የግጥም አለም

የግጥም አለም ገጣሚዎችን እና አፍቃሪዎቻችውን ማቀራረብ

14/09/2019

የማጀት ስር ወንጌል

ሙያተኛ ሀገሬ ከማጥገብ ጎደለ በረከት እራቀው የገበታሽ ለዛ፣
ተሻምቶ ለመጉረስ ከበላነው ይልቅ የደፋነው በዛ፡፡

ሙያሽ ባያስደፍር አጀብ ቢሰኙበት፣
ማዕዱ ቢሙላላ ዓይነቱ ቢያምርበት፣
አበዛዙ አይደለም አበላሉ ላይ ነው የገበታሽ ውበት፡፡

እየተማመንን! የፉክክር ቅሚያ በርሃብ እየናጥን፣
ከደፋነው ጠግቦ ውሻችን በለጠን፡፡

ከምርት አላነስን፣
ጎተራችን ሙሉ ጀግና አራሽ መች አጥተን፣
ማሰብ የጎደለው አያያዛችን ነው ገደል የከተተን፡፡

ይልቅ ግዴለሽም! ከምግባር ምጣድ ላይ ሳንበስል አንጋግተሸ ከማዕድ አትምሪን፣
ገበታሽ እንዲያምር ከእግዜር የሚያስታርቅ ፍቅር አስተምሪን፡፡

ገበታ ዕድሜ ነው ባለ ማሰብ መክነን፣
ሳንፀነስ ጃጀን፣
ሳንጣድ አረርን፣
ከዘመን ገበታ ከፊደል አቅድመን ዘር እየቆጠርን፡፡

ገበታ ሀቅ ነው በክፋት ሊጥ ጋግረው ያሻገቱት እውነት፣
በሆዳም እስክስታ ረግጠው ያፈኑት የምስኪናን ጩኸት፡፡

እስከ ልጠይቅሽ በጥም ደዌ ደቆ የረሃብ ጠኔ ደፍቶት እልፍ ትውልድ ያልፋል፣
ቢራ ለመጥመቂያ ሚበተን ገብስ ግን ከሀገር መች ይጠፋል፡፡

ከሆድ በማይሻገር የማጀት ቤት ዕውቀት አጥብበሽ አትለኪን፣
እስቲ መኖር ይግባን ከማስተዋል መቅደስ ሰው መሆን ስበኪን፡፡

ዘመን ካልገበረው ከችጋር ተራራ ከሲኦል ዳር ኑሮ፣
እንዴት ነው መሻገር ከመርፌ ቀዳዳ በጠበበ አይምሮ፡፡

ከምስኪን ዘመን ላይ የማይኖሩበትን ዕድሜ መበዳደር፣
ለአንዲት ማምሻ ደስታ በአያት እስትንፋስ ላይ ቁማር መደራደር፣
ያሳፍራል አይደል?

እያደጉ ማነስ እያነሱ መዝቀጥ፣
አጎንብሶ ያፀናን የድሃ እናት ጉልበት በጭካኔ መርገጥ፣
ያሳምማል አይደል?

