19/03/2021
የመንግስት ተቋማትን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ለወረዳ የመንግስት ተቋማት የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ባለሙያዎች የማነቃቂያ ስልጠና ለ2 ተከታታይ ቀናት ሰሞኑን በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት አማካኝነት ተሰጠ፡-
በጽ/ቤቱ የልማት እቅድ ክትትልና ግምገማ የስራ ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ውብአዝመራ ወርቁ እንዳሉት የዚህ ስልጠና ዋነኛ አላማ የመንግስት ተቋማትን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የመረጃ ልውወጥ እና የሪፖርት ግንኙነትን በማጠናከር የዘርፉን ባለሙያዎች ብቃትና ክህሎት በስልጠና ማሳደግ ታስቦ ነው ብለዋል፡፡
የስራ ቡድን መሪዋ ከዚሁ ጋር አያይዘው እንዳሉት የተቋማትን የመረጃ አሰጣጥ ስርአት በማዘመን ተግባራትን በእቅድ መሰረት አካተው እንዲሰሩና የስራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ወቅቱን ጠብቀው ለሚመለከተው አካል እንዲያደርሱና የተሻለ አሰራርን ለማምጣት ይህ ስልጠና ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የመንግስት ተቋማት የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ባለሙያዎች በበኩላቸው ስልጠናው መሰጠቱ ለስራችን ውጤታማነት ግብአት ሊሆን ስለሚችል እና በተቋማት ላይ የሚያጋጥሙ የአሰራር ክፍተቶችን ለማስተካከል እና ለማረም አጋዥ ስለሆነ በቀጣይነት ስልጠናው ወቅቱን ጠብቆ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ሰልጣኞች አክለውም እንዳሉት ይህ ስልጠና በበጀት አመቱ መጀመሪያ ላይ መሰጠት ቢችል ለስራችን የበለጠ አቅም ይሠጠናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የሚዲያ ልማትና አብዝሃነት ቡድን
መጋቢት 2013 ዓ.ም