ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ

  • Home
  • Ethiopia
  • Hossana
  • ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ

ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ " ሁሉም ሰው የሚታወቅባት ኢትዮጵያ ! Ethiopia, Where Everyone Recognized !" አድራሻ፡-ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ፅ/ቤት

01/06/2026
"የጥሞና ጊዜ" ከነገ ጀምሮ መሆኑን ያውቃሉ?!ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ያሉት 4ቱ የመጨረሻ ቀናት የጥሞና ወቅት ይባላሉ።የጥሞና ወቅት በቅድመ ምርጫ ዑደት ውስጥ የሚገኝ ጊዜ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ...
27/05/2026

"የጥሞና ጊዜ" ከነገ ጀምሮ መሆኑን ያውቃሉ?!

ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ያሉት 4ቱ የመጨረሻ ቀናት የጥሞና ወቅት ይባላሉ።

የጥሞና ወቅት በቅድመ ምርጫ ዑደት ውስጥ የሚገኝ ጊዜ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የምርጫ ዑደት መመሪያ መሠረት ምርጫ ከመደረጉ በፊት ያሉትን አራት ቀናት ያካትታል።

በጥሞና ወቅት ታዲያ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ሊተገብሯቸው የሚገቡ ኃላፊነቶች አሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፡-

1. የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችና ደጋፊዎቻቸው ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የሚያካሂዱት የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ድምፅ መስጠት ከመጀመሩ ከአራት ቀን በፊት መጠናቀቅ አለበት።

2. የፓለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው አራት ቀን ሲቀረው ማንኛውንም አይነት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይፈቀድላቸውም፡፡ (በኢንተርኔት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በግንባር፣ ቤት ለቤት፣ በአደባባይ ፣ በአዳራሽ ስብሰባ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ ማከናወን በጥብቅ የተከለከለ ነው)
3. የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ቃለ-መጠይቆችን ማድረግ አይፈቀድላቸውም።

4. የምረጫ ቦርዱ የሚያወጣቸውንም መመሪያዎች ሊፈጽሙ ይገባል።

ለመገናኛ ብዙኃን ተቋማት
1. የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በጥሞና ወቅት ማንኛውንም ምርጫ ተኮር እንቅስቃሴዎችን ማሰራጨት አይፈቀድላቸውም።በተጨማሪም የፓለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችን አግኝተው ቃለ-መጠይቆችን መሥራት አይፈቀድላቸውም።

2. የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከምርጫ ቦርድ የሚወጡ መረጃዎችን የማስተጋባት ኃላፊነት ሲኖርባቸው ከዚህ ውጪ በመመሪያዎች ላይ ያልተደነገጉ ተግባራትን እንዲፈጽሙ አይፈቀድላቸውም።

#ምርጫ #ጥሞና #ፓርቲዎች #ሚዲያ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ55ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ወሳኝ ረቂቅ አዋጆች፣ ፖሊሲዎችና ደንቦች ላይ ተወያይቶ ሙሉ ድምፅ ውሳኔዎችን አሳለፈ*****************************1...
26/05/2026

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ55ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ወሳኝ ረቂቅ አዋጆች፣ ፖሊሲዎችና ደንቦች ላይ ተወያይቶ ሙሉ ድምፅ ውሳኔዎችን አሳለፈ
*****************************

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው በሁለት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለአርብቶ አደር ምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከአፍሪካ ልማት ባንክ የአርባ ስድስት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ (46,300,000) የአሜሪካን ዶላር ብድር ስምምነት ነው፡፡

