17/04/2025
"ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ስጦታ ናቸው"
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ በታይም መጽሔት የዓመቱ የዓለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተካተቱ።
ዶ/ር ላሪ ብሪሊያንት፤"ዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ስጦታ ናቸው" ሲሉ አሞካሽቷቸዋል፡፡
ታይም መጽሔት በየዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የሚላቸውን የ100 ሰዎች ስም ዝርዝር ይዞ የሚወጣ ሲሆን፤ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የአገራትና የድርጅት መሪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አርቲስቶችና ስፖርተኞች እንዲሁም ፀሐፊያን ይካተቱበታል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በታይም መጽሔት የ2025 ተጽእኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነታቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ሰዎች በእኩልነት የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ባበረከቱት አመራር ታይም መጽሔት በ100 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ አካትቷቸው ነበር።
ዶ/ር ቴዎድሮስ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "በዝርዝሩ ውስጥ መካተቴ በምሠራበት የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ ለሚሠሩ ባልደረቦቼም እውቅና ነው" ብለዋል።
በመጽሔቱ ላይ ስለ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሃሳባቸውን ያጋሩት ዶ/ር ላሪ ብሪሊያንት በበኩላቸው፤ "ዶ/ር ቴዎድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ከሆኑ በኋላ የዓለማችንን የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀይረውታል" ብለዋል።
የፈንጣጣ በሽታ ከዓለም ላይ አንዲጠፋ ቁልፍ አስተዋጽኦ ያደረጉት ዶ/ር ላሪ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ይህንን ማድረግ የቻሉት "በበሳል አመራርና ሳይንሳዊ በሆነ የውሳኔ አሰጣጥ" በመታገዘ ነው ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ "ለዓለም ጤና ስጦታ ናቸው" ያሉት ዶ/ር ላሪ፤ "የዓለም ጤና ድርጅትን ለመጀመሪያው ጊዜ የመሩ አፍሪካዊ መሪ፣ የመጀመርያው ሕክምና ያላጠኑ መሪ፣ ሚሊዮኖችን የገደለውን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የተጋፈጡ የመጀመሪያው መሪ፣ አሁን ደግሞ አሜሪካ ከመሠረተችው ተቋም ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ስትወጣ የተጋፈጡ መሪ ናቸው" ሲሉ በመጽሔቱ ላይ ጽፈዋል።
(ቢቢሲ)