06/06/2026
በገንዳውሃ ከተማ ቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማጠናከርና ለተማሪዎች የተሻለ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር በተያዘው እቅድ መሰረት በገንዳውሃ ከተማ ቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዲስ የትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በይፋ ተቀምጧል።
በመሰረት ድንጋዩ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ የገንዳውሃ ከተማ ዋና ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሃመድ፣ የገንዳውሃ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ አስማረች ቆያቸው፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ይግለጥ አበባው፣የገንዳውሃ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ በየነ አዳነ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ መምህራንና ወላጆች ተገኝተዋል።
በፕሮግራሙ ንግግር ያደረጉት የገንዳውሃ ከተማ ዋና ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሃመድ፣ ትምህርት የማንኛውም ማህበረሰብ እድገት መሰረት መሆኑን ገልፀው የዛሬው ፕሮጀክት የከተማዋን የትምህርት አገልግሎት ለማሳደግና በተለይም የተማሪዎችን የመማር ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የገንዳውሃ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ አስማረች ቆያቸው በበኩላቸው፣ በሰው ሀብት ልማት ውስጥ ትምህርት ያለውን ወሳኝ ሚና በማንሳት የትምህርት ቤቱ ግንባታ የተማሪዎችን የመማሪያ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ህብረተሰቡም የፕሮጀክቱን ስኬት ለማረጋገጥ በትብብር እንዲሰራ አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ይግለጥ አበባው በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በዘመናዊ የግንባታ ደረጃዎች መሰረት እንደሚገነባ ገልፀው ለተማሪዎች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመዋል። የግንባታ ሂደቱም በቅርበት እንደሚከታተል አስረድተዋል ።
ተሳታፊዎችም የትምህርት ቤቱ ግንባታ ለከተማው እና ለተማሪዎች ትልቅ እፎይታ እንደሚያመጣ ገልጸው ፕሮጀክቱ በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የመሰረት ድንጋዩ መቀመጥ በገንዳውሃ ከተማ የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች አንዱ ሲሆን ትውልድን በእውቀት ለማብቃት እና የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን የሚያግዝ ጠቃሚ ፕሮጀክት መሆኑ ተጠቅሷል።
የገንዳውሃ ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን፡፡