13/05/2026
በወረዳው ባቶ ቃልቦ ቀበሌ አጠቃላይ የህዝብ ውይይት መድረክ ተካሄደ
ግንቦት 05/2018 ዓ.ም. (የማ/ወ/መ/ኮ)፦
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ ባቶ ቃልቦ ቀበሌ፣ መልካም አስተዳደርን፣ የልማት ጉዳዮችን እና ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረገ ሰፊ የህዝብ ውይይት መድረክ ከቀበሌው ማህበረሰብ ጋር ተካሂዷል።
በመድረኩ የዳውሮ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ህብረት ስራ መመሪያ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር በተላ በየነ፣ የማረቃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክልሉ አስፋው፣ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ እና የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስናቀ አካሉ፣ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቀስስ ባንተይዋሉ ፎላ፣ የቀበሌ ደጋፊ አመራር እንዲሁም ከወጣት እስከ አዋቂ ያለው በስፋት ተገኝተዋል።
በቦታው የተገኙት የማረቃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክልሉ አስፋው በንግግራቸው፣ መንግሥት የህብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመፍታት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በብልፅግና መንግሥት ዘመን በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን በማንሳት፣ ቀጣይም የህዝቡን ጥያቄዎች በትኩረት በመፍታት የብልፅግና ጉዞውን ለማሳካት መንግሥት እና ህዝብ በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የዳውሮ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ህብረት ስራ መመሪያ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር በተላ በየነ በበኩላቸው፣ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ዳውሮ በልማት እየተቀየረች መሆኗን ጠቅሰው፣ ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች በውይይት እየተፈቱ እንደሚሄዱ ገልጸዋል። ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶችም ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ እንደሚሰራ አስረድተዋል። ብልፅግና ስራውን እየሰራ ችግሮቹን እየፈታ እንደምሄድ አጠንክረው ተናግረዋል።
የማረቃ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቀስስ ባንተይዋሉ ፎላ በበኩላቸው፣ ትምህርት የማንኛውም ማህበረሰብ እድገት መሠረት መሆኑን ገልጸው፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪ እና ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በውይይቱ የተሳተፈው ማህበረሰብ በዋናነት በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ማነቆ ሆነው የቆዩ የመሠረተ ልማት ጉዳዮችን አንስቷል፤ በተጨማሪም የትምህርት ጥራት ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ጥያቄ አቅርቧል። በአካባቢው ያሉ ልዩ ልዩ ችግሮች ተፈትተው ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥም አሳስበዋል።
ከማህበረሰቡ ለቀረቡ ጥያቄዎች በቦታው የተገኙ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በቂ ማብራሪያ እና ምላሽ በመስጠት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ምልክት የስንዴ ነዶ መሆኑን ለህዝቡ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርተው፣ ህዝቡም የስንዴ ነዶን በመምረጥ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት ከመንግሥት ጋር በአንድነት እንደሚሰሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። በተጨማሪም የአካባቢው ማህበረሰብ ከመንግሥት ጎን በመቆም በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንደሚሳተፍ ቃል ገብቷል።
ዘገባው፡የማረቃ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።