መንገስ ከሚያባላስ መጥገብ ከሚያቃቅር ማግኘት ከሚያጎለን፣
ማጣት ውሎ ይግባ ባርነት ይሰንብት ድህነት ይግደለን፡፡

ከረፈደ ፀፀት ደረት እየደቁ ከእግዜር ቢዋቀሱ፣
ትርጉሙ ምንድነው ሲኖር ተቃቅሮ ሲሞት መላቀሱ፡፡

በእናታችን አድባር በፍቅሯ ይሁንብን፣
መድመቅ ካጋደለን ቆሽሸን ይመርብን፡፡

በመጠማት ሲቃ እስትንፋስ እስኪያንቃት ነፍሳችን ትርበትበት፣
ብቻህን ከመጥገብ አብሮ መራብህ ነው ሰው የመሆን ውበት፡፡

በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ አይንዳን፣
በማሰብ ስር እንፈወስ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን ከመንጋነት ሚያግድ እረኛ አያሻህም ከህሊናህ በላይ፣
ስታስብ መሪ ነህ በብስለት ከፍታ በማስተዋል ሰማይ፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን የጎጥ አረም ነቅለህ በአንድነት መስክ ላይ ፍቅር ትዘራለህ፣
በወረወሩብህ የጥላቻ ድንጋይ ትውልድ የሚያፋቅር ድልድይ ታበጃለህ፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን ዝምታህ ኃያል ነው ጀግና የሚያንበረክክ፣
ከፈሪ ቀረርቶ ከባዶ ሰው ጩኀት፣
ሀገር ላምስ ከሚል በመንደር አጀንዳ በአሽኮለሌ ተረት፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን ነጻ ነህ እያሉህ መታሰር ያምርሃል፣
መቀመቅ መበስበስ፡፡

የኖርክለት እውነት ሀገር እስኪፈታ፣
በሀቁ እስኪመዘን ስለ በርባን ክብር የቆሸሸው ፍቅር የታሰረው ጌታ፣
ከድል ታሪክ ሰማይ ከሥልጣኔ ዳር ከጥበብ ከፍታ፣
እንሻገራለን ህዝብነትን ትተን ሰው የሆንን ለታ፡፡

በትረ ጥበበ ቢካን ዓለም ሊያንቀጠቅጥ ድል ሥልጣን ቢሰጠው፣
ጀግና መሪ አይደለም ብርቱ ተመሪ ነው ሀገር ሚለውጠው፡፡

አስተውል ወዳጄ ጠልተን ላንጣላ ችለን ላንጋደል ነደን ላንፋጀው፣
የኛው ትርምስ ነው በልቶ ለሚያባላ ጠላት ሚበጀው፡፡

ስጋና ደም እንጂ የአንድነታችን ውል የፍቅራችን ቀለም፣
ያሰመርነው ክልል የታጠርንበት ዘር ቋንቋችን አይደለም፡፡

ከመዋሃድ መቅደስ ትውልድ እናስተምር፣
ዘመን ይመርቀን ፍቅራችን ምን ጎድሎት ደማችን ያስታርቀን፡፡

በልጆቿ አጥንት በደም ኪዳን ምለን የገባንላት ቃል፣
ከጩኀት ያለፈ ዘመን የሚሻገር ተግባር ይጠይቃል፡፡

በአንድ ሃሳብ ተጋምደን በድል ድር እናብር ውድቀታችን ያንቃን፣
ሠርተን እናሳምን ሆነን ድል እንንሳ የአፍ ጀግንነት ይብቃን፡፡

ምስኪኒቷ እናቴ! በሞላ ጎዳና ባልጠበበ ድንበር በዘር ገመድ ታግዳ፣
ነጻ ነኝ ትላለች መንጋነት ያሰረው ባሪያ ትውልድ ወልዳ፡፡

የጀግንነት እብሪት ልባችንን ደፍኖት ማሰብ እየከዳን፣
እንዴት ነው ነጻነት እንዳበደ ፈረስ ስሜት እየነዳን፡፡

ገድሎ የመንገስ ጥማት ጩኀት ላገነነ አመጽ ላጀገነው፣
ለዚህ ምስኪን ትውልድ በጅምላ እየነዱት፣
በመንጋ እያሰበ ነጻነት እንዴት ነው?

