የደቡብ ጎንደር ዞን አብን ፅ/ቤት South Gondar Zone NaMA

የደቡብ ጎንደር ዞን አብን ፅ/ቤት South Gondar Zone NaMA Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from የደቡብ ጎንደር ዞን አብን ፅ/ቤት South Gondar Zone NaMA, Political organisation, Debre Tabor.

ጉና በጌምድር ላይ አብን ዶክተር አማረች አስራትን የአማራን ህዝብ እንድትወክል በእጩነት አቅርቧል።ስዓትን ይምረጡ!!
07/03/2021

ጉና በጌምድር ላይ አብን ዶክተር አማረች አስራትን የአማራን ህዝብ እንድትወክል በእጩነት አቅርቧል።
ስዓትን ይምረጡ!!

የበጌምድሯ ታች ጋይንት ወረዳ የአብን እጩ የህዝብ እንደራሴ መ/ር ስመኘው መብራቱ !! በመምህርነት ዘርፍ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ የነበሩ ። መልካም ዕድል!!
07/03/2021

የበጌምድሯ ታች ጋይንት ወረዳ የአብን እጩ የህዝብ እንደራሴ መ/ር ስመኘው መብራቱ !! በመምህርነት ዘርፍ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ የነበሩ ። መልካም ዕድል!!

አልነጃሽ መስጅድ ጥቃትን በተመለከተ ከአብን የተሰጠ መግለጫ፤****የአገራችንም ይሁን የዓለማችን የእምነትና ስልጣኔ ግንባር ቀደም ምልክቶች ከሆኑት መካከል የኢትዬጵያዊው አልነጃሽ መስጅድ ግን...
02/01/2021

አልነጃሽ መስጅድ ጥቃትን በተመለከተ ከአብን የተሰጠ መግለጫ፤
****
የአገራችንም ይሁን የዓለማችን የእምነትና ስልጣኔ ግንባር ቀደም ምልክቶች ከሆኑት መካከል የኢትዬጵያዊው አልነጃሽ መስጅድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑት ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል።

አልነጃሽ መስጅድ የሙስሊሙ ኢትዬጵያዊ ወገናችን፣ አጠቃላይ የኢትዬጵያ ሕዝብና የመላው ዓለም የታሪክ አካል ነው። በኢስላም ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሂጅራ የተደረገበት እስከመባል የደረሰ ጉልህ ቦታ ያለው የታሪክና የእምነት አካል ነው።

ትህነግ በቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት አገራችን በሕይወት፣ ንብረትና ቅርስ ረገድ ዘግናኝ ጥፋቶችን እንዳስተናገደች ይታወቃል። ትህነግ ለታሪክና እምነት ዋጋ የማይሰጥ ድርጅት መሆኑ ከውልደቱ ጀምሮ የሚታወቅ ባህሪው ነው። የእምነት ተቋማትን ለማጥቃትም ይሁን በምሽግነት ለመጠቀም የማያመነታ ኃይል እንደሆነ እንገነዘባለን። ነገር ግን አልነጃሽ ላይ የተፈፀመው ጉዳይ ከጥቅል ፖለቲካ ግምት ያለፈ እንደሆነ አብን ይገነዘባል።

ስለሆነም አልነጃሽ መስጅድ ላይ የደረሰው ጥቃት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በገለልተኛ መልኩ በጥልቀት መመርመር ያለበት እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል። ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲሁም መላው የኢትዬጵያ ሕዝብ በመስጅዱና መቃብር ቦታዎቹ ላይ የደረሰውን ጥቃት፣ መጠኑንና የፈፀመውን አካል በግልፅ ማወቅ እንደሚፈልግ እንረዳለን። የተዘረፉ ቅርሶች እንዳሉ እየተነገረ ያለውን ጉዳይም በአግባቡ መመርመርና ማጣራት ያስፈልጋል።

በተገቢው ሁኔታ ከተጣራም በኋላ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየጠየቅን ጎንለጎን አፋጣኝ የመልሶ ግንባታና የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ ለመንግስትና ለመላው የኢትዬጵያ ሕዝብ ለማሳሰብ እንወዳለን።
አልነጃሽ የመላ የሀገራችን ህዝብ ቅርስ መሆኑ እየታወቀ የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ እንደሆነ በማድረግ የተለመደ ሆኖም ያልተገባ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ከማንም ወገን የሚደረግ እንቅስቃሴ ተገቢነት የሌለውና በአፋጣኝ ሊቆም እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በአልነጃሽ መስጅድ ላይ በደረሰው ጥቃት እጅጉን ማዘኑን እየገለፀ በተለይ ለሕዝበ ሙስሊሙ ወገናችን አጋርነቱን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

ታኅሣሥ 24 ቀን 2013 ዓ.ም

ሸዋ ፥ አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ!

የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
TUBE አብን ቱዩብ
https://www.youtube.com/channel/UCFgxM206ypqgQa8Kd_NWSww

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
https://t.me/NaMAVoice

Struggles and strives for the realization of wholistic, strategic and sustainable benefits, rights and interests of the Amhara.

27/10/2020

ሰበር መረጃ!
***
ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውንና እየተፈፀመ ያለውን ተከታታይ የዘር ፍጅት ለማውገዝ ጥቅምት 18/2013 በአማራ ክልል እንዲሁም ጥቅምት 22/2013 በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፎችን መጥራቱ ይታወሳል።

የአብን ከፍተኛ አመራሮችን ስለሰልፉ ዝርዝር ሁኔታዎች በዋና ጽ/ቤቱ እየመከሩ ባሉበት ወሳኝ ሰዓት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከበባ በመፈፀም መግባትና መውጣትም አትችሉም የሚል አፈና በመግባቱ የታቀደውን ሰልፍ በተቋማዊ ማዕከላዊነት ለመምራት እና ለሰልፉ የተዘጋጁ ሎጂስቲኮችን ለማንቀሳቀስም ሆነ ሰልፉን ለመምራት ስራ አስፈፃሚው ወደ ክፍለ ሀገር እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግረናል።

በዚህ የተነሳም አብን የጠራውን ሰልፍ በኃላፊነት መምራት የማይችል መሆኑን የድርጅታችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ሕዝባችን እንድታውቁት እንፈልጋለን።

መንግስት አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን የወጣ አምባገነንነት ውስጥ በመግባቱ በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው የትግል አካሄዶችን በተመለከተ የምናሳውቅ መሆኑንም ጨምረን እናሳውቃለን።

21/09/2020

በወቅታዊ ጉዳዬች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ፤
*
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መስከረም 9 እና 10 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሕዝባችንን ባጋጠሙት ወቅታዊ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።

1/ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕዝባችን ላይ የተፈፀመውን የዘር ጥቃት በተመለከተ፦

አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ማንነትን መሰረት አድርገው የተፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ተጨባጭ መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። በዚህም ከ160 በላይ ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተጨፈጨፉ ተገንዝቧል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራው ሕዝብ ጥንተ እርስቱን ተነጥቆ፣ ሰብዓዊና ዜግነታዊ መብቱ ተገፎ ለሦስት አሰርት ዓመታት ለዝርፊያ፣ ለመፈናቀል እና ለተደጋጋሚ የዘር ፍጅት የተጋለጠበት ነው፡፡ በተለይም ‹‹ለውጥ›› እየተባለ በሚጠራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በክልሉ ውስጥ ባለው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረገው የዘር ማፅዳትና ሰብዓዊ ጥቃት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

ንቅናቄያችን ልክ ከሰኔ 22 እስከ 24 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአማራው ሕዝብ ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ እንደገለገፀው ሁሉ በቤንሻንጉል ክልል የተፈፀመው ጥቃት ተራ የማኅበረሰቦች ግጭት ወይም የሽፍቶች ድርጊት ውጤት ሳይሆን በአማራ-ጠል ትርክት ላይ የተመሰረተ፣ ስልታዊ የሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል፡፡

በዚህ አሰቃቂ ጥቃት የትኅነግ ተቀጥላ የሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የቤንሻንጉል ክልል መንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ የአማራ ሕዝብንና የአገሪቱን ሰላም ለማሳጣት የሚታትሩ ባዕዳንና ውስጣዊ ኃይሎች ያሰማሯቸው የሽብር ቡድኖች እጃቸው እንዳለበት አብን ያምናል።

የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለተከታታይ ቀናት ሕዝባችንን(አማራ/አገው) በማንነታቸው እየመረጡ በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በኃይል አሰባስበው ለጅምላ ጭፍጨፋ ሲያዘጋጁ የክልሉ መንግሥት መረጃ እና ጥሪ እየቀረበለት ባለመድረሱ፤ የፌዴራል መንግሥቱም ባለው የደኅንነት መረጃ ተመርኩዞ ጥቃቱን ለመከላከል ፈጥኖ እርምጃ ባለመውሰዱ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አብን በጥብቅ ያምናል፡፡

አብን በሕዝባችን ላይ ከእንግዲህ ማናቸውንም አይነት ማንነቱን መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊታገስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን እየገለፀ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትኄ ካልተበጀለት ጉዳዩ ከአማራው አልፎ ታላቅ ብሔራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ፦

ሀ. መሳሪያ የታጠቁ ገዳዮችን በመደገፍና እንዳላዩ በማለፍ ለጥቃቱ መዋቅራዊ ከለላ የሰጡና በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የዘር ማጥፋቱ ተባባሪ የሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤

