05/06/2026
ግንቦት 28/2018 ዓ/ም
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት ወቅታዊና መደበኛ ስራዎችን በመገምገም የበጀት አመቱ ቀሪ ስራዎች በሚቀጥሉት 20 ቀናት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ አስቀመጠ!!
፨፨፨፨፨///፨፨፨፨፨
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዲሁም የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ናስር ሀሰን የመስተዳደሩ ምክር ቤት አባላት በተገኙበት ወቅታዊና መደበኛ የንቅናቄ ስራዎች በወልቂጤ ከተማ ገምግመዋል።
ምክትል አስተዳዳሪው የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማት ስራዎች፣የገቢ ፣ የፋይዳ መታወቂያ ስርጭት፣የኢቲዮ ኮደርስ ስልጠና፣የንግድ፣የስራ እድል ፈጠራና የነዳጅ ስርጭት ሁኔታ የደረሱበት አፈፃፀም ገምግመው በቀጣይ 20 ቀናት ታቅደው መሰራት ባለባቸው ተግባራት ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
አቶ አበራ ወንድሙ እንደገለፁት የህብረተሰባችን የኑሮ ጫናን ለመቀነስ በገበያ ዋጋ ማረጋጋት ላይ የምንሰራው ስራ ልዩ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል::
በነዳጅ አቅርቦት ስጭትና ህገወጥነቶች ላይ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ውጤት እያስገኙ ቢሆንም አሁንም ቀሪ ስራዎች ስላሉ አቅዶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም ህገ ወጥ የነዳጅ ክምችት በሚያደርጉና በአላስፈላጊ መንገድ ነዳጅ እየሸጡ የሚገኙ አካላት ላይ ልዩ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት 20 ቀናት ያላሳካናቸው ቀሪ የአመቱ እቅዶቻችንን ሙሉ በሙሉ ልናሳካ ይገባል ያሉት አቶ አበራ በተለይም የገቢ ስራችን ያሉንን እድል ሁሉ ተጠቅመን ገቢን አሟጣን ልንሰበስብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በገቢ አሰባሰብ ላይ አፈፃፀማቸው ከዞን አማካይ በታች የሆኑ መዋቅሮች በሚቀጥሉት 20 ቀናት በልዩ ሁኔታ እቅዳቸውን ሊያሳኩ እንደሚገባም አፅንዎት ሰጥተዋል።
በዞኑ የተከለሰውን የገቢ እቅድ ጨምሮ እስካሁን ለመሰብሰብ ከታቀደው ከ83 በመቶ በላይ መሰብሰብ መቻሉን የጠቀሱት ምክትል አስተዳዳሪው እስከ ሰኔ 30 ድረስ ከ810 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መስራት ይገባል ብለዋል።
ካለ ፋይዳ መታወቂያ ምንም አገልግሎት ማግኘት የማይቻልበት ደረጃ እየደረስን እንደሆነ ልናውቅና ህዝቡንም ልናሳውቅ ይገባል ያሉት አቶ አበራ በተያዘው በጀት አመት 100% ለማሳካት መስራት እንደሚገባ በማመላከት አሁን ከደረስንበት አፈፃፀም አንፃር ሰፊ ውስንነት እንዳለ ጠቁመዋል
የከተማ ኮሪደር ልማት በአምስቱም ከተሞች በተጀመረው መልኩ ተጠናክሮ በፍጥነትና በጥራት ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የገጠር ኮሪደር በተመለከት ከሌማት ትሩፋትና ከፅዱ መንደር ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል በማለት
ሞዴል የገጠር መንደር መፍጠ ላይ ታዳጊ ማዘጋጃዎች ላይ ቦታ መርጠን ወደ ተግባር ልንገባ ይገባል።
ከስራ እድል ፈጠራ አንፃር ያሉ ስራዎች እድገት ቢያሳዩም በelmis ከመመዝገብ አንፃር ግን ያሉ ውስንነቶች እንዲታረሙና የተለዩ ስራ አጥ ዜጎችም ከአጋሮች ጋር በመሆን ወደ ስራ የሚገቡበት መንገድ ለማመቻቸት እየተደረገ ያለው ጥረት መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የነገይቱን ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ተፎካካሪ ለማድረግ ያለመና ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የተለመ ፕሮግራም እንደሆነ በመረዳት ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ስልጠናው ከመስጠት ባሻገር ስልጠናውን ተጠቅመው ገቢ ማግኘትና ፈጠራ የጀመሩ ልጆችን ማበራከትና ለሚዲያ ማቅረብ ይገባል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ናስር ሀሰን በበኩላቸው የተቀመጡት አቅጣጫዎች በ20 ቀናት ውስጥ መፈፀም እንደሚገባና አመራሩ ሌሎች ትላልቅ ተግባራት በመራበት አግባብ ስራዎቹን እንዲመራ አሳስበዋል።
ወቅታዊ የግብርና የትምህርትና የጤና ስራዎችም አቀናጅቶ መምራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መረጃው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ነው።