12/07/2025
ከእንግዲህ ተስፋችን ማነው?
እየገረመኝ ነው። ማለት ሰው የሆነ ምድራዊ ስኬት ይፈልጋል መቸም፤ ለዚያ ደግሞ ያው ብር ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት የሚገርመው ሰው ስንት ብር እንደሚፈልግ አያውቅም። በቃ ብር ነው የሚፈልገው፣ ሊወድቅ የሚንገዳገድ ሰው ያገኘውን ነገር እንደሚይዝ የሆነ ብር ይፈልጋል። ግን ብር ብቻ ሳይሆን ቁጥር ራሱ ጋሽቧል።
ተመልከቱ፦ ለምሳሌ አሁን አስር ሺ ብር የላችሁም፣ ቢኖራችሁም ምንም አይቀይርም! መቶ ሺ ብርም የላችሁም፣ ቢኖራችሁም ምንም አይቀይርም፣ አንድ ሚሊየን ብር የላችሁም፣ ቢኖራችሁ ደስ ይላችኋል፣ ብዙ ነገር የሚቀየር ይመስላችኋል፤ ግን እንደስሙ ምንም ነገር በዘላቂነት አይቀይርም።
ከኪራይ ቤት አትወጡም፣ ከታክሲ አትላቀቁም፣ ከተቀጣሪነትም ደፍሮ አያስወጣም፣ ቤት አይገዛ፣ መኪና አይገዛ፣ ደህና ስራ አያሰራ ...ትዳር አያሲዝ፣ ልጅ ደህና ትምህርት ቤት አያስተምር ፣ አያምጣው እንጅ ከበድ ያለ ህመም ብትታመሙ አያሳክም። ይሄም ሆኖ ደግሞ አይገኝም!! ቢገኝም ባይገኝም እፎይ የሚያስብለው ቁጥር ራሱ ተዛብቷል። ግን በህይወታችን ምንም ለማይቀይር ትንሽ ገንዘብ እንዳንራብ ሳይሆን የበለጠ እንዳንራብ በየቀኑ አፈር ግጠን እንሰራለን። ሶሻሊዝም አይሉት ካፒታሊዝም፣ "ኢዝም" አልባ ነገር! አይገርማችሁም?
ሰው ተኝቶ ህልሙ እንቁላል ፍርፍር፣ ቀይ ወጥ ምናምን ከሆነ-- እማማ ዝናሽ ራሳቸው ካለሁለት መቶ ብር ህልም አይፈቱም። እና ብዙኃኑ ሲጀመር ህይወቱም ህልሙም ተራ ነገር ሆኖበታል፤ የህልሙ ዋጋ ከማስፈቻው በታች ነው። እንግዲህ ደሀ በህልሙ ቅቤ ባይበላ፣ ምናምን የሚባለውን ተረት አስቡ፤ ህልም እንኳን የሚያስወድድ ህይወት!
ሳስበው ታዲያ ሰው ሳይሆን ፈጣሪ ራሱ አራግፎ ከባዶው እንደገና ሊሰራን ይሆን እንዴ እላለሁ። ከእርሱ ሌላ ምንም ተስፋ እንዳናደርግ ርቃናችንን ቆምንኮ! አይዞህ /አይዞሽ ማለት እንኳን የሚያሳቅቅበት ጊዜ!
(አሌክስ አብርሃም)