/አስ/ሪ አቶ ጌታሁን ደራ በዚህም ህዝብና ሀገር ላይ ትልቅ በደል መፈፀሙን ገልጸዋል።
አያይዘውም መንግሥት ከጦርነት ይልቅ የሠላም አማራጭ ማቅረቡን የጠቀሱት አስተዳዳሪው ይኼዉ አሸባሪ ቡድን ለሠላም የተሰጠዉን ዋጋና ዕድል ተቀባይነት በማሳጣቱ ሀገሪቱ ተገዳ ወደ ጦርነት እንዲትገባ መገደዷንም ጠቁመዋል።
አክለውም አሸባሪዉ ህወሃት ለ3ተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ አመራሩ እና ሕዝቡ የጋራ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።
በመጨረሻም ሀገሪቱ ችግር ሲያጋጥማት አመራሩ፣ የፓርቲዉ አባላትና በየትኛዉም ደረጃ የሚገኙ አካላት ተገቢና ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታና መረጃ በተገቢው በመረዳት እንዲሁም ከሀሰተኛ መረጃ ምንጮች በመጠንቀቅ በሀገርና በህዝብ ላይ የተቃጣውን ጦርነት በጋራ ለመመከት ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ የኢሠራ ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ዓለማዬሁ ጎምኦሌ በአስተያየታቸው አመላክተዋል።
" ለሀገር ክብር፣በትግል እናብር ! "
ዘገባው የኢሠራ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።