07/09/2026
በበዓላት ወቅት የሚደርሱ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ እየተሰራ እንደሆነ ተገለጸ
ወላይታ ሶዶ ጳግሜ 02/2018 ዓ/ም (ደኢፖኮ)
በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘዉን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የትራፊክ ዲቪዥኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በቀጣይ ቀናት የሚከበረዉን የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ የመንገድ ትራፊክ አደጋ እንዳይደርስ ሁሉም በኃላፊነት እንዲወጡ የትራፊክ አደጋ ክትትልና ቁጥጥር ዲቪዥን ኃላፊ ም/ኢ/ር ዳንኤል በደቻ ጠይቀዋል።
አሽከርካሪዎች ይህንን ወቅት ከፍተኛ ኃላፊነት በመዉሰድና በተፈቀደዉ ፍጥነት በማሽከርከር አጠቃላይ የትራፊክ መመሪያና ደንብን አክብረዉ እንዲያሽከረክሩ አደራ ብለዋል።
በዓሉን አስመልክቶ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ለግብይት ወደ ከተማ ስለሚመጡ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ባለመዘናጋት በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ ኃላፊዉ አሳስበዋል።
አሽከርካሪዎች በመጠጥና በአደንዛዥ ዕጽ ተጠቅመዉ እንዳያሽከረክሩ የተጠየቀ ሲሆን ይህንና መሠል ድርጊቶችን ጥንቃቄ በማድረግ ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ተጠይቋል።
እግረኞች የዘዉትር ተግባር የሆነዉን ግራ መስመርን ብቻ በመጠቀም መንቀሳቀስና ለመሻገር ሲፈልጉ ለዚህ ተብሎ በተሰራዉ ዜብራን ብቻ በመጠቀም አደጋ እንዳይደረስ የበኩላቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ ይገባል።
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር የአንድነት እና ከትራፊክ አደጋ የጸዳ በዓል እንዲሆን ኢንስፔክተር ዳንኤል በደቻ መልካም ምኞታቸዉን ገልጸዋል።
ዘገባው የጌዴኦ ዞን ፖሊስ መምሪያ ነው።