02/10/2025
የክልሉ ሙያ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት ምቹ የስራ አከባቢን ለመፍጠር ያከናወናውን የቢሮ እድሳት እና ማስፋፊያ አጠናቆ አስመርቋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የፌደራል እና የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት (መስከረም 22/2018) ዓ.ም
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) እንደገለፁት የክልሉ ሙያ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት የተቋቋመበትን ዋና አላማ ለማሳካት እያከናወናቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በቂ እውቀት ያለውን ዜጋ ለመፍጠር እንዲቻል ተቋማቱን ማጠናከር እና ማስፋት ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ተቋማቶች ተሞክሮውን በመውሰድ ቢሮዎቻቸውን ለስራ ምቹ እንዲያደርጉ እና ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት ፈጣን እና ጥራት ያለው እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ ስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰሎሞን ሶካ እንዳሉት ሀገራችን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምራ በመጨረስ እና አዳዲስ ስራዎችን በመጀመር የህዝቦችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየተጋች ነው ብለዋል።
የክልሉ ሙያ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት ከዚህ በፊት በነበረው ምልከታ ተቋሙ የቢሮ እጥረት ያለበት እና ፅዱ አለመሆኑን ከተመለከትን በኋላ በፍጥነት መታደስ እና ማስፋፊያ ሊደረግበት እንደሚገባ ከተቋሙ ጋር በማቀድ በአንድ አመት ውስጥ ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
ትውልድን የሚቀርፁ እና ክህሎት እና እውቀት ያለው የሰው ሀብትን የሚያበቁ ተቋማት ምቹ ቢሮዎች እና ፅዱ አካባቢ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የክልሉ ሙያ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት በሚመጥነው መልኩ መታደሱ የሚበረታታ እና በቀጣይም ይህ ተግባር በሌሎች ተቋማትም መጠናከር ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሯች ባያክ በበኩላቸው ቢሮው እና ተጠሪ ተቋማቱ ጥራት ያለው አሰራር እንዲኖራቸው ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።
በተለይም ክህሎት መር ተግባራትን ከማከናወን ጎን ለጎን ተቋማትን የመገንባት እና የማሻሻል ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ዳይሬክተር አቶ ኡቶንግ ኡጁሉ እንደገለፁት ተቋሙ የተጣለበትን ሀላፊነት በጥራት እና ፍጥነት ማከናወን እንዲችል ምቹ አካባቢን መፍጠሩ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የቢሮ እጥረት ያለ በመሆኑ እና አካባቢው ፅዱ ባለመሆኑ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እንደነበር ገልፀዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር እንዲሁም ሀብት በማሰባሰብ ተቋሙን የማደስ እና ማስዋብ ስራ ለመስራት መቻሉን አስረድተዋል።