ሁለተኛው ለስድስተኛ ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር የአንድ መቶ አርባ ስድስት ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ (146,100,000) ኤስ ዲ አር ብድር ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሁለቱም የብድር ስምምነቶች ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ወጥቶ ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም ባለፉት አመታት በሀገራችን በርካታ የኢኮኖሚ ለውጦች የተደረጉ በመሆኑ የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ከዘመናዊ ዓለም አቀፍ ልምዶች ጋር ለማጣጣም፤ የታክስ አለመግባባቶችን በፍትሐዊነት፣ በሰላማዊ መንገድና በቅልጥፍና ለመፍታትና የተጠያቂነትና ግልጸኝነት አሰራር ለማስፈንና የታክስ ሕጎችን በተጠናከረ መልኩ ለማስፈጸም እንዲያስችል ተደርጎ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የግብርና ዘርፍን ከተለምዶአዊ አሰራር ወደ ቢዝነስ መር ሥርዓት ለማሸጋር፤ አነስተኛ አምራቾችን የገበያ የመደራደር አቅም ለማሳደግ፣ የእሴት ጭማሪና የኢንዱስትሪ ግብዓት ትስስርን ለመፍጠር፤ የተሻለ አቅም ያላቸው ወደ መካከለኛ አልሚነት የሚደርጉትን ሽግግር በሕግ ለመደገፍ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የካርበን ገበያ ስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የካርበን ግብይት አሰራሮችንና ሂደቶችን በግልፅ ለመደንገግ፣ በካርቦን ፕሮጀክት አካባቢ በሚኖረው ማህበረሰብና አካባቢው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አሰራሮችን ለመዘርጋት፤ ከካርበን ንግድ የሚገኘው ገቢ በመንግስት፣ በአልሚዎች፣ በአካባቢው ማህበረሰብ እና በባለድርሻ አካላት መካከል በፍትሃዊነት የሚከፋፈልበትን አሰራር ለመዘርጋት እና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ውሎችና የገባቻቸውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ቃል ኪዳኖች ከሌሎች ጋር በትብብር እንድትወጣ የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ሞያዊ ነፃነትን ለማረጋገጥ፣ የተቆጣጣሪ እና የፈጻሚ አካላትን የቁጥጥር እና የአሠራር ተግባራትን ሚና በግልፅ ለመለየት፣ በሁሉም ኦፊሽያል ስታቲስቲክስ አመንጪዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር፣ የመረጃ ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ፣ የስታቲስቲክስ ውጤቶችን ጥራት ለማሻሻል፣ ተደራሽነታቸውን ለማረጋገጥ እና ሀገራዊ አሠራሮችን ከዓለም አቀፍ የስታቲስቲክስ መርሆዎች እና ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም እንዲያስችል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

6. አስከትሎም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ከአሥር አመቱ የልማት ዕቅድ፣ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ፣ ከምዕተ አመቱ የልማት ግቦች እና ከሌሎች ፖሊሲዎች ጋር ተጣጥሞ የአገራችንን የኢነርጂ ሀብት በአነስተኛ ዋጋ በማልማት ዘላቂ፣ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ በዋጋ ተመጣጣኝና ተወዳዳሪ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲኖርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

7. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው ብሄራዊ የሴቶች ማብቃት እና የስርዓተ ጾታ እኩልነት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው ለስርአተ ጾታ መዛባት ስር ነቀል የሆኑ ጉዳዮች ላይ በቂ ትኩረት ለመስጠት፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን በአግባቡ ለመከላከል እና ጥበቃና ምላሽ ለመስጠት፣ ልዩ ትኩረት ለሚሹ ሴት አካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ስርአተ-ጾታን መሰረት ካደረጉ አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች ጋር በማጣጣም ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

8. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንሹራንስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ገበያውን ተኣማኒነት የሚያጠናክር፣ ፍትሃዊ፣ ደህንነቱ ተረጋገጠ እና የተረጋጋ የኢንሹራንስ ገበያ እንዲኖር የሚያበረታታ፣ የመድን ገቢዎችን እና የመድን አገናኞችን ደንበኞች ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ የኢንሹራንስ ገበያውን ለመቆጣጠርና ለመምራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

9. በማስከተል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የንግድ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የንግድ ስርአትን በአግባቡ ለመምራት፣ በተመረጡ የገበያ ክፍተት ባለባቸው ዘርፎች ክፍተቶችን ለመሙላት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር፣ የሀገራችንን የወጪ ንግድ በግብርና ምርቶች ያለውን ጥገኝነት በማላቀቅ የወጪ ምርትና አገልግሎት ብዝሃነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ የምርት ደህንነት መስፈርቶችን ለማውጣት እና ፍትሃዊ የንግድ አሰራርን ለመዘርጋት፣ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነትን እንዲገነቡ፣ ምርታማነትን እንዲያሳድጉና የአካባቢ አቅምን እንዲያዳብሩ ድጋፎችን በመስጠት በዘርፉ ያሉ ተግዳሮችን ለመፍታት እንዲያስችል ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

10. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንን አደረጃጀት፤ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ባለስልጣኑ በህግ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲያስችለው ማሻሻያ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

11. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት ተጠቃሚ የሚሆኑ ባለቤቶችን መረጃ ግልጸኝነት ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በአግባቡ ለማስፈጸም እንዲያስችል ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

12. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ከሥርዓተ ምግብ መዛባት ጋር የተያያዙ በሽታዎች በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢያዊ፣ በምርታማነትና በማህበራዊ መስተጋብር እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስና ለማጥፋት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይህን ስራ የሚያስተባብር አደረጃጀት ለመፍጠር፤ ሀብት በዘላቂነት ለመመደብና የማህበረሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ፣ ሀገራችን የገባቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶችና የተቀመጡ የምግብ ስርዓትና ሥርዓተ ምግብ ግቦችን ለማሳካት የህግ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

13. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸምን ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ በታወቀ ጥቅል የበጀት ድጋፍ ስርዓት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ፣ የፋይናንስ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊነት እና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ፣ የራስን ወጪ በራስ የመሸፈን ድርሻን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ፣ በተቋማቱ መካከል ተመጣጣኝ የመማር-ማስተማር፣ የአገልግሎት ጥራት እና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ ሁኔታ ሀላፊነት የተሞላበት ስራዎችን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

የሰላምና ጸጥታ መዋቅሮች በክልሉ ያልተገደበ ሰላማዊ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲኖር ያደረጉት ቅንጅታዊ ስራ ውጤታማ እንደነበር  የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ ። (ሆሳዕና፣ ግንቦት 12/ ...
20/05/2026

የሰላምና ጸጥታ መዋቅሮች በክልሉ ያልተገደበ ሰላማዊ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲኖር ያደረጉት ቅንጅታዊ ስራ ውጤታማ እንደነበር የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ ።

(ሆሳዕና፣ ግንቦት 12/ 2018)፣ ቢሮው ወቅታዊ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ እየገመገመ ነው።

የሰላምና ጸጥታ መዋቅሮች በያዝነው በጀት አመት በተያዘው ግብ መሰረት በክልሉ ያልተገደበ ሰላማዊ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲኖር ያደረጉት ቅንጅታዊ ስራ ውጤታማ እንደነበር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል ።

ቢሮው ከዞንና ልዩ ወረዳ መዋቅሮች ጋር ወቅታዊ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በሆሳዕና ከተማ እየገመገመ ይገኛል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ሰላማዊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ መዋቅሩ ባደረገው የተቀናጀ ጥረት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ።

እነዚህ በእቅድ የተደገፉ የሰላምና ጸጥታ ማስከበር ተግባራት ሰዎች በየትኛውም ሰኣት ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻላቸውንም ሃላፊው አስታውቀዋል ።

እንደ ክልል በበጀቱ አመቱ መግቢያ ላይ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረገጥ ተቀዳሚ ግብ ተቀምጦ ወደ ስራ መገባቱን የጠቆሙት አቶ ተመስገን ይህ እንቅስቃሴ በህዝቦች መካከል መተማመንና አንድነት እንዲፈጠር ከማገዝ ባለፈ በየአካባቢው ያሉ ችግሮችና አለምግባባቶች እንዲፈቱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

መዋቅሩ ሰላምን ማስጠበቅ የህዝብ እሴትና ባህል እንዲሆን እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑንም አቶ ተመስገን ገልጸዋል ።

የፍትህ አካላትና የጸጥታ መዋቅሮች ቅንጅት ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ማህበረሰቡ ፈጣን ፍትህ እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለውም የቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል ።

ክልሉ ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር በመቀናጀት የአዋሳኝ አካባቢ ነዋሪዎችን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ያደረገው እንቅስቃሴ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል ።

በተለይ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተቀናጀ መንገድ እየተሰሩ ያሉ የጸጥታ ማስከበር ተግባራት የሁለቱን ክልሎች ነዋሪዎች ነጻና ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ ከማስፈን ባለፈ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርና ሁለንተናዊ ግንኙነት እየፈጠሩ እንደሆነ አስረድተዋል ።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ መዋቅር የቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊነት በማረጋገጥ እና ህገ ወጥ የግብርና ግብኣት እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ረገድ ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት አቶ ተመስገን አሳስበዋል ።

ምንጭ: የክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የ9 ወራት አፈጻጸምና የድጋፋዊ ክትትል ማጠቃለያ ሪፖርት ገመገመግንቦት 11/2018 ዓ.ም ሆሳዕና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥ...
19/05/2026

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የ9 ወራት አፈጻጸምና የድጋፋዊ ክትትል ማጠቃለያ ሪፖርት ገመገመ

ግንቦት 11/2018 ዓ.ም ሆሳዕና

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ፤ በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች ያደረገውን የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛ ሩብ ዓመት የተቀናጀ የድጋፋዊ ክትትልና የአፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያ ሪፖርት የኤጀንሲው ማኔጅመንት አካላት በተገኙበት ገምግሟል።

የድጋፋዊ ክትትል ሪፖርቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሽፋንን ከማሳደግ፣ የታብሌት ዲጂታል ምዝገባን ከማዘመን፣ ከባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ከመልካም አስተዳደር አንጻር የታዩ ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን ያመላከተ እንደሆነም ተመልክቷል ።

በድጋፈዊ ክትትሉ እንደተመለከተው አነዚህ መዋቅሮች የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች በማኔጅመንት ተገምግመው ለሚመለከተው አካል መላካቸውና የሰው ኃይል በየመዋቅሩ ከ70 በመቶ በላይ መሟላቱ በጥንካሬ ተነስቷል።

በተለይም የምዝገባ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት፤ በስልጤ ዞን የአልቾ ወርሮ ወረዳ ሽልማትና ቃዋቁቶ ቀበሌያት፣ እንዲሁም በጉራጌ ዞንና በቀቤና ልዩ ወረዳ ሙሉ በሙሉና በከፊል በታብሌት (ዲጂታል) ምዝገባ መጀመሩ በትልቅ ስኬትነት ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በጉራጌ ዞን የአሠራር ጥሰት በፈጸሙ መዝጋቢ ባለሙያዎች ላይ ከደመወዝ ቅጣት እስከ ሥራ ማሰናበት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱና የአገልግሎት ክፍያ ተመኖች በግልጽ ተለጥፈው መገኘታቸው፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተደረጉ አበረታች ጥረቶች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።

የሞት ምዝገባ ሽፋንን ከማሳደግ አንጻር በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የሚገኙ ዕድሮች የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በመተዳደሪያ ደንባቸው ውስጥ በማካተታቸው የሞት ምዝገባ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ተወስዷል። በየም ዞንም ከፍርድ ቤት ጋር በተደረገ የተቀናጀ አሠራር የፍቺ ምዝገባ አፈጻጸምን ከመቶ ፐርሰንት በላይ ማድረስ ተችሏል።

በሌላ በኩል፣ በሂደቱ ላይ አሁንም በርካታ ትኩረት የሚሹ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች መኖራቸውን ሪፖርቱ በጥብቅ አመልክቷል።
ከእነዚህም መካከል የተሰራጩ የክብር መዛግብትና የምስክር ወረቀቶች በፋይናንስ ደረጃ ኦዲት አለመደረጋቸው በዋና ዋና ክፍተትነት ተለይተዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ ቀበሌያት በሰው ኃይል እጥረት፣ በጸጥታ ችግርና በክህሎት ማነስ ምክንያት ምዝገባዎች የተቋረጡባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው ተጠቁሟል።

በመጨረሻውም ኤጀንሲው የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የፊት አመራሩ፣ የባለሙያው፣ የባለድርሻ አካላትና የጠቅላላው ኅብረተሰብ የተቀናጀ ድጋፍና ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን መገለጹን የኤጀንሲው ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

ሠላምን በማፅናት የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ግጭትን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ጠንካራ ተቋም መገንባት እንደሚገባ ተመላከተ(ሆሳዕና፣ ግንቦት 10/2018) ፣ የማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል...
18/05/2026

ሠላምን በማፅናት የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ግጭትን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ጠንካራ ተቋም መገንባት እንደሚገባ ተመላከተ

(ሆሳዕና፣ ግንቦት 10/2018) ፣ የማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የእቅድ አፈፃፀምና ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን ከተጠሪ ተቋማት ጋር በሆሳዕና ከተማ ገምግሟል።