ለ. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚኖረው ሕዝባችን አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ፣ በየአካባቢያቸው የፖሊስና የደኅንነት መዋቅሮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸው እንዲከበር፣ በማኅበረሰብም ደረጃ ደኅንነታቸውን የሚያስጠብቁበት አስቸኳይ መፍትኄ እንዲፈለግ፤

ሐ. የፌደራል መንግሥቱና ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በአማራው ሕዝብ ላይ በሚፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ላይ የያዘውን ዳተኝነት እንዲያቆምና ችግሩን ለመከላከልና ከመሰረቱ ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ፤

መ. የአማራ ብልፅግና ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ በሦሥት ወራት ውስጥ ብቻ ሁለት እጅግ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ወንጀሉን በስሙ ከመጥራት ጀምሮ ለችግሩ ዘላቂ መፍትኄ በመፈለግ ረገድ ያሳየው አቅም እና ፍላጎት ከደረጃ በታች መሆኑና ከእንግዲህም ለችግሩ ዘላቂ መፍትኄ ከዚህ አካል ሊመጣ እንደማይችል ሕዝባችን በግልፅ እንዲገነዘበው፤

ሠ. ሕዝባችን በተከታታይ ለዘር ማጥፋት እና ዘር ማፅዳት ጥቃቶች የተጋለጠበት የቤንሻንጉል ክልል አማራው ፍጹም ሥነ-ሕዝባዊ አብላጫ እያለው ፖለቲካዊ ውክልና በማጣቱ የተነሳ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የክልሉ መዋቅር የነዋሪዎቹን መብቶች በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲከለስ ድርጅታችን አብን ያሳስባል፡፡

2/ በአማራ ክልል የደረሰውን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ በተመለከተ፦

በአማራ ክልል በዘንድሮ ክረምት ዝናብ ምክንያት በተፈጠሩ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች በአጠቃላይ በ6 ዞኖች በሚገኙ 36 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 164 ቀበሌዎች በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለፁ ጉዳቶች እንዳደረሱ ይታወቃል፡፡

በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ፣ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር በሊቦከምከም፣ ደራና ፎገራ ወረዳዎች በከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመጠቃታቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ፡፡

አብን እነዚህ በጎርፍና በመጥለቅለቅ የተፈናቀሉ ወገኖች በአስቸኳይ የእለት እርዳታ እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ እየገለፀ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ይጠይቃል፡፡

በጎርፉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሊነሱ በሚችሉ የወባ እና ሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች ሕዝቡ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡

ተጎጂዎች ሰብሎቻቸው እና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው በመሆኑ አፋጣኝ ድጋፍ እና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንዲከናወኑ፣ ለመጪው ዘመንም የሚያስፈልጋቸውን ሁለገብ እርዳታ የማዘጋጀት ስራ እንዲሁም ለዘለቄታው በየዓመቱ የክረምት ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ተመሳሳይ አደጋዎች ለመጠበቅ ዘላቂ መፍትኄ እንዲፈለግ ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም በአማራ ሕዝብ ታላቅ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ አቅጣጫውን በመሳቱ በሕዝባችን ላይ ሥርዓት እና መዋቅር ሰራሽ ጥቃቶቹ ስጋት ደቅነውበት እንደቀጠሉ አብን ይገነዘባል፡፡

እጅግ ራስ ወዳድ በሆነው ሰፊ የፖለቲካ ውቅር ውስጥ ጨካኞች እና ያልተገሩ ስብስቦች በአማራው ላይ ጥቃታቸውን ባስቀጠሉበት አግባብ፣ ለኩርፊያቸው እና ለደም ጥማታቸው አማራ ቋሚ ግብር ወይም ማስያዥያ የሚሆንበት የፖለቲካ ድባብ በትግላችን መገፈፍ ይኖርበታል።
በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ያሉ ተዋናዮችንና በቸልተኝነትና በሴራ ተባባሪ የሆኑ አካላትን ጭምር ለማጋለጥ እና በኃላፊነት እንዲጠየቁ ለማድረግ አብን እንደሚሰራ በአፅንኦት ለማስገንዘብ ይወዳል፡፡

በመጨረሻም አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለመግለፅ ለመላው የአማራ ሕዝብና ለሕዝባችን ወዳጆች ከነገ ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት በምናደርገው ጥቁር የመልበስ እና ተያያዥ የሐዘን መግለጫ ሥርዓቶች እንዲካፈሉ አብን የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ!

07/09/2020

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፤
****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ድርጅታዊ ኅልውና ባገኘባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የአማራ ህዝብ እውነተኛ ድምፅ በመሆን ህዝባችንን ከኅልውና ስጋት ለመታደግ፣ አንድነቱን ለማረጋገጥና ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ የተቀጣጠለውን ንቅናቄ ጠንካራና የማይቀለበስ መሰረት በማስያዝ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽዖ አድርጓል። የአማራውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጥያቄዎች ከፍ አድርጎ በመያዝና ለነፃነት፣ ለፍትኅና ለእኩልነት የሚደረገውን ትግል በመምራት ሕዝባዊ አመኔታን ለማትረፍ ችሏል፡፡

አብን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ርእይ የሰነቀ ንቅናቄ በመሆኑ በአገራዊ የሽግግር ሂደት ውስጥ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ አማራው በታላቅ መስእዋትነት ያስገኘው ለውጥ መስመሩን እንዳይስት፣ በትግላችን የተንበረከኩ ጠላቶች መልሰው እንዳያንሰራሩ፣ የፈነጠቀው የለውጥ ተስፋ እንዳይጨነግፍና ዳግም የአገራችንና የሕዝባችን ኅልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያላሰለሰ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጥረቶቻችን እንደሚጠበቀው ያህል ፍሬ ከማፍራት ይልቅ እየመከኑና የአገራዊው የፖለቲካ አውድ ከጊዜ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መምጣቱን የሚጠቁሙ በርካታ ምልክቶችን አስተውለናል፡፡ ንቅናቄያችን በዚህ ረገድ በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን ጽኑ አደጋ በሚያሳዩ ሦስት አበይት ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም በግልፅ ለማሳወቅ ይሻል፡፡

1. በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ በደሎችና የዘር ጥቃቶችን በተመለከተ፦
አብን በአገራችን በየትኛውም ክፍል፣ በማናቸውም ኃይልና በየትኛውም ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ የሽብርና የዘር ጥቃቶችን ያለማመንታት አውግዟል፡፡ የጋሞ ተወላጆች በቡራዩ በግፍ ሲጨፈጨፉ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ታፍሰው ወደ ጦር ካምፕ ሲጋዙ፣ የጌዴዖ ወገኖቻችን ሰብዓዊ እርዳታ ተነፍገው በርኃብ ሲረግፉ፣ ቤተ እምነቶች በእሳት ሲጋዩና አማኞች በጭካኔ ሲታረዱ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ በማሰማት ዜጎች ከጥቃት እንዲጠበቁና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩ ጥረት አድርገናል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ የተከሰቱትን ማንነትና እምነት ተኮር የዘር ማፅዳት፣ የዘር ፍጅትና ሰብዓዊ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለማስቆም ሰፊና ያላሰለሰ ትግል አድርገናል፡፡ ዜጎች በአማራነታቸው ተመርጠው ቤታቸው ሲፈርስና ሲፈናቀሉ፣ አማራ ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በዘር ጥቃት ተገደው ሲለቁና እገታ ሲፈፀምባቸው፣ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች በሚኖረው ሕዝባችን ላይ የዘር ማጽዳትና ሰብዓዊ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ከማውገዝና ማዕከላዊና ክልላዊ መንግሥታት ጥቃቶቹን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ግፊት ከማድረግ ባለፈ አደጋውን አስቀድሞ መከላከልና ማስቀረት በሚቻልበት መንገድ ላይ ሰፊና የተቀናጁ ጥረቶችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡

በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን ካደረጋቸው በርካታ ጥረቶች መካከል ለአብነት በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የሽብር ኃይሎች ማንነት ተኮርና በተለይም አማራውን ዒላማ ያደረጉ የዘር ጥቃቶች ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ከሁኔታዎች ጥናት በመተንበይ ለዚህ ማዕከላዊ መንግስቱ ልዩ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ በአካል ለአገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች ከማስረዳት ባለፈ በመግለጫ ጭምር በአንክሮ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

1.1. ከሰኔ 29 - ሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት፦

መንግሥት ተቀዳሚ የሆነውን ሰላምና ደኅንነት የማሰከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ባለመቻሉ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሽፋን በማድረግ ጽንፈኛ ኃይሎች ጥምረት ፈጥረውና ተዘጋጅተው በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ በዋነኝነት በአማሮች ላይ፣ በተጓዳኝም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ከሰኔ 29 ሌሊት እስከ ሐምሌ 1፣2012 ዓ.ም ድረስ በሽፋኑም ባስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትም እስከዛሬ ከታየው እጅግ ሰፊና አሰቃቂ የዘር ጥቃት ፈፅመዋል፡፡
አብን ይህን መረን የለቀቀ የዘር ማጥፋት ድርጊት በወቅቱ ከማውገዝ ባሻገር ጭፍጨፋው በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የጥናት ቡድን ልኮ በደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ላይ ዝርዝር መረጃዎችን በማሰባሰብና በማጠናቀር ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ሰነዱ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው የአገር ውስጥና ዓለማቀፍ አካላት በተለይም ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ፣ ለሰብአዊ መብት ተቋማትና ለአማራ አደረጃጀቶች እየተሰራጨ ሲሆን ፣ ንቅናቄያችን የዘር ፍጅቱ እውቅናና ትኩረት እንዲያገኝና ፍትህ እንዲረጋገጥ ቀጣይ እርምጃዎችን የሚወስድ ይሆናል፡፡

ሀ. የጥፋቱ አድማስ፦

ንቅናቄያችን ያደረገው ጥናት በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል ከተፈፀመው ሰፊ የዘር ጥቃት ውስጥ በስድስት ዞኖች በሚገኙ በ26 ከተሞችና አካባቢዎች የደረሰውን ያካትታል፡፡ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ደብረዘይት፣ ናዝሬት፣ መተሐራ፣ ዝዋይ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ቡልቡላ፣ መቂ ከተሞችን፤ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ አሳሳ፣ ዶዶላ ከተሞችን፤ በምሥራቅ ሃረርጌ ዞን ሃረማያ፣ ባቴ፣ ከምቦልቻ፣ ጉርሱም ከተሞችን፤ በሃረማያ ወረዳ ኦዳ በሊናና መልካ ገመቹ አካባቢዎችን፤ በጃርሶ ወረዳ አሌ ከተማን፣ ሚደጋ ቶላ ወረዳን፤ በባቢሌ ወረዳ የተለያዩ ስፍራዎችን፤ እንዲሁም በሃረሪ ክልል ሃረር ከተማን፤ በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ጭሮ ወይም አሰበ ተፈሪ፣ ሚኤሶ፣ አሰቦት ከተሞችና አካባቢዎችን፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን በተለይም ወሊሶ፤ በጅማ ዞን በጅማ ከተማ የደረሱትን የዘር ጥቃቶች ያካትታል፡፡

በጥቃቱ ከወደመው ኃብትና ንብረት መካከል 378 መኖሪያ ቤቶች፣ 111 ከብቶችና በርካታ የእርሻ ማሳዎች፣ የእህልና የሸቀጣሸቀጥ ክምችቶች፤ ከ300 በላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶችና ህንፃዎች፣ 189 ሆቴሎችና ፔንሲዮኖች፣ 5 ትምህርት ቤቶች፣ 15 መድሃኒት ቤቶችና የህክምና ተቋማት፣ 8 ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት፣ 117 የተለያዩ ተሸከርካሪዎች ተዘርፈዋል፤ ተሰባብረዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናት፣ የእምነት መገልገያዎችና ታሪካዊ ቅርሶች ሳይቀር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። በተፈፀመው እጅግ ከፍተኛ ጥቃት በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ኃብትና ንብረት ወድሟል፡፡

አብን በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ባጠናቀረው ዘገባ ግኝት መሰረት ከሰኔ 29 እስከ ሃምሌ 1/2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው ጥቃት ዓለምአቀፍ የዘር ማጥፋት መስፈርቶችን የሚያሟላና የማያሻማ የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል፡፡

ጥቃቱ በዘርና በእምነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ‹‹ነፍጠኛ›› እና ‹‹የነፍጠኛ ኃይማኖት›› በሚል የዘር ፍጅት መለያ በዋነኝነት በተጠቀሱት ዞኖች የሚኖሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮችን ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ ሙስሊም አማሮችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ኦሮሞዎችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ለጥቃት ተዳርገዋል፡፡
በዚህ የዘር ማጥፋት ጥቃት ከ200 በላይ አማሮች በአሰቃቂ ሁኔታ በሜንጫ፣ በዱላና በድንጋይ እየተጨፈጨፉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የጥቃቱ ሰለባዎች ከቀላል እስከ ፅኑ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በጥቂቱ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ወገኖችም አስቸኳይ የእለት እርዳታ ፈላጊ ሆነው ሜዳ ላይ ተጥለዋል፡፡

የአማሮች ሀብትና ንብረቶች እየተመረጡ በመውደማቸው ጥቃቱ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሆን ተብሎ የህይወት ዋስትና እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ችግሩ በነዚህ አካባቢዎች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በመላው ኦሮሚያ የሚኖሩ ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ አማሮችና ኦርቶዶክስ አማኞችን ለከፍተኛ የኅልውና ስጋትና ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት ዳርጓቸዋል፡፡

ለ. የጥፋቱ ተዋንያን፦

በሁሉም አካባቢዎች ጥቃቱን በተቀናጀ ሁኔታ በመምራት፣ በማስተባበርና በመፈፀም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ በተለይ በኦሮሞ ፅንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ሳይቀር ‹‹ቄሮ›› በሚል ስም የተደራጁ ወጣቶች ዋነኛ የጥቃት ኃይሎች ነበሩ፡፡

እነዚህ ቡድኖች ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው አቅራቢያ ከተማ ወይም ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ እየተሰማሩ የሚያጠቁ ፣ በከተማው የሚገኙ ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን ቤቶችና ንብረቶችን ዝርዝር የያዙ ጠቋሚዎች በቅንጅት የሚሰሩበት ነው፡፡ ለንብረቶች ማቃጠያ ቤንዚንና መሰል ግብአቶችንም የሚያቀርቡ ነበሩበት፡፡

በተለያዩ ደረጃ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር አመራሮችና አባላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጥቃቱ ከመሳተፋቸውም በላይ ጭፍጨፋውን ለማስቆም ፍላጎት አጥተው ቆመው መመልከታቸውንም ከፍጅቱ የተረፉ እማኞች አስረድተዋል፡፡ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት አመራሮችም እንደ ሻሸመኔና አርሲ ነገሌ ባሉ አካባቢዎች ለቀረበላቸው የድረሱልን ጥያቄ ‹‹ከበላይ ትዕዛዝ አልተሰጠንም›› በሚል ለእርዳታ አልተገኙም፡፡

የዘር ፍጅቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ወንጀሉን በስሙ በመጥራት ወንጀለኞችን ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ ድርጊቱን ተራ ግጭት በማስመል ወደ ማስተባበል ገብተዋል፡፡ ከዘር ፍጅቱ የተረፉ ተጠቂ ወገኖችንም በተገቢው ሁኔታ በማቋቋም ረገድ ዳተኝነት ይስተዋላል፡፡

1.2. የአብን አቋም፦

በአጠቃላይ አብን በጥናቱ ባረጋገጠው መሰረት በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት ተገቢውን ትኩረት ያለማግኘቱና ችግሩን በአጭር ጊዜም ይሁን በዘለቄታ ለመፍታት የሚታየው ዳተኝነት ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ ስለሆነም፦

ሀ) የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት መሆኑ ታምኖበት በስሙ እንዲጠራና ለተፈፀመው ወንጀልም ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠየቅ፤

ለ) መንግሥት የተፈፀመውን የዘር ፍጅት የሚያጣራና የሚመረምር ልዩ የምርመራ ኮሚሽንና አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት እንዲያቋቁምና ወንጀለኞች የሚዳኙበት ልዩ ችሎት እንዲሰይም፤

ሐ) መንግሥት በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀል የሚዘክር ቋሚ መታሰቢያ እንዲያቆም፤

መ) ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰቦችና ህዝቦች መካከል የእርቅና የመግባባት ስራዎች እንዲጀመሩ ፤

ሠ) የኦሮሚያ ክልልም በክልሉ ለሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ማህበረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው የሚከበሩበት ዋስትና እንዲሰጥ ፤

ረ) መንግሥት የዘር ፍጅቱን በመዘገባቸው ምክንያት ያሰራቸውን የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቅ አብን ይጠይቃል፡፡

2. በአዲስ አበባ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና ብክነቶችን በተመለከተ፦

ፓርቲያችን አብን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል መንግስቱ በከተማዋ ውስጥ የሚፈፅሙትን ወንጀሎች ፣ ሙስናና ብክነቶች የሚመረምር ቡድን በማቋቋም ሰፊ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጥናት የተገኘ መረጃን መሰረት በማድረግ በከተማዋ ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ ተቋማትን በአንድ ብሔር ተወላጆች የመሙላት፣ ሕገ-ወጥ የመታወቂያ እደላና በርካታ ተያያዥ ወንጀሎች እንደተፈፀሙ አረጋግጧል፡፡ ይህም በተለይ ከሰኔ 2011 ወዲህ እጅግ የተባባሰ እንደነበር ተገንዝቧል፡፡

2.1. ሕገ-ወጥ ወረራ፣ ሰፈራና ማፈናቀል
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአንጡራ ሃብታቸው ያቆሙት ጎጇቸውና ድርጅቶቻቸው ያለርህራሄና ያለሕግ አግባብ የሚፈርሱባትና ዜጎች ሜዳ ላይ የሚወረወሩበት፤ ከፊሎች ደግሞ በዘር፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በጥቅም ትስስር በገፍ መሬት የሚቸራቸው፤ የከተማዋ ነዋሪ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ የገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት በልዩ መብት የሚታደላቸው ከተማ ሆናለች፡፡

አብን በከተማዋ የሚፈፅሙትን ሕገወጥነቶች ከማውገዝና በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከማጋለጥ ባሻገር አቅም በፈቀደ መጠን የሰብአዊ ርዳታዎችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ለመታደግ ጥረት አድርጓል፡፡ መላው ሕዝባችን በተለይም ለህዝብና ለአገር ጥቅሞች ፣ መብቶችና ፍላጎቶች ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከንቅናቄያችን አገርን የማዳን ታሪካዊ ጥሪ ጎን እንዲቆሙ ወትውተናል፡፡

ከዚህም ባለፈ ንቅናቄያችን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ በማጥናት ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ አቤት ብሏል፡፡ ታኅሣሥ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመንግስት በመገኘት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋር እስከመወያየት ደርሷል፡፡ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮች መኖራቸውን በማመን አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚበጅላቸው ቃል ቢገቡም አንዳችም ሳይደረግ አሁን ካለንበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡

ሰለዚህም አብን ይህ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ፅኑ ብሔራዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ፦

ሀ) አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመውን ሁሉንአቀፍ ወረራ በተመለከተ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ አንድ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም፤

ለ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን የመሬት አስተዳደርና ማስተላለፍ፣ የመታወቂያ አወጣጥ፣ የቅጥርና ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲያጣራ/ኦዲት እንዲደረግ፤

ሐ) በኦዲት ግኝቱ በሚመጣው መሰረት ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ሁሉም አካላት ለፍትኅ እንዲቀርቡ፤

መ) በኦዲት ግኝቱ ለተለዩ ጉድለቶች አጣሪ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ መሰረት የማስተካከያ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፤ እንዲሁም

ሠ) ምርጫ ተካሂዶ ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ የከተማ አስተዳደር ምክርቤትና ካቢኔ እስኪዋቀር ድረስ አሁን ያለው የሽግግር አስተዳደር ዘላቂ ውጤት ሊኖራቸው ከሚችሉ ውሳኔዎች እንዲታቀብ፤ አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

2.2. ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፦

ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤትና በከተማ አስተዳደሩም በኩል የሚሰሩ ዋና ዋና 15 ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ስለፕሮጀክቶቹ ዝርዝር መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል፡፡

በዚህም መሰረት በጀታቸው/ወጪያቸው የታወቁ ፕሮጀክቶች የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ 5.737 ቢሊዮን ዶላር (ወቅታዊ ምንዛሪው ከ212 ቢሊዮን ብር በላይ) እና ተጨማሪ 59.2 ቢሊዮን ብር በአንድ ላይ ወደ 271 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ በጀታቸው ካልታወቁ ጋር ሲደመር ከዚህ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

አዲስ አበባ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንድትሆን የሚደረገውን መንግስታዊ እንቅስቃሴ በመርኅ ደረጃ አብን ይደግፋል፡፡

ይሁንና የሜጋ ፕሮጀክቶቹ እጅግ የተጋነነ ወጭ የሚወጡባቸው በመሆናቸው (White Elephant Projects)፤ ይኸው ከፍተኛ በጀት አገራችን በብድርና እርዳታ የምታገኘው በመሆኑ፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር የቅደም ተከተል ችግር ያለባቸው መሆናቸው ፤ ከአዋጭነት፣ ባለድርሻዎችን ከማሳተፍ፣ ከዲዛይንና ግንባታ አካሄድ፣ ከብክነትና ሙስናን ከማስቀረት፣ በግልጽ ጨረታ የግንባታ ኮንትራክተሮችን ከመለየት እንዲሁም በየጊዜው ስለፕሮጀክቶቹ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ከመስጠት አንፃር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆናቸውን አብን ያምናል፡፡

መንግስት ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ግልጽነት ባልተሞላበትና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ባላስቀመጠ መልኩ ማዋሉ ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡ ስለሆነም፦

ሀ) መንግስት ስለፕሮጀክቶቹ ለህዝብ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ፤

ለ) በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአገራችን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተደቆሰ በመሆኑ ቀውሱ አገርን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ማኅበራዊ ቀውስ ከማደጉ በፊት አስፈላጊ የኢኮኖሚ ድጋፍ ማእቀፎችን ቀርፆ ወደ ሥራ እንዲገባ፤

ሐ) የተጋነኑና አንገብጋቢ ያልሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ በጀቱን የነፍስ አድን ርዳታ ለሚፈልጉ ወደ 18 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንዲያውለው፤

መ) በአገራችን ያለው የሥራ አጥነት በአስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘቱን በማጤን መንግስት ጊዜውንና አቅሙን ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያውል አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

3. ብሔራዊ ውይይትና መግባባትን በተመለከተ፦

አብን የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ በምርጫ ብቻ እልባት ያገኛል የሚል አቋም የለውም፡፡ ስለዚህም ከምርጫ በፊት እንደ አገር መደማመጥ፣ መከባበርና መተማመን እንዲቻልና አሁን የተፈጠረው የሽግግር ጊዜም እንዳለፉት ዘመናት እድሎች እንዳይከሽፍ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የሰለጠነ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር እንዲዘጋጅ፤ ለዚህም ግልጽ ማእቀፍ እንዲኖርና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የብሔራዊ ውይይት መድረክ እንዲከፈት ወትውቷል፡፡

መንግሥት ለእውነተኛ የፖለቲካ ድርድርና ብሄራዊ መግባባት ዳተኝነት በማሳየቱ ምክንያት ፅንፈኛ ኃይሎች አገር አፍራሽ ድርጊታቸውን በማናለብኝነት እንዲቀጥሉ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ትሕነግ የሚዘጋጅበት ሕገ-ወጥ ምርጫ በወረራ በተያዙ የአማራ መሬቶች በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የሚኖረው ህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ፅኑ አፈናና ግፍ መንግሥት እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት ዘግይቶም ቢሆን የወሰነውን ውሳኔ የፌዴራል መንግሥቱ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርግና ትህነግ በህገወጥ ምርጫ በወልቃይትና ራያ ህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ሰብአዊ ቀውስ እንዲያስቆም አብን ጥሪ ያቀርባል፡፡

በተጨማሪም ፡-

ሀ) አገርን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማመን መላው የፖለቲካ ኃይሎች የአገራችን አደገኛ ወቅታዊ ሁኔታ ባጤነ መልኩ በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ፤

ለ) መንግስት በውል የታወቀና የታቀደ ሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር የማስተባበርና የማመቻቸት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤

ሐ) ሁሉም ዜጎች በተለይም ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ምኁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ባለኃብቶች ለሚደረገው ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ውጤታማነት የየድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው፤

መ) የዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡ የሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ሂደት እንዲደግፍና መንግስት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጫና እንዲፈጥር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ታሪካዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡


‹‹አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!››

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)፤

አዲስ አበባ፣ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!

ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም

ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) አባላትና ደጋፊዎች !!***የአማራ ሕዝብ ኹለንተናዊ ትግል አምጦ የወለደው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሕዝባችን የተጋረጠበትን የኅልዉና አደጋ በመቀልበስ፤ ...
07/09/2020

ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) አባላትና ደጋፊዎች !!
***
የአማራ ሕዝብ ኹለንተናዊ ትግል አምጦ የወለደው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሕዝባችን የተጋረጠበትን የኅልዉና አደጋ በመቀልበስ፤ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በእኩልነትና በፍትኃዊነት የሚኖርባትን አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያ እውን የማድረግን መንታ ኃላፊነት ተሸክሞ በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ብዙ የተመዘገቡ አባላትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን አፍርቷል፡፡

ንቅናቄያችን በመላ ሀገሪቱ በርካታ ቢሮዎችን ከፍቶ ሕዝባችንን እያነቃና እያደራጀ ይገኛል፡፡ በሕዝባችን የተጋረጠው አደጋ ዘርፈ ብዙና ሥርዓትና መዋቅር ሰራሽ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተጠናከረ አቅምን ይጠይቃል።

የአብንን የፋይናንስ አቅም የተጠናከረ የማድረግ ዓላማ ያለው "ጳጉሜን ለአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)!" በሚል ከጳጉሜ 1-5 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደው ዘመቻ የአብን መዋቅር ባለባቸው አካባቢዎች በሙሉ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚህ ዘመቻ አባላት ወርሃዊ መዋጯቸውን ይከፍላሉ፤ የንቅናቄያችን ደጋፊዎችና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አብንን በቀጥታ ወይም በከፈታቸው የባንክ አካውንቶች በገንዘብ በመደገፍ በትግሉ ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳርፋሉ። በተጨማሪም በዘመቻው ዋናውን፣ የዞን እና የወረዳ የአብን ጽ/ቤቶችን በግብዓት የመደገፍ ተግባራት ይከናወናሉ።።

በደብብ ጎንደር ዞን ለምትገኙ ደጋፊዎቻቸን እና አባላቶቻችን በሁሉም ወረዳ ፅ/ቤቶችና በዞኑ ማስተባበሪያ ቢሮ በአካል በመገኘት ወይም በተከፈቱት የባንክ አካውንት ማገዝ እንደምትችሉ እንገልፃለን ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የደቡብ ጎንደር ዞን ማስተባበርያ ፅ/ቤትን በገንዘብ ለመደገፍ፦

★የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ፦
የሒሳብ/ቁ 1000340274974

★ በአባይ ባንክ፦
የአካ/ቁ - 2131111149195014

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

13/08/2020

የሰኔ 23 2012 ዓ.ም. በባቱ፣ሻሸመኔ እና አካባቢው የነበሩ ጥቃቶችን ተከትሎ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የተጠናቀረ ሪፖርት

ቁ.047/SMNE/20
4/12/12 ዓ.ም.

መግቢያ
አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሌሊቱን እና በማግስቱ 23/10/12 የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ተከስተው በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
ከኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና አርቲስቶች ሕብረት ጋር ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተርና ቡድናቸው በሐምሌ 27 እና 28 2012 ዓ.ም.በነበሩት ቀናት በባቱ እና ሻሸመኔ ከተሞች እና አካባቢ በተወሰነ መልኩ ተዘዋውረን የደረሰውን ጉዳት ለማየት ሙከራ አድርገናል፡፡
ባቱ ከተማ
አብነት ገለታው
እኛ አግኝተን ያናገርናችው ሶስት ወንድማማቾች ባቱ ከተማ ዘመድ ቤት ሀዘን ተቀምጠው ቢሆንም አምስት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማለትም አባታቸውን፡ እናታቸውን፡ ወንድም፣ እህታቸውን እና የአጎታቸውን ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ያሳጣቸው ድርጊት ግን የተፈጸመው ከባቱ 7ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው አዳሚ ቱሉ ከተማ እንደነበር ነግረውናል፡፡
የሟቾች ስም ዝርዝር

አቶ ገለታው አውላቸው (አባት) ዕድሜ 60

ወ/ሮ ፀሀይ መንግስቴ (እናት) ዕድሜ 47

ወጣት ሳሙኤል ገለታው (ወንድም) ዕድሜ 24

ወጣት ነፃነት ገለታው (እህት) እድሜዋ 22

ወጣት ዋሴ አግዜ (የአጎት ልጅ) እድሜ 21 ናቸው

ተጎጂዎቹ ጥቃቱ የደረሰባቸው በእምነታቸውና በማንነታቸው እንደሆነ የሚያምኑ ሲሆን ቤተሰቦቻቸውን ያጡት በድብቅ ሳይሆን ፖሊስ ባለበት ሀገር በቀን ቤታቸው ተሰብሮ ተገንጥሎ መስኮት በመሰባበር ገብተው በግፍ በአሰቃቂ ሁኔታ ቆራርጠው ነው የገደሏቸው ብለውናል፡፡

“ መግደላቸው ሳያንስ ሙሉ ቀን ከጠዋት 3፡30 እስከ 10 ሰዓት ድረስ ሳይሸሹ ፤ ሌሎች ልጆችም አሉ ሲመጡ እንገድላለን ብለው እየጠበቁን ስለነበር እኛም ሄደን ሬሳ እንኳን ማንሳት አልቻልንም ነበር፡፡ አዱኛ ንጉሴ የተባለ ደግ የአባታችን ጓደኛ ነው ፡በዚያ አስቸጋሪ ሰዓት ሄዶ ሆስፒታል በመውሰድ የሬሣ ሣጥን በመግዛት ያነሳቸው፡፡ ቤተሰቦቻችን ስራ ከመስራትና ለአካባቢው መልካም ከማድረግ ውጪ ምንም ነገር ውስጥ የሌሉ ነበሩ፡፡ለተከራዮቻቸው እንኳ እንደ አባትና እናት ደግሰው የሚድሩ የሌሎችን ሰዎች ልጆች እንኳ ያሳደጉ ያስተማሩ ነበሩ፡፡ በማያውቁት ተገደሉብኝ ” ብሏል ልጃቸው አብነት ገለታው፡፡
ሚክያስ ገለታው
ሚክያስ እሱም አምስት ቤተሰቦችን የተነጠቀ የአብነት ወንድም ሲሆን ሁኔታውን እንዲህ ገልጾልናል፡፡
“ ቤተሰቦቼን በቀን በፋስ በቆንጨራ ቁርጥርጥ አድርገው ነው የገደሉብኝ ሬሳ እንኳ ማንሳት አልተቻለም፡፡ ምንድነው ፖሊስ የለውም እንዴ ሀገሩ? ፖሊስ ምንድን ነው የሚሰራው? አባታችን የሀገር ሽማግሌ ነበር፡፡ በማግስቱ የኛ ቤተሰቦች የቀብር ቦታ አዳሚ ቱሉ ማርያም ቤ/ክርስትያን ያዘጋጁት ቦታ ነበር ለመቅበር ስንሄድ አልተቻለም፡፡ ከዚያ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስትያን ስንሄድ ደግሞ ጭራሽ ነፍጠኛ እዚህ አይቀበርም ብለው ከለከሉ ከዚያ መከላከያ መጥቶ ነው የአባታችን ወዳጅ የቤተሰቡን የመቃብር ቦታ ሰጥቶን ለመቅበር እንኳን የቻልነው፡፡ የኔስ ቤተሰቦች አልቀዋል፡፡የሌላውስ የመኖር ዋስትና ምንድን ነው? እነዚህ ገዳዮች የኛን ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ክርስትያን ሳይሉ የመላውን ኢትዮጵያውያን እናት አባት እህት ወንድም ና ዘመድ ነው የገደሉት፡፡ መንግስት እነዚህን ገዳዮች በአደባባይ ያውጣልን፡፡ እኛም ቤተሰቦቻችን ጀምረውት የነበረውን በጎ ስራ ሁሉ እናስቀጥላለን፡፡ማረድ የፈለገ መጥቶ ማረድ ይችላል ” ብሎናል፡፡

መምህር አስናቀ ደቻሳ
በባቱ ከተማ በቤ/ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰባሰቡትን ንብረታቸው የተጠቃባቸውን ወገኖች በጎበኘንበት ወቅት ስለሁኔታው አጠር ያለ መግለጫ የሰጡን በሙያቸው መምህር የሆኑት አቶ አስናቀ ደቻሳ እንደገለፁልን፡
“ወደ 218 ገደማ ሆቴሎች የንግድ ቦታዎች ዝቅተኛ ተዳዳሪ ንብረቶች ፋርማሲ ሳይቀር ተቃጥለዋል ወድሟል፡፡ ወደ 30 የሚሆኑ የንግድና የቤት ተሸከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡ ወደ 52 የሚሆኑ የንግድ ስፍራዎች ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ተጎጂዎችንም ማህበረሰቡ ተቀብሎ በየሰው ቤት ይገኛሉ፡፡የችግራቸው መጠን ቢለያይም የሚቀምሱት የሚለብሱት የሌላቸው ወገኖችም ግን አሉበት፡፡ የምግብ፣የአልባሳት እና መልሶ መቋቋም የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብለውናል፡፡

አቶ መንበሩ አድገህ
የ 80 ዓመቱ አቶ መንበሩ ፡በባቱ ፣መቂና ሞጆ ከተሞች ላይ በመንግስት መ/ቤት ለ42 ዓመታት አገልግለው ጡረታ ከወጡ 20 ዓመት እንደሞላቸው የሚናገሩት የዕድሜ ባለፀጋ በ23/10/12 በባቱ መኖርያ ቤታቸው ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲናገሩ
“ብዙ ሆነው መጡ ግባ ብለው አስገብተው አንድ ሁለቱ ጭንቅላቴን መቱኝ ሌሎቹ ተው ብለው ሌላ ሰው ቤት አስገብተው ዘጉብኝ ከዚያ ቤቴና ንብረቴን እሳት አነደዱበት፡፡ሳገለግል የኖርኩት ሁሉንም ህዝብ ነበር፡፡ እኔም አብሬ እሞታለሁ ምን ቀረኝ ብዬ እሳት ልገባ፡መከላከያዎች ናቸው ያተረፉኝ፡፡”

ሻሸመኔ


ሻሸመኔ ከተማዋን ተዘዋውረን እንደተመለከትናት መጠነ ሰፊ የንብረት ጉዳት ደርሶባታል፡፡ህይወታቸውንም ያጡ ወገኖች አሉ፡፡
አቶ እንዳልካቸው ጥጋቡ
አቶ እንዳልካቸው መኖርያ ቤት ስንደርስ ሀዘን ላይ ነው ያገኘናቸው፡፡ ከሟች ባለቤታቸው ጋር በኦርቶዶክስ ክርስትና መሰረት ቆርበው እንደነበር እና ለ22 ዓመታት በትዳር ቆይተው እንደነበር ነግረውናል፡፡ በትዳራቸውም ኤፍራታ የተባለች የ13 ዓመት ሴት ልጅ እና ሶፎንያስ የተባለ የ11 ዓመት ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡
“ በ23/10/12ዓ.ም. ብዙ የማናውቃቸው ሰዎች ወደ ቤታችን በመምጣት ክፈት አንተ ነፍጠኛ አማራ፡ የነፍጠኛ ቤት እያሉ በሩን መደብደብ ጀመሩ በሩ ጠንካራ ስለነበር በገጀራ 3 ቦታ ቀደዱ ከዛም ሰው የሚገባበትን አነስተኛ ተካፋች በመፍለጫ ላሜራውን ቀደዱ ዋናውን በር ቤንዚን አርከፍክፈው በሩን እያቃጠሉ ገንጥለው ገቡ፡፡ ባለቤቴ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው ወ/ሮ ሜሮን ተስፋዬ፤ እንዲሁም ሁለት ልጆቻቸው የ11 ዓመቱ ሶፎንያስ እንዳልካቸው እና እህቱ የ13 ዓመቷ ኤፍራታ እንዳልካቸው በቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ እኔ ላይ ጌጀራ ደግነው ባለቤቴን መሬት ላይ ጣሏት እግሯን ይዘው ጎተቷት፡፡ ልብሷን አስወልቀው እንገልሻለን የአማራ ልጅ አይወለድም የክርስቲያን ልጅ አይወለድም እያሉ ወደ አንገቷ እና ሆዷ አስጠግተው እየሳሉ ሲያስፈራሯት ስለእናት ብላችሁ እናት የላችሁም እያለች እየጮኸች ለመነቻቸው፡፡ አብረው ከነበሩት ሴቶች መካከል ግደላት ሰንጥቅና አሳየኝ የምትልም ነበረች፡፡ ይህ አሰቃቂ ሁኔታ ሲሆን ሁለት ልጆቿን ግራና ቀኝ አንበርክከው እነሱ ፊት ነበር፡፡ ይህ ድርጊት በግምት ከ40 ደቂቃ እስከ 1ሰዓት ያህል ቆይቷል በዚህ መሃከል ግን ባለቤቴ ሜሮን ራሷን ስታ ነበር፡፡ ልጆቼም እያለቀሱ ሶፎንያስም እናቴን እያለ ይጮህ ነበር እኔን ግደሉኝ እያለ ያለቅስ ነበር፡፡ በዚህ መሐል ከእነርሱ መካከል አንዱ በቃ በቃ እረፉ ይህን ማድረግ የለብንም ብሎ መናገር ጀመረ እርስ በራስ በኃይል ለመናቸው፡፡ ከውጭም ሌላ ሴት ቀሬ መጥታ እንዴት እንዲህ ታደርጋላችሁ ብላ ተናገረቻቸው፡፡ በዚህም ባለቤቴን ራስዋን በሳተችበት ትተው እኔን መሳርያ አምጣ አሉኝ፤ እንደሌለኝ ነገርኳቸው፡፡ ገንዘብ አምጣ አሉኝ እሺ ብዬ ወደ ካዝና ወስጃቸው ቁልፍ እስከማወጣ ድረስ መትተው ጣሉኝ ፡፡በመጥረብያና በብረት ካዝናውን ገንጥለው 480000(አራት መቶ ሰማንያ ሺህ ) ብር ወሰዱ፡፡ወርቅ አምጣ አሉኝ የቤቱን እቃ በሙሉ አውድመው ሄዱ” ብሎናል፡፡
ከዚያም ባለቤቱንና ልጆቹን ይዞ ወደ ሀዋሳ ለመሄድ መንገድ ዝግ ስለነበር ጎረቤት ለሁለት ቀን እንደቆየ መንገድ ሲከፈትም ሀዋሳ ሄዶ ጓደኛው ቤት አድረው በማግስቱ ታቦር የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል እንደወሰዳትና ሀኪሟ በዚህ ሁኔታ ሊረዷትና ኦፕራስዮንም ማድረግ እንደማይቻል ምክንያቱም በመጀመርያ በጣም መረጋጋትና ከጭንቀት መውጣት እንዳለባት ነግሮን ነበር፡፡
“ እሷ ግን እንቅልፍም የላት እንደጮኸች መጡብኝ አረዱኝ ልጄን ልጄን እንዳለች እንደባነነች፡ በ13/11/12 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ላይ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡ “ብሎናል፡፡
“ ልጆቼም ጤናቸውን አጥተዋል እየባነኑ ነው ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግስት ይፍረደኝ! የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ!የሐይማኖት አባቶች ፍረዱኝ! ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ፣የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርያት፣ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ወ/ሮ መዓዛ፡ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ እናት ናችሁ፤ ነፍሰ ጡር ላይ ጎራዴ? ይደረጋል? ስሜቱ እንዴት ነው? ስሜቱ ምን እንደሚመስል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረዱ “ ብሏል፡፡
* አቶ እንዳልካቸው ከሻሸመኔ ከተመለስን በኋላ በስልክ ባነጋገርነው ወቅት በከፍተኛ ሀዘን ተውጦ “እውነቱን ለህዝብ አሳውቁልኝ በተለያየ መንገድ ያላልኩት ነገር እየተባለ እየተነገረ እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ይህም በሐዘን ላይ ሐዘን ሆኖብኛል፡፡ ባለቤቴ ላይ የደረሰባት ነገር በራሱ አሰቃቂ ግፍ ነው፡፡ የ9ወር ነፍሰ ጡር መሬት ላይ ጥለው እግሯን ይዘው ጎትተው ልብሷን አስወልቀው አንገቷና ሆዷላይ አስጠግተው እየሳሉ እናርዳለን፡ እንገላለን የአማራ ልጅ አይወለድም ፡የክርስትያን ልጅ አይወለድም እያሉ ሁለት ልጆቿ ፊት ነው ይህ የተደረገው ብያለሁ፡፡ አረዷት በገጀራ ሰነጠቋት አላልኩም፡፡ ሀዋሳ ታቦር የእናቶች እና ሕፃናት ሆስፒታል ወስጃት ነበር፡፡ያረፈችው በ13/11/12 ነው፡፡ከዚህ በፊትም የኢሳት ጣብያ ጠይቀውኝ ይህንኑአስረድቻለሁ፡ በሀዘን ላይ ሀዘን አይጨምሩብኝ፡፡ ይህንን ለህዝብ አሳውቁልኝ፡፡ለራሴ ልጆቼ ከፍተኛ ጭንቀትና መባነን ላይ ናቸው፤ ነፍጠኛ ምን ማለት ነው? አማራ ምን ማለት ነው? እያሉኝ ግራ ተጋብቻለሁ፡ ቤት ውስጥ መተኛት አልቻሉም“ ብሎናል፡፡
አቶ ብዙአየሁ ጥጋቡ
የሶስት ወንድ ልጆች አባት ሲሆን የአቶ እንዳልካቸው ወንድም ነው፡፡ እሱም በቤቱ ከቤተሰቡ ጋር እያለ
“ ሀጫሉ መገደሉን ሌሊት ሰምተን ደነገጥን ከዛ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እየጮሁ ነፍጠኛ ነፍጠኛ ኦርቶዶክስ ኦርቶዶክስ እየተባለ ነፍጠኛን ግደል ነፍጠኛ አይኖርም እያሉ በሞተር እየጮሁ ነበር፡፡ ሌሊት 10 ሰዓት ጀምሮ ዝርፍያ ተጀመረ፡፡የኔንም ቤት ጠዋት 12፡05 ላይ መደብደብ ጀመሩ፡፡ በመሬት በቀዳዳ እያየኋቸው ነበር በበር ስር ዝቅ ብዬ እያየኋቸው ነበር በግምት መቶ ይሆናሉ ገጀራ፣መፍቻ፣ባለንቲኖ፣ነጭ ጋዝ ቤንዚን ይዘዋል፡፡ ከቤቴ ፊት ለፊት ያለው ውብሸት ሆቴል ገቡ፡፡የዚህን ጊዜ እኔ ልጆቼን ይዤ በጎረቤት አጥር ዘልዬ አመለጥን፡፡ ጓሮ ነገር ነበር፡ የእንሰት ተክል ያለበት እሱ ውስጥ ተደበኩኝ፡፡ ወደ 4፡25 ሲሆን ኮፍያ ሹራብ አድርጌ ወጣሁና ወደ ስራ ቦታዬ ጋ ለማየት ሔድኩ ብዙ ልጆች ቆመዋል፤ ፈርቼ ተመልሼ ገባሁ፡፡ ለ4፡40 አካባቢ ቤቴን የሚወስዱትን ወስደው እንዳለ በእሳት አነደዱት፡፡ ካዝና ውስጥ የነበረ 413000(አራት መቶ አስራ ሶስት ሺህ ) ብር እና 20 ግራም ወርቅ ወሰዱ፡፡ ለስራም ቅዳሜ በ 19/10/12 ብቻ የ1050000 (አንድ ሚልየን ሀምሳ ሺህ ) ብር ጎማ ነበር የገዛሁት ያ ሁሉ ንብረት ወደመ፡፡ቅድሚያ ልጆቼንና ቤተሰቤን ማትረፍ ስለነበረብኝ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር፡፡ እኔንም ሊገድሉ እየፈለጉኝ ነበር፡፡ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት እያቀያየርን ተደበቅን መከላከያ ከገባ በኋላ ፍለጋውም ረገበ በሌላ ቀን ልጆቼን እና ባለቤቴን ወደ ሃዋሳ ላኩዋቸው” ብሎናል፡፡
“ ይህ ሁሉ የሆነው ፖሊስም ልዩ ሀይልም እያለ ነው፡፡ ከሌሊት ጀምሮ እንደገና በቀን ሲፈጸም ፖሊስ ምን ያደርጋል? ካሁን በኋላስ ዋስትናችን ምንድን ነው? አልታዘዝንም ነበር የሚሉት፡፡ እኛ ምን አደረግን? “ ብሏል፡፡
ብዙአየሁ ቀጥሎ “ ሃሙስ በ25/10/12 ዓ.ም. ጎረቤት ፖሊስ ነበር የተቃጠለብህን ንብረት አስመዝግብ ብሎ ጠራኝ፡፡ አልመጣም ይቅርብኝ ስሜቴ ጥሩ አይደለም ስል፤ ግድ የለም ስትደርስ ደውልልኝ አለኝ፡፡ ስደርስ ወዴት ነህ አሉኝ ፖሊሶች አይ ተደውሎልኝ ነው አስመዝግብ ተብዬ ነው አልኳቸው፡፡ አንዱ አትገባም አለኝ፡፡ አሁን ተደውሎልኝ ነው ለምን አልገባም ስለው አንተ …(ስድብ)………ነፍጠኛ ብሎ በጥፊ መታኝ፡፡ሌሎችም ፖሊሶች መጡ በዱላ ቀጠቀጡኝ፡፡ አዛዡም እያየ ነው የተመታሁት ብሏል፡፡ ያስጣሉትም እንዴት ትመቱታላችሁ ንብረቱንም አጥቶ ብለው ሁለት በስም የጠቀሰልን ፖሊሶች እንደሆኑ ነግሮናል፡፡ ስወጣም የመታኝ ፖሊስ እዚች ሀገር ሰርተህ ትበላታለህ! ብሎ ዛተብኝ፡፡ ፖሊሶቹ ስምንት ወንዶች እና አንድ ሴት ነበሩ ብሎናል፡፡ይህ ሲሆን ጓደኞቼም ወንድሜም አይተዋል” ብሏል፡፡
ወ/ሮ ቆንጂት በላይ


የሟች ባለቤታቸው ስም አቶ ወንደሰን መኮንን
ወ/ሮ ቆንጂት ቤት ስንደርስ ሌላ አሳዛኝ ድርጊት እንደተፈፀመ ሰማን፡፡ ሟች ባለቤታቸው አቶ ወንድወሰን መኮንን
የ79 ዓመት ባለፀጋ እንደነበሩና በሻሸመኔ ከተማም ከ40 ዓመታት በላይ እንደኖሩ በ23/10/12 ዓ.ም. በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ ነግረውናል፡፡
“ታማሚ ነን፤ ስኳር፣ ግፊትና የነርቭም ችግር አለበት፡፡እኔም እንደዛው የልብ ሕመም እና ግፊት አለብኝ፡፡ በዕለቱ በራችን መደብደብ ጀመረ፤ ከዛ ዘለው ገቡ፡፡ ነይ ውጪ፡ ድርጅትሽን አቃጥለን ነው የመጣነው፡ ቤትሽንም እናቃጥላለን ሲሉኝ፡ ምን አደረኩ ብላቸው ሀጫሉ ሞቷል አሉኝ፡፡ ነፍሱን ይማረው፡ ታድያ እኔ ምን አደረኩ ብላቸው፡ ያንቺ ዘመዶች ናቸው የገደሉት አሉኝ፡፡ የትኛው ዘመዴ፡ ኧረ እኛ ሽማግሌዎች ነን ብዬ ለመንኳቸው፡፡ ጩቤ ፣አካፋ፣ ቆንጨራና ግንድ መፍለጫ ይዘዋል፡፡እግራቸው ላይ ወድቄ እየለመንኳቸው ውጪ ብለው አስወጡኝ፡፡ ሰዎች ጎረቤት አስገቡኝ፡፡ ባለቤቴን ይዘው አስረው አየጎተቱ አሰቃይተውት ኪሱን እየበረበሩ አንገቱ ላይ ገመድ አስገብተው እየጎተቱ ከቆዩ በኋላ አንገቱን አረዱት፡፡
አስከሬንም አንሰጥም ብለው ስንት ሰዓት ሙሉ ቆይተው ልጆቼንም ሊገድሉ ሲያባርሩ ዋሉ፡፡ እሱም በስቃይ ተቀበረ፡፡ “ ብለውናል፡፡
ይንጋልኝ ወንደሰን
የሟች አቶ ወንደሰን እና ወ/ሮ ቆንጂት ልጅ ሲሆን እሱም
“ ቤታችን ላይ ጥቃት እንደደረሰ ሰምተን ስንመጣ እኛንም ሊገድሉን በጌጀራና በቆንጨራ ነው ያሳደዱን ሮጠን በየጎረቤቱ እየተደበቅን ነው የተረፍነው፡፡ የአካባቢው እናቶች ሳይቀር ለምነዋቸዋል እነርሱንም እያነቁ እየገፈተሩ ነው የመለሷቸው፡፡ከ2-3 ለሚሆን ሰዓት ከተደበቅን በኋላ ፌደራል ፖሊስ አግኝተን ብንለምናቸው ራሱ እኛ አንገባም ራሳችሁን አስመልጡ ነበር ያሉን፡፡ ከዚያም የከተማው ፖሊስ መምርያ ሄደን ስንለምናቸው የተወሰኑት አንገራገሩ የተወሰኑት ደግሞ እያወቅናቸው እንዴት እንዲህ እናደርጋለን ብለው ወደ 30 የሚሆኑ ፖሊሶች ጋር ሄደን አስከሬን አንስተን ሆስፒታል አስገባን፡፡
አባቴ የታረደው ጠዋት 3፡30 አካባቢ ሳለ ሆኖ አስከሬን ማንሳት እንኳን ተከልክለን፡ አስከ 11፡30 ዝናብ ሁሉ እየዘነበበት ነው የቆየው፡ በጥቆማ ቅድመ ዝግጅት የነበረ በሚመስል መልኩ ቀጥታ እኛ ቤት ሲመጡ ለእናቴም ድርጅትሽን አቃጥለን ነው የመጣነው ብለዋታል፡፡ ሉሲ መኝታና ግሮሰሪ የሚባል ድርጅት ነበራት በእሳት ነዶ ወድሟል፡፡ ”
ወ/ሮ ስላስ አባዲ
ወ/ሮ ስላስ አባዲ ለ32 አመታት በሻሸመኔ ከተማ እንደኖሩና ከሶስት አመታት ወደዚህ የአይን ብርሀናቸውን እንዳጡ በ23/10/12 በነበረው ችግር ምክንያት ቤት ንብረታቸው እንደወደመ፣ የለበስኳትንም ልብስ ሰው ነው ያለበሰኝ ብለውናል፡፡
“ ክርስትያን ከሆናችሁ በክርስትያን አምላክ ሙስሊም ከሆናችሁ በሙስሊም አምላክ እያልኩ ለመንኳቸው እነርሱ ግን ቤቴን አቃጠሉት፡፡ “

ወ/ሮ መብሪት አያሌው
የማየት የተሳናቸው የወ/ሮ ስላስ አባዲ ልጅ ስትሆን ከ3ወር ልጇ ጋር በቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልላ ነው ያገኘናት፡፡
“ በዕለቱ በ23/10/12 ማለት ነው፡ ቤታችን እያለን ብዙ ሆነው መጡ ብረታ ብረት ገጀራ ቆንጨራ ይዘዋል፡፡ መስኮቱን መሰባበር ጀመሩ መስታወት ሲሰብሩ ልጄን እና እኔን እንዳጋጣሚ መቱን፤ ባለቤቴም በነፍስ ነበር ሲፈልጉት የነበረው አምልጦ ወጣ እኔም በበቆሎ ውስጥ ለውስጥ ሄጄ ነው የጠፋነው፡፡ ሕይወታችን ተርፏል በቢጃማ ብቻ ነው የቀረነው፡፡ የእኔም የበሽተኛ እናቴም ሙሉ ንብረት ነው የወደመው” ብላናለች፡፡


ወ/ሮ አስናቀች ዘውዴ
“ ከ50 ዓመት በላይ በሻሸመኔ ከተማ ኖሬአለሁ፡፡ ባለቤቴ እና ልጄ በፊት ሞተውብኛል፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያፈራሁት ንብረቴ ተቃጠለ ድንገት ባዶዬን ቀረሁ፡፡ የኔም የልጄም ቤት ባዶ አደረጉት፡፡አሮጊቷ የታለች ትውጣ እንረዳት ነፍጠኛ ናት እያሉ ጎረቤቶቼ እግዚአብሔር ይስጣቸው ደብቀው ነፍሴን አተረፉልኝ ብለዋል፡፡ እኔ ጡረተኛ ነኝ ሌላ ሀገርም የለኝ ብሞትም የምቀበረው እዚሁ ነው፡፡” ብለውናል፡፡
አቶ ጌቱ ተመለሰው
አቶ ጌቱ ሻሸመኔ ከተማ ከ20 ዓመታት በላይ እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ ከባለቤታቸውና ከ3 ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ ከመኖርያ ቤታቸው ጋር የተያያዞ ሱቅ የነበራቸው ሲሆን የሸማቾች ሸቀጥ ያከፋፍሉ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሻሸመኔ ተ/ሐይማኖት ቤተክርስትያን ተጠልለው ላሉት ኮሚቴ ሆነው እያስተባበሩ ያሉ ሲሆን
“በ 23/10/12 ዓ.ም. ከጠዋት 1 ሰዓት ጀምሮ በአካባቢያችን ችግር ነበር፡፡ የኔም ቤት ከነንብረቱ ከነሱቁ ጨምሮ፡ በአካባቢያችን 8 ቤቶች 6 ባጃጆች እና 2 መኪናዎች ተቃጥለዋል፡፡ ዕድሜ ልክ ለፍተን ያፈራነው ንብረት በደቂቃዎች ውስጥ ሲጋይ ከባድ የአእምሮ ህመም ነው ያለው፡፡ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበረውም ነፍጠኛ የምኒሊክ አሽከር እያሉ ነበር፡፡ ነፍሳችን የተረፈውም በአካባቢው ተወላጆች ነው፡፡ አሁን ተጠልለን ያለነው በቤተክርስትያን ውስጥ ነው” ብለውናል፡፡ ”

