03/06/2026
በደቡብ ወሎ ዞን የምርጫና የሰላም ማስከበር ተግባራት አፈፃፀም ተገመገመ፤ ለቀጣይ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎችም አቅጣጫ ተቀመጠ
የደቡብ ወሎ ዞን የምርጫና የሰላም ማስከበር ተግባራት አፈፃፀምን የሚገመግም የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ በአቶ መሐመድ አሊ የቀረበውን ዝርዝር የአፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
እጅግ ስኬታማ ምርጫ መፈጸሙ ተነስቷል። በየደረጃው ያለ አመራር፣ የፀጥታ ኃይልና ሕዝቡ ለስኬቱ የነቃና የላቀ አበርክቶ ማድረጋቸው በውይይቱ ተረጋግጧል፡
በሂደቱም የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችና ያጋጠሙ ውስንነቶች በዝርዝር የተለዩ ሲሆን፥ ጉድለቶችን በአስቸኳይ በማረም የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል።
ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ለአጠቃላይ ዕድገት ወሳኝ መሆኑ በመድረኩ የተሰመረበት ሲሆን፥ በቀጣይም የሰላም ሥራዎችን በቁርጠኝነት ከመስራት በተጓዳኝ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በላቀ ውጤታማነት ለማከናወን የሚያስችል ስልታዊ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚህ ወሳኝ የውይይት መድረክ ላይ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ እንዲሁም ሌሎች የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው የጋራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።