29/03/2026
ከመገለል ወደ ማዕከልነት፡ የመጋቢት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አካታችነት አዲስ ምዕራፍ
*****************************
የመጋቢት 2010 ዓ.ም ለውጥ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ቀደም ሲል የነበረውን የተገደበ እና የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ የበላይ የሆኑበትን ሥርዓት በመቀየር ረገድ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ይመዘገባል።
ይህ ለውጥ በተለይ ላለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት "አጋር" በሚል መጠሪያ ከማዕከላዊ የውሳኔ ሰጪነት ሚና ተገልለው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ መሐል ያመጣበት ሂደት ዋና መገለጫው ነው።
ቀደም ሲል በነበረው የኢሕአዴግ አወቃቀር ውስጥ አራቱ አባል ድርጅቶች ብቻ የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት ሲሆን ፤ እንደ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሐረሪ ያሉ ክልሎች በሞግዚትነት የሚመሩበት ሥርዓት ሰፍኖ ቆይቷል።
ይህ አሠራር በክልሎቹ ሕዝቦች ዘንድ የሁለተኛ ዜግነት ስሜት በመፍጠር ለሀገራዊ አንድነት መላላት ምክንያት ሆኖ የቆየ ቢሆንም፣ ከለውጡ ማግስት ይህ ታሪካዊ አድልዎ በውህደት ተቀይሯል።
የቀድሞ "አጋር" ክልል ተወካዮች በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ማለትም በሥራ አስፈፃሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እኩል ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ የክልሎችን እኩልነት በተግባር ተረጋግጧል።
ከዚህም ጎን ለጎን በስደት የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ መደረጉ ለአንድ ፓርቲ የበላይነት ስርዓት ማብቃት ትልቅ መሠረት ጥሏል።
ምንም እንኳ የፖለቲካ ባህላችንን ከእልህ ወደ ውይይት የመቀየር ጉዞ አሁንም ፈተናዎች ቢገጥሙትም፣ የመጋቢት ለውጥ ያስገኘው ፖለቲካዊ አካታችነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ታሪካዊ መነሻ ነው።
ይህንን ዕድል ለዘላቂ ሰላም ማዋል የሁሉም ፖለቲካዊ ተዋናዮች የጋራ ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
በለሚ ታደሰ
ሙሉ መረጃውን በአስተያየት መስጫው ያገኙታል! 🔗