ነጻነት ምርጫ ነው አምሮ ቢደላደል ጥፋት ያመነነው የመንጋዎች መንገድ፣
እንቅፋቱን ወዶ ለኖሩለት እውነት ለብቻ መራመድ፡፡

ነጻነት ማመን ነው ቀን ወዶ ቢያጀግን ቀን ጠልቶ ቢከዳም፣
ቢቆሽሹም ቢደምቁም እራስን መቀበል ራስን መምሰል ነው የነጻነት ገዳም፡፡

ነጻነት ማሰብ ነው በአንድነት መለምለም የኔነትን አረም ከህሊና ማጥፋት፣
ዘር ሆኖ ከማነስ ሀገር ሆኖ ማበብ ዓለም ሆኖ መስፋት፡፡

ንገሯት ለሀገሬ በጀግኖቿ ትግል ድንበር ባታስደፍር ከእጀ ገዥ ብትወጣ፣
ነጻ ነኝ እንዳትል በገዛ ልጆቿ በእጅ አዙር ተሸጣ ፡፡

ስሩን ካልሸመነው በመዋሃድ ጥለት በማስተዋል ሸማ፣
ታሪክ አናደምቅም በጭብጨባ ድግስ በሆይ ሆይታ ዜማ፡፡

ምን ብናቀነቅን በየሰልፉ ሜዳ ወኔ ብንደግስም፣
በፈረሰ አይምሮ በደቀቀ አንድነት ሀገር አናድስም፡፡

በጭፍን ከመሮጥ አስቦ ማዝገም ነው የመራመድ ውሉ፣
ሁሉም እንቅፋቶች እስኪጥሉን ድረስ ምርኩዝ ይመስላሉ፡፡

በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ አይንዳን፣
በማሰብ ስር እንፈወስ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡

ከእግዜር ልንወዳጅ ለምህረቱ ጥላ እምባ ብንደግስም፣
ልብን ሳይመልሱ ለንስሃ መሮጥ ከጽድቅ አያደርስም፡፡

ውብ ነገን እናውርስ ትላንትን አክመን በይቅርታ ፀበል፣
ትውልድ ይጨርሳል ያረገዝነው እምባ የቋጠርነው በቀል፣
ከመስጠት አንጉደል ከቀማኞች ገደል ተረግጠን ብንጣል፣
ካሸከሙን በቀል ምናወርሰው ፍቅር ሀገር ይለውጣል፡፡

ከዕድሏ ጣሪያ ላይ ዘር የቀዳደው ሽንቁሯ ቢበዛም፣
ያ ከንቱ ፎካሪ ባፈጀ ቀረርቶ ሺህ ጉራ ቢነዛም፣
ሚሊዮን ዘር ቢሸጥ አንድ ሀገር አይገዛም፡፡

ኢዮጵያዊነት ነው የትርታችን ልክ የነፍሳችን ግጥም፣
መልስ ቤት በራቀው በከረመ ፀሎት ሰርክ ብታንጋጥም
አጎንብሳ ድሃ ባፀናችው ጉልበት ብትረጋገጥም
ነፍሷን አደህይታ ባሻረችው ቁስል ብትገሸለጥም፣
ሀገር ሆና ገዝፋ በየ ጎጣጎጡ አትርመጠመጥም፡፡

የዘመን እውነት ነን ከደግነት ሰማይ በጥበብ የኖርን፣
ትዕግስትም ልክ አለው ፈርተን እንዳይመስለው ስላቀረቀርን፡፡

ማተብ አስሮን እንጂ ተጣልተን እንዳንቀር በክፍፍል ገደል፣
ከሀገር ክብር በልጦ ሞት ብርቃችን አይደል፡፡

ንገሩት ለዛ ሰው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ኃይል እንደ ተራራ ገዝፎ ቢከመርም፣
ክንዱን አፈርጥሞ እልፍ የሰገደለት ጀግና ቢሰድርም፣
ዓለም የሞተበት የጠላት ማርከሻ ጦር ቢደረድርም፣
በአንድ ዓይናችን ሰላም በኢትዮጵያችን ክብር አንደራደርም!!!

