21/05/2026
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት የ10 ወራት የገቢ አፈጻጸም ከጽ/ቤቱ ባለሙያዎች ጋር ገመገመ
ሆሳዕና፤ ሚያዝያ 2018 ዓ.ም
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የጽ/ቤቱ ማናጅመንት አባላት፣ የቡድን መሪዎች እና መላው ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን፣ መድረኩን የሆሳዕና ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አውላቸው ዮሐንስ መርተውታል።
በመድረኩ መጀመሪያ ላይ የጽ/ቤቱ የልማት ዕቅድ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ኤልያስ የ10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርቱም የከተማዋን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦት በመፍጠር ረገድ የታዩ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በሰፊው ተገምግመዋል።
📊 የገቢ አፈጻጸም
በአጠቃላይ በ10 ወራት ውስጥ 1 ቢሊዮን 9 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል። ይህም ከባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት የታየበት መሆኑ ተመላክቷል።
የተሰበሰበው ገቢ ዝርዝር ስብጥር፦
• መደበኛ ገቢ: ከ1.35ቢሊዮን ብር በላይ
• ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ: ከ541 ሚሊዮን ብር በላይ
• ከውዝፍ ዕዳ: ከ22.5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።
⚖️ ሕግን ከማስከበርና ታክስ ኦዲት አኳያ የተከናወኑ ሥራዎች
የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ከመቀጠል አኳያ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ፦
1. የደረሰኝ ቁጥጥር: ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ በተያዙ 118 ግብር ከፋዮች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ 11 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል።
2. የታክስ ኦዲት ምርመራ:133 ፋይሎችን በታክስ ኦዲት በመመርመር 55.3 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ግኝት ማስመዝገብ ተችሏል።
⚠️ ያጋጠሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶች
በግምገማው ወቅት የታክስ ማጭበርበር፣ ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ እና የሊዝ መሬት አቅርቦት ማነስ እንደ ዋና ማነቆዎች የተነሱ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በቀጣይ የሚከተሉት የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፦
• 📌 ያለ ደረሰኝ ግብይት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የጀመረውን ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል።
• 📌 ውዝፍ ዕዳ ባለባቸው ላይ የንብረትና የባንክ ዕገዳ ሥራዎችን በቁርጠኝነት መተግበር።
• 📌 የሊዝ መሬት አቅርቦትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማመቻቸት ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን ይበልጥ ማሳደግ።
🎯 በመጨረሻም የ/ቤቱ ማናጅመንትና ቡድን መሪዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ የተመዘገበው ውጤት የሚበረታታ መሆኑ ተገልጿል።
"የከተማችንን ወጪ በራስ ገቢ ለመሸፈን" የሚለውን ታላቅ መርህ ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ባለሙያዎችና የከተማዋ ግብር ከፋዮች በቅንጅትና በታማኝነት እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት