29/02/2024
HPV የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከየካቲት 25 - 29/2016 ዓ.ም በልዩ መልኩ እድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች በዘመቻ ይሰጣል።
____
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም ላይ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች 70 ዓመት ሳይሞላቸው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ህይወታቸው ያጣሉ።
በሃገራችን ኢትዮጵያ በዓመት በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት 5ሺህ ሰዎች ህይወታቸው የሚያልፍ ሲሆን እድሚያቸው ከ14 ዓመት በላይ ከሆኑት ሴቶች ከአምስቱ 4 የሚሆኑት በህይወት ዘመናቸው ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
በማደግ ላይ በሚገኙ ሃገራት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን የገለፁት በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣አፍላ ወጣቶች እና ህጻናት መሪስራ አስፈፃሚ የክትባት ቡድን አማካሪ የሆኑት አቶ ተመስገን ለማ በሃገራችን ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ለህብረተሰባችን ከፍተኛ ስጋት የሆነው የማህጸን በር ካንሰር በገዳይነቱ በ2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ለቫይረሱ መፈጠር ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝ የጠቆሙት አቶ ተመስገን ለሚዲያዎች፣ለጤና መረጃና ምክክር አገልግሎት ባለሙያዎች እንዲሁም ጤና ላይ ለሚሰሩ የተመረጡ ማህበራት ባለሙያዎች ባስተላለፉት መልዕክት የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከየካቲት 25 - 29 በልዩ መልኩ እድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች ብቻ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጥ የነበረውን የማህጸን በር ካንሰር ክትባት አንድ ጊዜ አንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አማካሪው ትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫና የቅድመ መከላካል ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል ።