23/05/2026
ባለፉት አምስት ዓመታት ከ2003 ዓ.ም በፊት ህጋዊ እውቅና ከተሰጠው አካል ፍቃድ ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ ለተያዙ 7228 ይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲመጡ መደረጉን ጽ/ቤቱ ገለጸ።
በድሬደዋ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ጽ/ቤት ባለፉት 5 ዓመታት ለ11,796 ይዞታዎች የሽንሸና ፕላን በማዘጋጀት፣ ከእነዚህ ውስጥ በህግ እውቅናና ፍቃድ ለተሰጣቸው ከ2003 ዓ.ም በፊት ለተያዙ 7228 ይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመስጠት ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲገቡ መደረጉን ገልጿል።
የመሬት ይዞታ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሁሴን መሀመድ ሳኒ እንደገለጹት፣ የህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረውን በይዞታው ላይ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝና ንብረት ማፍራት እንዲችል ወደ ህጋዊ ስርዓት የማምጣት ስራ በስፋት ተሰርቷል።
በዚህም በእቅድ ከተያዘው 100% በላይ አፈፃፀም መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ይዞታዎቹ በፕላን መሰረት እንዲሰፍሩ በማድረግ የህብረተሰቡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ማስከፈት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም ህብረተሰቡ በይዞታው ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በማግኘቱ ወደ ህጋዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በመግባት ተጠቃሚ እየሆነ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም አስተዳደሩ ከዘርፉ የሚያገኘው ገቢ እንዲያድግ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ግንቦት 15 ቀን 2018 ዓ.ም