የቢሮ ሀላፊ ተወካይና የፀጥታ መረጃ ዘርፍ ሀላፊ አቶ መስቀሉ መንጃ እንደተናገሩት ቢሮው ሠላምን በማፅናት የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ግጭትን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ጠንካራ ተቋም ለመገንባት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንደሀገርና ክልል የተለያዩ በርካታ ፍላጎቶች የሚስተዋልበት ወቅት በመሆኑ የፀጥታ መዋቅሩን አደረጃጀት በማጠናከር ሠላምን ዋነኛ አማራጭ በማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተቋሙም ሆነ የተጠሪ ተቋማት ተልዕኮ ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ እና የህዝቦችን ደህንነት ማረጋገጥ መሆኑን የተናገሩት አቶ መስቀሉ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የመከላከልና ሲከሰቱ የመቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፀጥታ ስራው ህዝባዊ መሠረት እንዲያገኝ በማድረግ በሠላም እሴት ግንባታና በግጭት አፈታት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ከወጣቶች ፣ከሴቶች እና ከተለያዩ አደረጃጀት ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራም ተጨባጭ ውጤት መጥቷል ብለዋል።

ግጭት ሳይፈጠር አስቀድሞ ለመከላከል የመረጃ ስርዓትን በማጠናከርና ለግጭት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች በመለየት እየተሰራ መሆኑን አመላክተው ይህን የሚሸረሽሩ በፀረ ሠላም ሀይሎችና በጽንፈኛ የማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎች ምንጭ እንዲሁም ተዓማኒነት በመለየት መመከት ከማህበረሰቡ ይጠበቃል ብለዋል።

ሠላምን በአንድ አካል ብቻ ማረጋገጥ ስለማይቻል ከህብረተሰቡ ፣ከየአካባቢው የፀጥታ አካላትና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

የማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አማካሪ አቶ ሸረፋ ሌገሶ በበኩላቸው ሠላም የሁሉም ድምር ውጤት በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር መስራት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ማጽናት እንደሚገባ ተናግረው ከማህበረሰቡ ጋር በሠላም ጉዳይ መድረኮች በመፍጠር ግንዛቤ የመስጠት ስራው ተጠናክሮ የሚሰራ ነው ብለዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫው ሠላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ሂደቱ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከናወን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በግምገማው መድረክ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳን ጨምሮ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ፣የፖሊስ፣የሚሊሻ እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ከክልል ኮሙኒኬሽን ገጽ የተወሰደ

የኢትዮጵያ አዲሱ የቃል-ኪዳን ድልድይ፡ ከቂም በቀል ስብራት ወደ ምክክር መድኃኒት!ቂምን አዝሎ መሮጥ መድረሻው ገደል ነው እንዲሉ  ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በታሪካዊና መዋቅራዊ ስብራቶች ውስ...
15/05/2026

የኢትዮጵያ አዲሱ የቃል-ኪዳን ድልድይ፡ ከቂም በቀል ስብራት ወደ ምክክር መድኃኒት!

ቂምን አዝሎ መሮጥ መድረሻው ገደል ነው እንዲሉ ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በታሪካዊና መዋቅራዊ ስብራቶች ውስጥ የቆየችው ያለፈውን ቁስል በዝምታ ሸፍኖ፣ ነገን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመቅረጽ በመሞከሯ ነው። ዛሬ ግን ይህንን የጥፋት አዙሪት የሚሰብር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል።

መንግሥት እንደ ትልቅ የሰላም ምሰሶ የተጠቀመበት ትናንትን በሽግግር ፍትሕ የማረም፣ ነገን ደግሞ በሀገራዊ ምክክር የመገንባት" ስትራቴጂ፣ ሀገራችን ለዘመናት ስትጠብቀው የነበረው የሰላም ድልድይ ነው።

ያለፉ በደሎች እና ግጭቶች ሳይታረሙና ተገቢው ፍትሕ ሳይሰጥ ወደ ፊት ለመጓዝ መሞከር የቆሰለን እግር ሳይታከሙ ለሩጫ እንደመዘጋጀት ይቆጠራል።

የሽግግር ፍትሕ ያለፈውን ሸክም የሚያቀልል ሲሆን ሀገራዊ ምክክር ደግሞ የነገውን መንገድ የሚጠርግ በመሆኑ ሁለቱ ሂደቶች የማይነጣጠሉና ተመጋጋሚ የሰላም መሣሪያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነቶችና ጥንታዊ እሴቶች ባለቤት ብትሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ የተቀነቀኑ የበደል ትርክቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታው ትልቅ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

ይህንን ስብራት ለመጠገን የተወጠነው ሀገራዊ ምክክር ግን ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ነው። ምክክሩ፡፡ “ለካስ ስለ ሀገሬ እኔም መምከር እችላለሁ፤ ለካስ የእኔም ድምፅ ይሰማል” የሚሉ ዜጎች ወደ ምክክሩ ቀርበዋል።

