01/06/2026
የምርጫ ሂደቱ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ጉዞ የሚያጠናክርና የሕዝብ ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ የሚገለጽበት ነው፦አቶ ይግለጡ አብዛ
ግንቦት 24/2018(ውልቂጤ)
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ይግለጡ አብዛ እንዲሁም የእዣ ቁጥር 2 ምርጫ ክልል የፓርቲው የክልል ምክር ቤት እጩ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ሕዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ በነጻ ፈቃዱ እየመረጠ ሲሆን፣ የምርጫው ሂደቱም በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
"ዛሬ አለመምረጥ ማለት ወደፊት በራስ ምርጫ ባልተወሰነ አስተዳደር መመራት ማለት ነው" ያሉት አቶ ይግለጡ፣ ሁሉም ዜጋ የዴሞክራሲ ግንባታን ለማጠናከር በምርጫው ላይ በንቃት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ እና በእዣ ቁጥር 2 ምርጫ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በምርጫ ጣቢያቸው በመገኘት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ወ/ሮ መሰረት በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ሕዝቡ በቀጣይ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት በነጻነትና በዲሞክራሲያዊ ሂደት እየመረጠ ሲሆን፣ በምርጫው የሚታየው ተሳትፎም የማህበረሰቡ የዲሞክራሲ ግንዛቤና ንቃተ ህሊና እያደገ መምጣቱን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።
በምሁር አክሊል ወረዳ የእዣ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ ገብረመድህን ቤዛ በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 63 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከጥዋቱ 12 ሰአት ጀምሮ ድምጽ እየተሰጠ መሆኑ ተናግሯል።
የምርጫ ሂደቱም ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው አሰራር መሰረት ፍጹም ሰላማዊ፣ድሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል።