30/01/2026
አየር ሀይል በ2030 የአፍሪካ ቁንጮ ለመሆን የሚያስችለውን ሪፎርም በማከናወን ላይ ነው፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የ90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል። ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በታሪኩ ከፍተኛው ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2030 የአፍሪካ ቁንጮ ለመሆን የሚያስችለውን ታሪካዊ ሪፎርም በማከናወን ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የአራተኛው አየር ምድብ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ቸርነት መንገሻ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ አየር ኃይሉ በአሁኑ ወቅት በታሪኩ ታይቶ የማይታወቅ ሁለንተናዊ የሪፎርምና የተቋም ግንባታ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ተቋሙ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ፣ የሌሎች ሀገራትን የአየር ክልል የመጠበቅና የመከላከል ብቃት መገንባቱን አረጋግጠዋል።
ይህም አየር ኃይሉን በ2030 በአህጉሪቱ ቀዳሚ ለማድረግ ለተያዘው ግብ እንደ ትልቅ መሠረት እንደሚቆጠር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቆየውን የፓን አፍሪካኒዝም ዐሻራ በማስታወስ፤ ቀደምት የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ተቋሙ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የበርካታ የአፍሪካ ሀገራትን የአየር ኃይል አባላት በማሠልጠን የአህጉሪቱ የዕውቀት ማዕከል መሆኑን አብራርተዋል።
የአየር ኃይል አካዳሚ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ገዛኸኝ ነጋሽ በበኩላቸው፣ የ90ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ተቋሙ ከሕዝብ ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
ተቋሙ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰው በጠንካራ ሙያዊ ሥነ ምግባር መሆኑን አመላክተዋል።
አሁንም ይበልጥ በመስራት በርካታ ጀግኖችን እያፈራ ይገኛል ያሉት ኮሎኔል ገዛኸኝ፣ ዜጎች ስለ አየር ኃይላቸው ጥንካሬና ዝግጁነት በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በዓሉ ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።
የዘንድሮው ክብረ በዓል ንስሮቹ ያለፉበትን ፈታኝ ውጣ ውረድ ከማስታወስ ባለፈ፣ ተቋሙ የታጠቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለዓለም በማሳየት የኢትዮጵያን የሰማይ ላይ የበላይነት ዳግም ያረጋገጠበት ሆኖ ተመዝግቧል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
https://dfmc.mod.gov.et/
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
https://youtube.com/-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
https://www.facebook.com/fdredefense.official