ከወረዳ እስከ ፌደራል፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቁጭ ብለው በጋራ እንዲመክሩ መደረጉ፣ ሂደቱ ምን ያህል አካታችና ተዓማኒ እንደሆነ ማሳያ ነው። የተበታተኑ ሐሳቦች ወደ አንድ የጋራ አጀንዳ መምጣታቸው ለሀገራዊ መግባባት የጸና መሠረት ይጥላል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ትልቅ ፋይዳ አላቸው። በቅርቡ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ወገኖች ሰላምን መርጠው ወደ ምክክር መድረኩ መምጣታቸው፣ የሐሳብ የበላይነት ከጠመንጃ ኃይል እንደሚበልጥ በተግባር ያሳየ ስኬት ነው።

ዛሬ ላይ የምናደርገው ምክክር የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ይወስናል። የቂም ቁርሾን ለትናንት ትተን፣ በፍቅር እና በውይይት የምትመራ፣ ለልጆቻችን የምትመች እና በሁለንተናዊ ብልጽግና የደመቀች ኢትዮጵያን መገንባት የትውልዱ የቤት ሥራ ነው።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ታላቁ ጉባኤ ሲጀመር፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሂደቱን በባለቤትነት ሊደግፈውና ሊሳተፍበት ይገባል።

የሀገራችንን ሰላም በጋራ ጥረት የምናጸናበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን በሰለጠነ ባህል የምትፈታ ሀገር እንድትሆን፣ ይህ ታሪካዊ የምክክር ጅማሮ ወደ ስኬት እንዲሻገር ሁላችንም የሰላም ጀግኖች ልንሆን ይገባል። ነገ ለልጆቻችን የምናወርሰው ሀገር በዛሬው ምክክራችንና በምናሳየው መቻቻል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ይህንን ወርቃማ ዕድል መጠቀም የታሪክ አደራ ነው።

ኢቢሲ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የመስክ ድጋፋዊ ክትትል ጀመረሆሳዕና (ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም) — የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀ...
07/05/2026

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የመስክ ድጋፋዊ ክትትል ጀመረ

ሆሳዕና (ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም) — የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ለመገምገም የሚያስችል ድጋፋዊ ክትትል መጀመሩን አስታውቋል ።

ይህ የመስክ ምልከታ በዋናነት የልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ ምዝገባ ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ለመለየትና የምዝገባ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚደረጉ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ዝግጅቶችን ለመገምገም ያለመ እንደሆነ የኤጀንሲው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዘግቧል ።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በተገኙበት  ሰባተኛውን ጠቅላላ  ሀገራዊ የምርጫ ሂደት ሠላማዊ በማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት  ተካሂዷል።ሆሳዕና ፣ ሚያዝያ 28 ፣ 2018፦የማዕከ...
06/05/2026

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በተገኙበት ሰባተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ የምርጫ ሂደት ሠላማዊ በማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።

ሆሳዕና ፣ ሚያዝያ 28 ፣ 2018፦የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በተገኙበት ሰባተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ የምርጫ ሂደት ሠላማዊ በማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል ።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በመድረኩ እንደገለፁት ፣የምርጫው ሂደት፣ በክልሉ ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ቀጥሏል፤ ይህ ሠላማዊ ሂደት እንዲቀጥል፣በተቀናጀና በተናበበ ሁኔታ ተጠናክሮ መሥራት ይጠበቃል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫው ሠላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ እንዲቀጥል ፣ ከምርጫ ጣቢያ ጀምሮ ዝግጁ በሆነ መንፈስ፣ በተደራጀና በተናበበ መንገድ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።

በመድረኩ የየአካባቢውን ወቅታዊ የሠላምና ፀጥታ አዝማሚያዎች የዳሰሰ ዉይይት ከማድረግ ባሻገር፣ በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት በመፍጠር ተጠናቅቋል ።

በዉይይት መድረኩ፣ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የፍትህ ቢሮ፣የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሚሊሻ ጽህፈት ቤት አመራሮች ተገኝተዋል።

Address

አድራሻ:~የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ፅ/ቤት ህንፃ 1ኛ ፎቅ
Hossana
HOSSANA,

Opening Hours

Monday 08:30 - 05:30
Tuesday 08:30 - 05:30
Wednesday 08:30 - 05:30
Thursday 08:30 - 05:30
Friday 08:30 - 05:30

Telephone

+468210183

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ:

Share