05/11/2025
ፍትኃዊነት ላይ የተመሠረተ ግብር እና ታክስ ለመሰብሰብ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን ማዘመን ይገባል ሲሉ የቤንች ሸኮ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ትዕዛዙ ተናገሩ ።
የገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017 መሠረት በማድረግ ለደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ አቀራረብ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በሚዛን- አማን ከተማ ተካሂዷል ።
የገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017 መሠረት በማድረግ ለደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዬች የሂሳብ መዝገብ አቀራረብ ላይ የተደረገ ውይይት በሚዛን- አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ መስፍን ጉብላ መንግሥት በውስጥ ገቢ ሙሉ በሙሉ ወጪን ለመሸፈን እየሠራ እንዳለ ጠቁመው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብር ሥርዓቱን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ትዕዛዙ ህጋዊነትን ጠብቀው የሚሠሩ ለህዝብ እና ለመንግሥት እንዲሁም ለራሳቸው ታማኝ የሆኑ ሕጋዊ ግብር ከፋዮች እንዲበረታቱ የገቢ ግብር አዋጁ ይረዳል ሲሉ ገልፀዋል።
ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ጋር የተለያዩ የውይይትና የምክክር፤ እንዲሁም የእውቅና መድረኮችን በመፍጠር ዘመናዊ የግብር ሥርዓቶችን በመተግበር በሁሉም የገቢ አማራጮች የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሠራ እንደ ሚገኝ ተገልጿል።
የወጡ የታክስ ህጎችን በማሥከበር እና የደረሰኝ ቁጥጥሩን ማጠናከር የህግ ተጠያቂነት ባለው መልኩ ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ለመቀነስ የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚዛን- አማን ከተማ ምክትል ከንቲባና የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ታገል ወንድሙ ጠቁመዋል።
ግብር ከፋዩ የገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017 በተለይም ደግሞ የአዋጁን አንቀፅ 87 በጥልቀት እንዲረዱት በማስቻል የሚጠበቅባቸውን የመንግሥት የግብር ግዴታን በወቅቱ እንዲፈፅሙ በማስቻል አቅማቸውን ሊፈትኑ ከሚችሉ ከፍተኛ የግብር ወለድ እና ቅጣት እንዲተርፉ ያግዛቸዋል ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነጋዴዎች መካከል አቶ አበባው ተክሉ ፣ አቶ ኡመር ሙስጠፋ እና አቶ ግርማ ወንድሙ በበኩላቸው መንግሥት ሕጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎችን በአሥራ ሥርዓት ሕጋዊ መስመር እንዲያስገባ አጭበርባሪዎችን ተከታትሎ ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።