~ ሕሊና ደሳለኝ

26/04/2019
26/04/2019
15/02/2019

https://youtu.be/E5wj3NrSRCQ

ልክ እንደ አውሮፓ እና አሜሪካ ጊዜ ቁጠባ በ አዲስ አበባ ተጀምሯል የሚያሰኝ ትዕይንት

https://youtu.be/UVuZMAgKmpA
06/12/2018

https://youtu.be/UVuZMAgKmpA

የትግላችን ልኩ የአሳር ደም ቢያስምጥም በሰፋ አገር ጠበን ኢትዮጵያን አንሰጥም by Helina Desalegn

03/10/2018

ኢትዮጵያ እመ-መከራ
የግዜር መመራመሪያው የስቃይ ቤተ-ሙከራ

መውደቅማ ነበር ያባት
እንደ ያሬድ እስከ ሰባት
እንደ በላ ብላቴና ፣ የእንክርዳድ ሙልሙል እንጎቻ
የትውልዴ እጣ ፋንታ ፣ መውድቅ መውድቅ መውድቅ ብቻ…

/በዕውቀቱ ስዩም/

12/07/2018

By
===================================
እንደምነህ ህውሀት ፣ እኔ አለሁ በጤና
ጤና እንደነሳኸኝ ፣ ጤና ይንሳህና
አለሁ ተደምሬ
ከሻብያ መንግስት
ተላላኪ ሴት ጋር ፣ ቀለበት አስሬ
ትውልድን ልቀጥል
ፍቅር እያነሳሁ ፣ ጥላቻዬን ስጥል
አለሁ ቃል ገብቼ ፣ ሀገር ላልገነጥል።
።።።።።።።።
አንተ ግን እንዴት ነህ
ተጠማሁኝ ላለ ፣ ሆምጣጤ ምትጥል
የወንድ ብልት ላይ
አምስት ሌትር ውሃ ፣ የምታንጠለጥል
ወንድ የምታኮላሽ ፣ ወንድ የምታመክን
እንደምነህ ህወሀት ፣ እንደምነህ አንተ ግን?
ህዝቡን በዘር በዘር ፣ ከፍለህ ምታፋጀው
የገዛ ህዝብህን ፣
ጠባብ አሸባሪ ብለህ ምትፈርጀው
በገዛ ህዝብህ ላይ ፣ ጦር ምታደረጀው
በዘግናኝ ሁኔታ ፣ ዜጋህን ምትረሽን
ሰማህ ወይ ሲወራ
መግደል ማሰር መግረፍ ፣ ያለፈበት ፋሽን
የወደቀ ሀሳብ ፣ መሆኑ ሲነገር
በወደቀ ሀሳብ
እንደማትነሳ ፣ የወደቀች ሀገር
ሰማህ ወይ ሲነገር?
።።።።።
እኔማ ይኸውልህ ፣ የለም የማልሰማው
የለም የማላየው ፣ በቀን በጨለማው።
እንደውም ሰሞኑን
ኢቲቪ ምንላት ፣ ያንተ የውሸት በር
ባየር ሰአቷ ላይ ፣ እውነት ስትናገር
እውነት ይዛ ስትበር
አየናት እያሉ
ሲነግረኝ ሰው ሁሉ
"ካላየሁ አላምንም !" ፣ በማለት ሞግቼ
ወደ ቤት ገብቼ
ቲቪዬን ብከፍታት
ጧ ብላ ፈነዳች
እውነት መናገሯን ፣ ማመን ስላቃታት ።
ፈንድታ በጠፋች
የቲቪዬ እስክሪን ፣ ማታስተላልፈው
የከረመ አቧራ ፣ በላይዋ ያረፈው
ምን አፈላሰፈው?
የህይወት ታሪኳን ፣ ስትጠፋ እንዴት ፃፈው? !
"ዘላለም ከምኖር ፣ በውሸት ታስሬ
አንደኛውን ልጥፋ ፣ እውነት ተናግሬ
።።።።።
እንደምነህ ህወሀት ፣ እኔ አለሁ በጤና
