30/05/2026
የሐረሪ እና የምስራቅ ሐረርጌ ማረሚያ ተቋማት ከሕግ ታራሚዎች ጋር ልዩ የውይይት መድረክ አካሄዱ።
ሐረር፤ ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም
የሐረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና የምሥራቅ ሐረርጌ ማረሚያ ቤት ተልዕኮና አቅማቸውን በማቀናጀት፣ ከሕግ ታራሚዎች ጋር ያለውን የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ የሚያጠነጥን ልዩ የውይይት መድረክ ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በጋራ አካሂደዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሐረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አድናን አህመድ፤ ሐረር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላምና በፍቅር አብሮ የመኖር ታሪካዊ እሴት የምትታወቅ ከተማ መሆኗን አስታውሰው፣ ይህ በጎ መገለጫ በማረሚያ ቤቱም ውስጥ በተግባር እየታየ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በከተማዋ በሚገኘው ማረሚያ ቤት የሁለቱ ክልሎች ሕግ ታራሚዎች በወንድማማችነትና በሰላም በጋራ የሚኖሩበት በመሆኑ፣ ተቋሙን በሀገሪቱ ካሉ መሰል ተቋማት መካከል ብቸኛና ልዩ ተምሳሌት እንደሚያደርገው በልበ ሙሉነት አስገንዝበዋል። የምስራቅ ሐረርጌ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ኮማንደር ከማል ገናም በበኩላቸው፣ ይህንን መልካም አንድነት ይበልጥ በማጠናከር በጋራና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ኮሚሽነር አድናን አህመድ በማጠቃለያ ንግግራቸው የሁለቱን ተቋማት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይም የሁለቱን ተቋማት ተልዕኮ በማቀናጀት ታራሚዎችን የማረም፣ የማነፅና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ የመቀላቀል ሂደትን ውጤታማ ለማድረግ አቅሞችን በትብብርና በቅንጅት ማስተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉት የሕግ ታራሚዎች በበኩላቸው፣ የተጀመሩ የልማትና የማሻሻያ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ፍላጎታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች ታራሚዎች መካከል ያለውን የሰላምና የአብሮነት ልዩ እሴት ጠብቀው ለማስቀጠል የበኩላቸውን ድርሻ በቁርጠኝነት እንደሚወጡ በሙሉ እምነት አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ኮማንደር ማህዲ