22/05/2026
"የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዓለም የደረሰበት የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ አቅሙን አሳድጓል" የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ)፦የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዓለም የደረሰበት የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ አቅሙን አሳድጓል ያሉት 117ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ ቀንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የተካሄደ ባለው በፓናል ውይይት ላይ ነው።
117ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ ቀን በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።
በዚህ ወቅት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደምበላሽ ገ/ሚካኤል፤ የሀገር ድምበር ተከብሮ ዜጎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ፖሊስ ትልቁን ሚና እየተወጣ ነው።
ተቋሙ በባሕላዊ አስተሳበብ የሚመላለስ አይደለም ያሉት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከአፍሪካ ብቁና አስተማማኝ ቁመና የገነባ ተቋም ሆኗል ብለዋል።
በሰው ኃብት ፣ በቴክኖሎጂ እና በተቋማዊ አደረጃጀት የሄደበት ርቀት ከለውጡ ወዲህ ከታዩ የሪፎርም ትግበራ ውጤቶች ተቋሙን አንዱ ማሳያ ያደርገዋል ሲሉም አንስተዋል።
በወንጀል መከላከል እና ተያያዥ ፖሊሳዊ ትግበራዎች የዲጂታል ሥርዓቶችን ወደ ሥራ በማስገባት የፖሊሳዊ ሥራዎችን ማዘመን መቻሉን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጀነራል ስማርት ፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ ዲጂታል ፎረንሲክ ላባራቶሪዎችን አደራጅቷል ነው ያሉት።
የዲጂታል ማዘዣ ማዕከል ( CCC,) የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ( EFP app,) የድሮን ኃይል እና digital communications ወደ ትግበራው ከገቡት መካከል ናቸው።
በወንጀል ምርመራ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ሽብርተኝነት ፣ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።
ዛሬ የሳይበር ወንጀሎችን ፣ የፋይናንስ ማጭበርበሮችን እና የተወሳሰቡ ዲጂታል ዐሻራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመተንተንና በማስረጃነት በማቅረብ ረገድ ተቋሙ በአፍሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ችሏል።
በዚህም የወንጀለኞችን መደበቂያ በማጥበቡ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ጥቂት ያደጉ ሀገራት የታጠቁትን ትጥቅ በመታጠቅ ከዘመኑ ጋር ዕኩል እየተራመደ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ይህም በቴክኖሎጂ ሥርዓት የታገዘ የወንጀል መከላከል አቅምን የሚያሳድግለት ከመሆኑም በላይ የትኛውንም የፀጥታ ስጋት ለመቀልበስ የሚያስችለው ነው።
አሁናዊ ተቋማዊ ቁመናው ከለውጡ ማግስት ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የመጣ መሆኑን አንስተው፤ የአመራር ቁርጠኝነት እና የአባላቱ ትጋት ከፍተኛ ሚና እንደነበረውም አስገንዝበዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ፖሊሳዊ አመራሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።