25/01/2026
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የማራኪ ክፍለ ከተማ ማኅበራዊ ዘርፍ ጽ/ቤት በግማሽ በጀት ዓመት ተግባር አፈጻጸም 1ኛ በመውጣት ተሸላሚ ሆነ።
በግማሽ በጀት ዓመቱ በመናበብ እና በቅንጅት በመሰራቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የጎንደር ከተማ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የ6ወር እቅድ አፈፃፀም በዛሬው ዕለት የገመገመ ሲሆን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉቀን ጌታሁን እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ተቀራርቦ እና በመቀናጀት በመሰራቱ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል ።
የችግር ተጋላጭ የሆኑ አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው የሴቶች የወጣቶች፣ የአረጋውያን፣ የአካል ጉዳተኞች እና የህጻናት አደረጃጀት እሰከ ታችኛው እርከን ድርስ ውጤት በሚያመጣ መልኩ መደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ተቋማት አካቶ ትግበራ ላይ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊዋ ሴቶች የወጣቶች የአረጋዉያን የአካል ጉዳተኞች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ተሳታፊነት ለማሳደግ መሰራት ይገባል ብለዋል።
የተቋሙን የመፈጸም አቅም ማሳደግ እንደሚገባ በመጠቆም ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ በመስራት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሴቶች አደረጃጀቶች ለሴቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ ቀበሌዎች ብቁና ተቀራራቢ ውጤት እንዲኖራቸው ክፍለ ከተሞች አስፈላጊውን ድጋፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ መስራት እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን በገቢ ማስገኛ ሴቶች እና ወጣቶች በማሰማራት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ወይዘሮ ሙሉቀን አሳስበዋል ።
የጎንደር ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ወጣቶች ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ልኪቱ አሰፋ በበኩላቸው የችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል ።
የሴቶች አደረጃጀት ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው የአካቶ ትግበራ ሥራ ከባለፈው ዓመት በተሻለ መንገድ መከናወኑን አብራርተዋል ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እስካለው ተባባል ደግሞ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባር ሁሉም ክፍለ ከተሞች አበረታች ሥራ መስራታቸውን ገልጸዋል ።
የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀት የክትትል እና ድጋፍ ሥራ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል ።
በበጀት ዓመቱ ማራኪ ክፍለ ከተማ ማኅበራዊ ዘርፍ ጽ/ቤት የተሻለ ውጤት በማስመዝገቡ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል።
ክፍለ ከተማው በ2018 በጀት ዓመት በ1ኛ ሩብ ዓመትም ከሌሎች ክፍለ ከተሞች በአፈጻጸም 1ኛ በመውጣት ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን በሁለተኛው ሩብ ዓመትም የተሻለ ሥራ በመሥራት የዕውቅና ደረጃውን አስጠብቆ ቀጥሏል።