13/04/2026
#ድሬና ኳስ
ስለ ድሬዳዋ የእግር ኳስ ታሪክ አጭር ቅኝት
ድሬዳዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ውድድሮችም ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸውን በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በማበርከት ትታወቃለች። በአፍሪካ እግር ኳስ ውድድር ታሪክ የኢትዮጵያን ተደጋጋሚ ተሳትፎ ስንመለከት፣ ከድሬዳዋ የወጡ አስደናቂ ተጫዋቾችን ስም በግንባር ቀደምትነት ማግኘት አይቀሬ ነው።
በቀድሞው ጊዜ ከ11 የብሔራዊ ቡድን ተሰላፊዎች ከ6 በላይ የሚሆኑት ከድሬዳዋ የነበሩ ሲሆን፣ እንደ አዳሙ አለሙ፣ ግርማ ዘለቀ፣ ሙቅቢል ጅብሪል፣ ተካበ ዘውዴ፣ መሐመድ ኡስማን(ሚግ)፣ አሰግድ ተስፋዬ፣ በከሬ አደም፣ መሐመድ ቢን ሸሪፍ፣ ዳኛቸው ደምሴ፣ ጌታቸው ወልዴ ፣ አባይነህ ጌታሁን ጌታቸው ገላሼ ፤ ፍሰሃ በጋሻው፣ አግላን ዚያድ፣ ኤልያስ ሙሜ ፣ አድላቸው ፍቅሩ ፣ አሸናፊ ግርማ፣ ዩርዳኖስ አባይ ፣ ሲሞን አባይ ፣ ሳምሶን ሚካኤል ፣ ኢብራሒም ጃሚ ወ.ዘ.ተ ሌሎችን ታዋቂና ስመጥር የእግር ኳስ ሊቆችንና ኮከቦችን ስፍር ቁጥር የለሽ የታላላቅ ክለቦች ማልያ ሰማቸውን በአራቱም ማዕዘን ያሰጠሩ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ። ታዲያ በአሁኑ ወቅትም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አስተዳደሩ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰቶ እየሰራ ሲሆን በዚህም የድሬዳዋ እግር ኳስ የቀደመ ገናና ታሪክም እየተመለሰ ይገኛል።
👉 ክለቦቿ
የቀድሞው የጥጥ ፋብሪካ ክለብ፣ የአሁኑ ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ክለብ በድሬዳዋ ከተማ የተመሠረተ ስመ ገናና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ሻምፒዮና የተጫወተ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ክለብም ጭምር ነው። በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ፣ በዚህ ክለብ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከኤርትራ የተወሰዱ ሲሆን፣ ይህም ለድሬዳዋ የእግር ኳስ ፕሮፌሽናሊዝምን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ነበረው።
በ1980 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና ስታሸንፍ፣ እንደ ተካበ ዘውዴ (ግብ ጠባቂ) እና መሐመድ ቢን ሸሪፍ ያሉ የቀድሞው የጥጥ ፋብሪካ ክለብ ተጫዋቾች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያ ለብሰው ተጫውተዋል። በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የ1964 ውድድር ላይ የጥጥ ፋብሪካ ክለብ የግማሽ ፍጻሜ ደረጃ ላይ በመድረስ ምርጥ አፈፃፀምንም አሳይቷል ።
ኢትዮ ሲሚንት ስፖርት ክለብ በድሬዳዋ ከተማ ሌላኛው አንጋፋ ክለብ ሲሆን፣ በ1964 የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ እንደ ሊቻኖ ቫሳሎ፣ ኤታሎ ቫሳሎ፣ ጌታቸው ወልዴ እና ግርማ ዘለቀ ባሉ ምርጥ ተሰጥኦ ባላቸው ተጫዋቾቹ አማካኝነት ኢትዮጵያን አስጠርተዋል ። እነዚህ ተጫዋቾች የሚመሩት ቡድን በ1964 ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮናም ሆነዋል።
👉ስለ ድሬዳዋ ስታዲየም አጭር ዳሰሳ
ታሪክ እንደሚያመለክተው፣ እ.ኤ.አ.በ1967 የድሬዳዋ ስታዲየም መሠረት ድንጋይ እንደ ተቀመጠ ይነገራል ፤ ታዲያ ስቴዲየሙ በየጊዜው የተለያዩ እድሳት እና ማሻሻያዎችን ተደርገውለታል።
