16/10/2024
የአደንዛዥ እፆች እና የህግ ተጠያቂነት በአትዮጵያ
--------------****-------------
የአደንዛዥ እፅ ትርጉም
አድንዛዥ እፅ ማለት ከምግብ እና መጠጥ ውጪ የሆነ ወደ ሰውነት ውስጥ በሚገባ ጊዜ በሰውነት ስራ ላይ አካላዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ለውጥ የሚያስከትል ማንኛውም ንጥረ ነገር ነው፡፡ እፆች ህጋዊ የሆኑትን እንደ አልኮል፣ ካፌን እና ትንባሆ እንዲሁም ህጋዊ ያልሆኑ ወይም የተከለከሉ እንደ ካናቢስ፣ ኮኬን እና ሄሮኢን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሳይኮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች (Psychoactive drugs) በማዕከላዊ የአዕምሮ ክፍል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር የሰዎችን አመለካከት እና ባህሪይ ይቀይራሉ፡፡
እነዚህ ንጥረ ነጥሮች በአራት ሊከፈሉ የሚችሉ ሲሆን እነሱም፡- ድብርት ፈጣሪ (Depressants)፣ አነቃቂ ወይም ቀስቃሽ (Stimulants)፣ ሃሉሲኖጅንስ (Hallucinogens) እና ሌሎች (Other) ናቸው፡፡ ድብርት ፈጣሪ ንጥረ ነገሮች የማዕከላዊ አዕምሮ ክፍልን እንቅስሴ ዝቅ በማድረግ ንቃትን ይቀንሳሉ (decrease alertness)፡፡ ቀስቃሽ ንጥረ ነገሮች ደግሞ በተቃራኒው አዕምሮን በማነቃቃት የሰውነትን መነቃቃት ይጨምራሉ (increase the body's state of arousal):: ሃሉሲኖጅንስ በበኩላቸው የሰዎችን ግንዛቤ (perception) በመለወጥ ሰዎች የሌሉ ነገሮችን እንዲሰሙ እና እንዲያዩ ሊያደርጉ ወይም ከእውነት የራቀ ሃሳብ እንዲያስቡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የሌሎች (Other) የንጥረ ነገሮች አይነት ስር የሚመደቡት ደግሞ ከላይ የተገለፁት ንጥረ ነገሮች ከአንድ በላዩን ባህሪዎች በአንድ ጊዜ ይዘው ሲገኙ ነው፡፡
የአደንዛዥ እፆች ውጤት/ተፅዕኖ (effects of drugs)
------------------------
አደንዘዥ እፆች በሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ውጤት የሰዎችን ሁኔታ ማለትም አካላዊ ሁኔታ፣ እድሜ፣ ፆታ፣ ስሜት፣ አመጋገብ፣ አካላዊ ብቃትና ጤና፣ መጠበቅ (expectation) እንዲሁም እንዴት እና በምን አይነት አካባቢ እንደተወሰዱ መሰረት በማድረግ ከሰው ሰው ሊለያዩ የሚችሉ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ድብርታም፣ ተናዳጅ፣ ቁጡ፣ እንቅልፋም፣የማይነቃቃ (unmotivated)፣ ጭንቀታም ወይም ወሬኛ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ አደንዛዥ እፆችን መጠቀም ስሜታዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን በማስከተል ሰዎች ከቤተሰባቸው እና ከማህበረሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
በአደንዛዣ እፅ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚዎችን ሲሱ ውስጥ በማስገባት የእፆቹ ጥገኛ ያደርጋሉ፡፡ የአደንዛዥ እፅ ሱስ ማለት አንድ ሰው ራሱን መቆጣጠር እስኪያቅተው ድረስ የሱስ አምጭ ንጥረ ነገሮችን ለመውሰድ ፍላጎት ሲያድርበት እና ችግር የሚያስከትሉ እንደሆነ እያወቀ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ሲወስድ ነው፡፡ አደንዛዥ እፆች የሰዎችን ሀሳብ፤ ስሜት፤ እንቅልፍ፤ የምግብ ፍላጎት እና ማህበራዊ ግንኙነትን የመቀየር ውጤት አላቸው፡፡
አእምሮን የሚያነቃቁ አደንዛዥ እፆች በሚወሰዱበት ጊዜ በዋናነት አእምሮ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር በአካላዊና ስነልቦናዊ ተግባሮች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ብዙ ሰዎች የአደንዛዥ እፅ በሚፈጥረው የአእምሮ መነቃቃት እና አመለካከት ለውጥ በመደሰት ይዝናኑበታል፡፡ በመጨረሻም ይህ በመሆኑ ሰዎች ሳያውቁት በተደጋጋሚ በመውሰድ ወደ ልምድ ወይም ሱስ ውስጥ ይገባሉ፡፡
አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ አለም አቀፍ ህጎቸ
----------------------
በአለም አቀፍ ደረጃ አደንዛዥ ዕፆችን መቆጣጠርን በተመለከተ ሶስት ዋና አለም አቀፍ ስምምነቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም፡፡
1. የናርኮቲክ ንጥረ ነገር ነጠላ ኮንቬክሽን (the Single Convention on Narcotic Drugs of 1961 (as amended in 1972),
2. የሳይኮትሮፒክ ንጥረ ነገሮች ኮንቬክሽን (the Convention on Psychotropic Substances of 1971), እና
3. የተባበሩት መንግስታት ህገ ወጥ የናርኮቲክ እና ሳይኮትሮፒክ እፆችን ላይ የተደረገ ኮንኔክሽን (the United Nations Convention against Illicit Traffic in Narcotic Drugs and Psychotropic Substances of 1988).
እነዚህ ስምምነቶች እርስ በእርስ ተደጋጋፊ እና አንዱ አንዱ የሚያሟሉ ናቸው፡፡
ከእፅ ጋር የተገናኙ ወንጀል ድርጊቶች
-----------------------
ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አብዛኛው የአለም አገራት የአደንዛዥ እፆችን ጥፋት (offenses) በተለያዩ የወንጀል መለኪያ ቢሆንም በህጎቻቸው ውስጥ አካተው ይገኛሉ፡፡ጥፋቶቹ የአቅርቦት (supply) እንደ እርሻ፣ ማምረት (በፋብሪካ) እና ማዘዋወር እንዲሁም የፍላጎት (demand) እንደ መጠቀም እና መያዝን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ህጎች ተለይተው ጎጂ ናቸው የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ወይም አደንዛዥ ዕፆችን ማምረትን፣ ማዘማወርን፣መጠቀም እና መያዝን ወንጀል የሚያደርጉ ሲሆን አተገባበራቸው ከሀገር ሀገር የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁኑና ብሄራዊ ህጎቹ የአለም አቀፍ የህግ ማዕቀፎችን መዋቅር የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ እፅና ወንጀል ቢሮ (UNODC) በተባበሩት መንግስታት ስር የአለምን ሰላምና ፀጥታ፣ የሰብዓዊ መብቶች እና እድገትን ለማረጋገገጥ አለምን ከአደንዘዥ እፅ፣ ከወንጀል፣ ከሙስናና ከሽብርተኝነት የመጠበቅ ተልዕኮን ይወጣል፡፡
አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ህጎች በኢትዮጵያ
------------------------
በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው ወጣት በዚህ ሱስ ወስጥ በመጠመድ ለጤና፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ በመዳረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በርካታ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለወንጀል ተጠያቂነት በመጋለጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አደንዛዥ እፆችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን ማምረትና በማሰራጨት የሚደረጉ ወንጀሎች ስር ተካቶ ይገኛል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 525 ላይ እንደተደነገገው መርዛማ ወይም የናርኮተክና ሣይኮትሮፒክ መድኃነቶችን ወይም እፆችን ማምረት፣ መስራት፣ማዘዋወር ወይም መጠቀም የወንጀል ተጠያቂነቂነትን ያስከትላል፡፡ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች በድንጋጌው ስር የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡- ማንም ሰው ልዩ ፍቃድ ሳይኖረው መርዛማ ነገሮችን ወይም ናርኮቲክ ወይም ሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶችን ወይም እፆችን ያበቀለ፣ ያመረተ፣ የሰራ፣ የለዋወጠ ወይም የፈበረከ፤ ንጥረ ነገሮቹን ይዞ የተገኘ፣ ወደ ሀገር ያስገባ ወደ ውጪ አገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የደለለ፣ የገዛ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ያሰራጨ፣ ያዘዋወረ፣ አሳልፎ የሰጠ ወይም ለሌላ ያስገኘ፤ንጥረ ነገሮቹን ለመስሪያነት፣ ማቀነባበሪያነት፣ ማምረቻነት፣ መሸጫነት ወይም ማከፋፈያነት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሆነበትን ቤቱን ግቢውን ወይም ቦታውን የሰጠ፣ ያከራየ ወይም የፈቀደ ከአምስት ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከአንድ መቶ ሺህ ብር በማይበልት መቀጮ እንደሚቀጣ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 525/1 ይደነግጋል፡፡
ቅጣቱን የሚዛከብዱ ሁኔታዎች በአንቀፅ 525/2 ስር የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም፡-
ወንጀሉ የተፈፀመው ለዚሁ ንግድ ወይም በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ወንጀል ለመፈፀም በተደራጀ የቡድን ወይም የማህበር አባል በሆነ ወይም ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ሙያው አድርጎ በያዘ ሰው እንደሆነ ፤
ጥፋተኛው የተከለከለውን ህገ ወጥ ነገር ወይም ለዚሁ ዓይነቱ ነገር መጠቀሚያ ቦታ እያወቀ የሰጠው ወይም የፈቀደው በአፍቅሮ ንዋይ፣በወራዳነት ወይም አግባብ በሌለው ሌላ ዓላማ እንደሆነ፤ወይም ተጠቃሚው ህፃን፣ለአካለ መጠን ያልደረሰ ወጣት ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ወይም የእፅ ሱስ ያለበት እንደሆነ፤
ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈፀመው ሕፃናትን ወይም አዕምሮው ያልተስተካከለ ሰውን ለወንጀል ድርጊቱ አፈፃፀም መጠቀሚያነት በማድረግ እንደሆነ
ወንጀሉ የተፈፀመው በማረሚያ ቤት፣በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማህበራዊ አገልግሎት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ፣ሕፃናት ወይም ወጣት ተማሪዎች ለትምህርት፣ለስፖርት ወይም ለሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በመጠቀሙበት ቦታ እንደሆነ ወይምወንጀለኛው ከዚህ ቀደም በፈፀመው ተመሳሳይ ወንጀል ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት የነበረ እንደሆነ ከአምስት አመት በማያንስ ፅኑ እስራት እና ከአንድ መቶ ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጠል፡፡
ስለሆነም ሰዎች አደንዛዥ ዕፆችን የተመለከቱ ክልከላዎችን ባለመተላለፍ እራሱን ከህግ ተጠያቂነት እና ንጥረ ነገሮቹ ከሚያስከትሉት የስነ ልቦና፣ ማህበራዊ እና የጤና ጉዳት ሊጠብቅ ይገባል፡፡