14/09/2026
#ሰኞ፡- እኛን እናስተዋውቅዎ (ክፍል አራት)
የባለጉዳዮች ግዴታዎች በፍርድ ቤት!
ሰላም ውድ የገፃችን ቤተሰቦች🙏! "እኛን እናስተዋውቅዎ" በተሰኘው አምዳችን የፍርድ ቤታችንን አሰራር፣ እሴቶች እና መርሆች ማካፈላችንን ቀጥለናል። ባለፈው ክፍል (ክፍል ሶስት) ላይ የፍርድ ቤት አገልጋዮች የህግ ምክር መስጠት ለምን እንደማይችሉ እና የህግ ግንኙነት ድንበራችንን ማየታችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የፍትህ ስርአቱ የተሳለጠ እና ቀልጣፋ እንዲሆን እናንተ ውድ ባለጉዳዮች ወደ ተቋማችን ስትመጡ ልታሟሏቸው ስለሚገቡ መሰረታዊ ግዴታዎች እናወራለን!
የፍርድ ሂደት የተሳካ የሚሆነው ዳኞች እና ሰራተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ባለጉዳዮችም የሚከተሉትን የድርሻቸውን ሲወጡ ነው፦
#1. የፍርድ ቤቱን ክብርና ስነ-ስርዓት ማክበር፦
ፍርድ ቤት የፍትህ አደባባይ በመሆኑ የፍርድ ቤቱን ክብር የሚመጥን አለባበስ መልበስ፣ በችሎት ውስጥ ፀጥታን ማክበር እና የዳኛውን ትዕዛዝ ያለማንገራገር መፈፀም የሁሉም ባለጉዳይ የመጀመሪያው ግዴታ ነው።
#2. ቀጠሮን ማክበር እና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፦
ለተሰጠዎት ቀጠሮ በሰዓቱ መገኘት ፍትህ እንዳይጓተት ትልቅ አስተዋፅዖ አለው። አንድ ባለጉዳይ ሲዘገይ የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ተገልጋዮች ጊዜ ያባክናል፣ የፍርድ ሂደቱንም ያጓትታል::
#3. እውነተኛ ማስረጃ እና ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ፦
ለፍርድ ቤቱ የሚሰጡት ማንኛውም ቃል፣ ማመልከቻ ወይም ማስረጃ እውነተኛ መሆን አለበት። ሀሰተኛ ማስረጃ ማቅረብ ፍትህን ከማዛባት ባለፈ በህግ የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል ነው።
#4. ከህገ-ወጥ አሰራሮች መቆጠብ፦
ባለፈው ክፍላችን እንዳነሳነው፣ ሰራተኞችም ሆኑ ዳኞች ገለልተኛ ሆነው ማገልገል አለባቸው። ስለዚህ ባለጉዳዮችም ይህንን ተረድተው በማንኛውም ሁኔታ ሰራተኞችንና ዳኞችን በስጦታ፣ በጉቦ፣ በዝምድና ወይም በሌላ ህገ-ወጥ መንገድ ለማግባባት መሞከር የለባቸውም። ፍትህ የሚገኘው በእውነት እንጂ በግንኙነት አይደለም!
#ግዴታውን ያወቀና ስርዓቱን ያከበረ ባለጉዳይ ለፈጣን ፍትህ መሰረት ነውና እውነተኛ ፍትህ የሚሰፍነው፣ የፍርድ ቤት አገልጋዮች በገለልተኝነት ፀንተው ሲሰሩ ፣ ባለጉዳዮችም የድርሻቸውን ግዴታ ሲወጡ ነው!
በድጋሚ 2019 ዓመት በሁሉም ረገድ ስኬታማ የምትሆኑበት ዓመት እንዲሆን እየተመኘን(https://www.facebook.com/100064507611552/posts/1497592959067610/?app=fbl)🌼🌼 በቀጣይ ክፍላችን ስንገናኝ እነዚህን ግዴታዎች ማይወጣ ባለጉዳይ ላይ ያለውን የሕግ ተጠያቂነት የምናይ ይሆናል፤ እስከቀጣይ ሳምንት ቸር እንሰንብት 🙏
መስከረም 04 ቀን 2019 ዓ.ም
✍️ ጯሂት
⚖️ "ፍትሕን በታማኝነት!"
🗣️ ሀሳብ አስተያየትዎን በኮመንት ያካፍሉን!
🤝 ቤተሰብ ይሁኑ! አዳዲስና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት የፌስቡክ ገፃችንን ላይክ እና ሼር ያድርጉ👇
[https://www.facebook.com/100064507611552](https://www.facebook.com/100064507611552)