03/01/2026
የመንግስት ሰራተኞች ከቤተሰባቸው በውርስ እና በስጦታ መሬት ማግኘት እንዲችሉ የፈቀደው አዲሱ አዋጅ !
ከሰሞኑን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አዲስ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ይፋ አድርጓል።
በአዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ዙሪያ በተሰጠ ማብራሪያ " አዲሱ አዋጅ ከዚህ በፊት ሲነሱ የነበሩ የዘርፉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አማራጮችን አካቷል " ተብሏል።
እስካሁን የነበረው አዋጅ ባህላዊ የመሬት አያያዝ እና የግጭት አፈታት ስርአቶችን ግምት ውስጥ ማስገባትና እዉቅና መስጠት ላይ ችግሮች የነበሩበት እንደሆነ በአሁኑ አዋጅ ግን ሽምግልና አንዱ የግጭትና አለመግባባትን የሚፈታበት አማራጭ ሁኖ እንዲካተት መደረጉ ተገልጿል።
ይህ አዋጅ የመንግስት ሰራተኞች ከቤተሰባቸው በውርስ እና በስጦታ መሬት ማግኘት እንዲችሉ ፈቅዷል።
አዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዟል ?
- በአዲሱ አዋጅ ካሁን በፊት ተግባራዊ በተደረጉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ህጎች ያልነበሩና የገጠር መሬት ባለይዞታዎችን መብትና ጥቅም ለማስፋት በግል ይዞታ ላይ የለማን የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥ እና ማስተላለፍ እንዲችሉ ይፈቅዳል።
- የገጠር መሬት ባለይዞታዎች መሬታቸውን በስጦታም ይሁን በውርስ ማስተላለፍ የሚችሉት በገጠር መሬት አዋጅ ለተፈቀደላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ነበር፡፡ ይህ ከቤተሰቦቻቸዉ መሬት የማግኘት መብት ሊኖራቸዉ የሚገቡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም ገድቦ ቆይቷል። በአሁኑ አዋጅ የመንግስት ሰራተኞች ከቤተሰባቸው በዉርስና በስጦታ መሬት ማግኘት እንዲችሉ ይፈቅዳል።
- በአዲሱ አዋጅ የገጠር መሬት ባለይዞታዎች የይዞታ መብትን ለፈለጉት ሰው በስጦታ፣ በውርስ ማስተላለፍ መብትን ለማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ይፈቅዳል።
- የገጠር መሬት ይዞታን ለብድር ዋስትና ማስያዣነት በመጠቀም የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበትን ድንጋጌ አካቷል። ይህም የክልሉን አርሶ አደር የብድር አቅርቦት ችግር መፍትሄ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
- በአዲሱ አዋጅ በአስገዳጅ ሁኔታ የመሬት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱ ዲጂታላይዝ መሆን እንዳለበት በግልፅ ተመላክቷል፡፡
- ለሴቶች፤ ለህፃናት፤ ከቀያቸዉ በጊዜያዊነት ለለቀቁ፤ በህግ ጥላ ስር ያሉ፣ ለህሙማን፤ ለአረጋዊያንና…ወዘተ ጉዳዩን ልዩ ትኩረት በመሰጠት የህግ ከለላና መብት ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ ከዚህ በፊት በነበሩ ህጎች ላይ ተካቶ ተፈጻሚ ቢሆንም በልዩ ትኩረት የተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ጥበቃ ትኩረት እና ባለቤት በመስጠትም በኩል ትኩረት ተሰጥቶታል።
(በአዲሱ አዋጅ ከተካተቱ ነጥቦች ውስጥ በዚህ ክፍል የቀረበው በከፊል ነው)
via ቲክቫህ ኢትዮጵያ