ስታዲየሙ በዋነኝነት ለእግር ኳስ ጨዋታዎች የሚያገለግል ሲሆን ሌሎችንም ብዙ አገልግሎቶች ይሰጣል፣ በስታዲየሙ ዙሪያ፣ ገቢ ከሚያመነጩ ሥራዎች በተጨማሪ፣ የስታዲየሙ መስፋፋት ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ሰዓት የድሬዳዋ አለም አቀፍ ስታዲየም የካፍ (CAF) መስፈርትን አሟልቶ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን እያስተናገደ ሲገኝ ይህም፤ በድሬዳዋ ለስፖርቱ ዘርፍ በተለይም ለእግር ኳሱ እድገት ከፍተኛ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ መሆኑ ያሳያል። በተለያዩ ወቅት አገር አቀፍ ጨዋታዎችን በማስተናገድ በሀገሪቱ ከሚገኙ ዘመናዊ ስታዲዩሞች ተመራጭ አድርጉታል። ታዲያ ለዚህ ድል ስፖርት ወዳዱ የአስተዳደሩ ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ከፍተኛ አስተዋፆ ያደረጉ ሲሆን ዘርፉን በቅርበት እየደገፉም ይገኛሉ።
ከጥቂት ቀናት በፊት ለ 2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ የድሬዳዋ አለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን እና የሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ብሔራዊ ቡድንን ጨዋታን ያስተናገደ ሲሆን ጨዋታውም በኢትዮጵያ 1 ለ 0 አሸናፊነት በድል ተጠናቋል።
ታዲያ በጨዋታው ወቅት ከፍተኛ ዝናብ የጣለ ቢሆንም የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሜዳ በሚገርም ሁኔታ ምንም ጭቃም ሆነ ውሃ ሳይታይበት ካለምንም እንከን በጥራት ጨዋታውን አከናውኖ አጠናቋል።
የድሬዳዋ ስታዲየም በዚህ ልክ ደረጃውን ከፍ አድርጎና በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ለመሰራቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቷል።
ታዲያ ጨዋታው ቀደም ሲል በዝግ ስታዲየም እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረ ሲሆን ደጋፊዎች በተገኙበት እንዲካሄድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፈቃድ ሰቷል።
የካፍ የደህንነት ኦፊሰር በድሬዳዋ ስታዲየም ተገኝተው ባደረጉት በአካል ምልከታና ግምገማ መሠረት፣ 10,000 ተመልካቾች በስታዲየሙ ተገኝተው ጨዋታውን እንዲከታተሉ በመወሰኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ጨዋታውን በመከታተል ዋልያዎቹን አበረታተዋል።
👉ስፖርት ወዳዱ የድሬ ህዝብ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መሥራች አገር ናት። እንዲሁም ደግሞ በ1962 የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ታላቅ ታሪካዊ ስኬት አላት። እንደ ይድነቃቸው ተሰማ ያሉ አንጋፋ የስፖርት አመራሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ታዲያ ድሬና ስፖርት ተነጣጥለው የማይታዩ መሆናቸው ቀደምት ታሪክ የሚያስረዳ ሲሆን የድሬዳዋ ማህበረሰብ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር በአፍሪካ ደረጃ በጣም ጎልቶ የሚታይ ነው። በዚህም ታዲያ የድሬዳዋ ክለቦቿ ከአገር አቀፍ እስከ አለም አቀፍ የደረሰ አበረታች ውጤቶች ባለቤት ናቸው። ማህበረሰቡም ለኳሱ ጥልቅ ፍቅር አለው።
ለዚህ ጥልቅ ፍቅር በርካታ ምክንያቶች አሉ። ስመጥር ታላላቅ ተጫዋቾች ከድሬዳዋ አልፈው በኢትዮጵያውያ የኳስ ታሪክ ላይ አሻራቸውን አኑረዋል። የድሬዳዋ እግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል ያለው ፉክክር ፍፁም ሰላማዊና ስፖርታዊ ጨዋነት የሚታይበት ነው። በዚህም ነው ማህበረሰቡ ለኳሱ ያለው ፍቅር የሚገለፀው፤ እነሆ "ስፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአብሮነት" በድሬዳዋ መገለጫ ሆኖ ይቀጥላል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን