03/06/2026
በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሴ ዳልኬ (ዶ/ር) በደቡብ ኮሪያ ሴዑል ከተማ የሚገኘውን የኮሎን ( KOLON) ጨርቃጨርቅና አልባሳት ካምፓኒ ጎበኙ፡፡(ግንቦት 26 ቀን 2018)
በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሴ ዳልኬ (ዶ/ር) በደቡብ ኮሪያ ሴዑል ከተማ በሚገኘው የኮሎን ( KOLON) ጨርቃጨርቅና አልባሳት ካምፓኒ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ከዋና ሥራ አስፈፃሚው ሚን-ቴ ኪም(Min-Tae Kim) እና ከሥራ ባለደረቦቻቸው ጋር ፍሪያማ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የኮሎን ( KOLON) ጨርቃጨርቅና አልባሳት ካምፓኒ የቢሮ ሰራተኛ የሆኑት ካንት ህቱን(Khant Htun) የካምፓኒውን ታሪካዊ አመሰራረት፣ዓላማ፣ ተልዕኮ እና ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሴ ዳልኬ (ዶ/ር) አገራችን በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የምትገኝ ወደ አፍሪካ መግቢያ በር የሆነች፣ ከተለያዩ ዓለማት ጋር የተሳሰረች እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የአየር መንገድ ትራንፖርት እና እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ ያላት፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብና 70% አምራች የሰው ኃይል ያላት፣ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነች፣ ጠንካራ የመንግስት ድጋፍ ያለባት፣ የንግድ ሊበራላይዜሽን ያደረገች፣ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ምቹ የኢንቨስትመንት መልክዓ ምድር ለመፍጠር የቢዝነስ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ዘርግታ የምትገኝ አገር መሆኗን በመጥቀስ የኮሎን ( KOLON) ጨርቃጨርቅና አልባሳት ካምፓኒ በአገራችን ጨርቃጨርቅና አልባሳት የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማራ ጠይቀዋል፡፡
በመጨረሻም የኮሎን ( KOLON) ጨርቃጨርቅና አልባሳት ካምፓኒ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በቀጣይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማጥናት ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል፡፡