ጤና እንደነሳኸኝ ፣ ጤና ይንሳህና
አለሁ ተደምሬ
አለሁ ተጣምሬ
የመለስን ራእይ ፣ በአብይ መንዝሬ
አለሁ የድጋፍ ሰልፍ
በፍቅር ስሰለፍ።
እንደውም እዚህ ጋር
የመለስን ራእይ ፣ ለማስፈፀም ብሎ
ጠብ የሚፈጥርብን ፣ ጠብመንጃ አንጠልጥሎ
የነበር ፌደራል ፣ ፍቅር የደመረው
የድጋፍ ሰልፍ ላይ ፣ ይዞት የነበረው
ሚያሰክር መፈክር
"ፍቅር ያሸንፋል
የመለስ ራእይ ፣ ገና ይንሻፈፋል!"
ሚል ፅሁፍ ነበረው
መለኮት ነው ሀይሉ
ጠብመንጃ ይጥላል ፣ ፍቅር የደመረው ።
።።።።።።
የሆነው ሆነና ፣ እንደምነህ ህውሀት
የመአቶች መአት
ከምፅአት ቀድመህ የመጣህ ምፅአት
በመለስ ራእይ
ራእይ የሌለው ፣ ትውልድ የፈለፈልክ
የወንዶች ሀገር ላይ ፣ ወንዶችን ያመከንክ
ግፍና ጭካኔህ ፣ የሚልቅ ከሰይጣን
የሚጫወትብህ ፣ ጥጋብና ቁንጣን
ተርበናል ስንል ፣ ጀሶ ምታነኩር
ባንዲራ ጨርቅ ነው ፣ ብለህ ምትደሰኩር
ኢሳያስ አፎርቄን
እንደጭራቅ ስለህ ፣ ባሳየኸን መድረክ
አየህ ወይ ሰው ሆኖ ፣ ለፍቅር ሲማረክ
ሰማህ ወይ ስለሱ ፣ በፍቅር ሲተረክ
አየኸው ወይ ቤቱን
አየኸው ወይ ሀብቱን ፣
አየኽ ወይ ስለሱ ፣
ኑሮው ማንነቱን ፣ እየመሰከረ
ህዝቡን እና ሀገሩን እንዳልመዘበረ
ንጉስ ሆኖ ሳለ ፣ ህዝብ ሆኖ እንደኖረ
አየህ ወይ ስለሱ?
እንደውም እንደውም
እኔን ከዚህ ቀደም
በሰደፍ ቀጥቅጦ ፣ ያረገኝ ደም በደም
የሻብያ መንግስት
ተላላኪ ብሎ ፣ ጥርሴን ያረገፈው
የሆነ አጋዚ ፣ በቀደም ባለፈው
የህወሀት መንግስት
ተላላኪ ብሎ ፣ ነገር ሲፈልገኝ
ጥርሴን ቀድሞ አርግፎት ፣ በድዴ አስፈገገኝ።
።።።።
የሆነው ሆነና
እንደምነህ ህውሀት ፣ እኔ አለሁ በደህና
በአስመራ መንገድ ፣ በሸገር ጎዳና
ፍቅር እየመራኝ
እያልሁ አሸወይና ፣ እያልሁ በሸነና
አለሁ ተስፋ አዝዬ
ባንዲራ ደም እንጂ ፣ ጨርቅ አይደለም ብዬ
አለሁኝ።

Adress

Stockholm

Öppettider

Måndag 09:00 - 17:00
Tisdag 09:00 - 17:00
Onsdag 09:00 - 17:00
Torsdag 09:00 - 17:00
Fredag 09:00 - 17:00

Aviseringar

Var den första att veta och låt oss skicka ett mail när የግጥም አለም postar nyheter och kampanjer. Din e-postadress kommer inte att användas för något annat ändamål, och du kan när som helst avbryta prenumerationen.

Dela