መሳፍንት ተስፋዬ
መሳፍንት በ ደብረ ፅጌ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልለው ስለሚገኙት ወገኖች በዚህ መልኩ ገልፆልናል፡፡
“ በአባወራ ደረጃ 44 ሲሆኑ አጠቃላይ 185 ግለሰቦች ሕፃናትን ጨምሮ ይገኛሉ፡፡ ቤት ንብረታቸው በሙሉ በእሳት ቃጠሎ የወደመ፡ በርና መስኮታቸው የተሰባበረ እና የተወሰኑም በስጋትና በዛቻ ወደ ግቢው ሸሽተው የመጡም አሉ ” ብሎናል፡፡
ሳብር ሀምዛ
“ ሻሸመኔ ተወልጄ፣ ወልጄ፣የልጅ ልጅ ያየሁባት ናት፡፡እናት አባቶቻችንን እዚሁ ነው የቀበርነው፡፡ የት እንሄዳለን ቤቱን ከሰራሁት አራት አመቴ ነው፡፡ በዝርፍያም በቃጠሎም ንብረታችን ወደመ እኛ ያለነው ገበሬ ማህበር ነው፡፡ እንዳለ ሆ ብለው መጥተው ሲወሩን በካነቴራ ነው ሸሽተን ያመለጥነው መስኪድ ቅርባችን ነበር ጎረቤት ቀበሌ ነው ቀበሌያችን፤ ራቁታችንን ስለነበርን የመስኪዱ አስተዳዳሪ ሸህ ጀማል አልባሳትን ረዱን ከኛ አካባቢ 10 እንሆናለን ስልጤዎች ከአንዷ በስተቀር፡ ተባረን የመጣነው ቤታችን የተቃጠለው ማለት ነው፡፡ ለ18 ቀናት ያህል እዛው መስኪድ ነው የቆየነው፡፡ አስተዳደሮች የሀገር ሽማግሌዎች ይዘው መጥተው ለበሽታውም እዚህ ከምትሆኑ ብለው ዋናው ቤት ሙሉ በሙሉ ቢነድም ሰርቪስ ተሰባብሮ ተገነጣጥሎ ተዘርፎ የተረፈ አንድ ክፍል ጠጋግነው አሁን እዛ ገብቻለው፡፡ ከኛ ትንሽ ራቅ ብሎም የተቃጠሉትን ጨምሬ 15 የስልጤ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ አራት የሚሆኑ ባጃጆች ፡ 5 Lሚኒ ባስ ታክሲን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ተሽከርካሪ ተቃጥሎብናል፡፡መስኪዱ ነው እኛን ጠብቆ ለዚህ ያደረሰን፡፡ ካገሩ ወጥተን እንዳንጠፋ ለ18 ቀን አቅፈው ይዘውን ከጎረቤታቸውም፡ ከየትም እያሉ ምግብም እያቀረበልን ነበር፡፡ ወረዳው፡ በቆሎ ከዛም ፓስታ አምጥተው ሰተውናል፡፡ በአጠቃላይ ሙስሊሞች ብቻ መስኪድ የተጠለልነው 53 እንሆናለን፡፡ከክርስትያኖቹ ጋር ከዚያ በላይ ነን፡፡ እኔ ብቻ 8 ቤተሰብ አለኝ፡፡ ይህን ሁሉ ሰው የረዱት ሼህ ጀማል የኑር መስኪድ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡”
ሳብር ሀምዛ ይህ አሳዛኝ ድርጊት ለመፈጸሙ ስለምክንያቱ የራሱን አስተያየት ሲያስረዳ
“ እኛ ምን እናውቃለን ምንአልባት በብሄር ከሆነ እንጂ በሐይማኖት ቢሆንማ እኛስ ሙስሊም አይደለን፤ ሙስሊም አይነኩም ከተባለ እኛን ለምን ነኩን” ሲል ይጠይቃል፡፡
ፋሪስ ሲራጅ
የአርባ አመቱ ፋሪስ ተወልዶ ያደገው ሻሸመኔ እንደሆነና የስድስት ልጆች አባት እንደሆነ፣ ወደ ስልጤ ልሂድ ብል እንኳ የሚያውቀኝ የለም፡፡ አባቶቻችን እንኳ ሞተው ሞተው እዚሁ ነው የተቀበሩት ሲል ይናገራል፡፡
“ በ23/10/12 ዓ.ም. የደረሰብን ግን እኛ ከዚህ እንድንወጣ ያለመ ይመስላል፡፡ ሌላ የምናውቀው ሀገር የለንም፡፡ ስድስት ልጆች ወልጃለሁ ስራም ዕድርም ሁሉም ነገሬ እዚሁ ነው፡፡ የመንግስት የመኪና ሚዛን ዘመናዊ ድርጅት ካቃጠሉ በኋላ ወደ እኛ ቤት መጡ ለሚዛኑ ይቀርባል ቤታችን በነፍስ አምልጠን መስኪድ ተጠለልን፡፡መልካም ሰዎች ናቸው ህይወታችንን ያተረፏት፡፡

ወ/ሮ ፀሐይ እልፋይ
ወ/ሮ ፀሐይ ዕድሜአቸው 50 የደረሰ ሲሆን በሻሸመኔ ከተማ ተወልደው አድገው እዚህ እንደደረሱ ይናገራሉ፡፡
“ መኖርያ ቤቴ ሙሉ በሙሉ፤ ሰርቪስ ቤት የነበረኝ ሙሉ እቃ ባዶ ሆኖ በርና መስኮት ሳይቀር ነው የጠፋው፡፡እኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነኝ ነገር ግን በቅርቤ የነበረው ለመኖርያ ቤቴ የሚቀርበውም መስኪድ ነውና እዛ ነው የተጠለልኩት የነበረው፡፡ ከቤቴ ፊት ለፊት የእስልምና እምነት ተከታዮች የስልጤ ብሔረሰብ ተወላጆች ነበሩ፡፡ የነሱም ንብረታቸው ከነቤታቸው መኪኖችና ባጃጆች ወድሞባቸዋል፡፡መስኪድ አብረን ነበር ተጠልለን የነበርነው፡፡ እኔ ከ14 ዓመት ልጄ እና ከማሳድገው የ4ዓመት የወንድሜ ልጅ ልጅ ጋር ወደ 15 ቀን በመስኪድ ተቀምጫለሁ፡፡ ሼክ ጀማል ነው የሰበሰበን፡፡ ከነቤተሰቡ ሰብስቦናል ልጆቹም ጭምር አይዞዋችሁ እያሉ እየመጡም ያዩናል፤ በረታችሁ ይሉናል፡፡ ት/ቤት አለ መስኪድ ውስጥ እዛ ነበርን፡፡ “
አቶ መኮንን ወ/ገብርዔል
የ ሀምሳ አንድ አመቱ አቶ መኮንን ተወልደው ባደጉበት ከተማ ሻሸመኔ ከባለቤታቸው እና አራት ልጆቻቸው ጋር የኖሩ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ወላጅ አባቴ እንኳን በ1928ዓ.ም. ነበር የመጣው፡፡ ቀደም ብሎ በሞት የተለየን ሰባ ዓመት የሚሆነው ወንድሜ እንኳን የተወለደው እዚህ ነው ብለውናል፡፡
“ እኔ የደረሰብኝ ጉዳት ብዙም አይደለም አጥር ለማፍረስ እንደሞከሩ ሕዝቡ ተባብሮ አትርፎታል ሁሉን ንብረቴን ሳይቀር ከብቶች ሳይቀር ወደ መስኪድ አስገብተው ነው ያተረፉልኝ የመስኪዱ አስተዳዳሪም የአካባቢው ነዋሪም በትብብር ው ያተረፉልኝ እንጁ አጥሩን መቅደድ ጀምረው ነበር፡፡ እንዳይነካ የኛ ነው በማለት ሳይገቡ ተቆጣጠሯቸው፡፡ እነሱን አባረው ትንሽ በረድ ካለ በኋላ ዕቃዬን አውጥተው በየቤቱ አደረጉልኝ፡፡
ለእኔና ቤተሰቦቼ አንድ ክፍል ለአንድአንድ ዕቃዎች ሌላ ክፍል ፡ ከብቶቹንም ለብቻ አድርገውልኝ ወደ 14 ቀን የሚጠጋ መስኪድ ውስጥ ያለ ት/ቤት ውስጥ ተቀምጠናል፡፡ ለኔም ብዙ ነገር የተባበሩኝ ሼህ ጀማል ናቸው” ብለውናል፡፡
አቶ ሰለሞን መኮንን
አቶ ሰለሞን ትውልዴም ዕድገቴም ኦሮምያ ላይ ነው ይላሉ፡፡ የ ስድስት ልጆች አባት እና የዜድ.ኤስ የግንድና ጣውላ መሰንጠቅያና ፈርኒቸር ባለቤት ናቸው፡፡
“ በ23/10/12 በከተማችን ሻሸመኔ ችግር ነበር፡፡ ጠዋት፡ ሰራተኛ ወደ ስራ ሊገባ ሲል ነው፡፡ ብዙ ሆነው ወጣቶች ለጥፋት ሲመጡ የአካባቢያችን ነዋሪዎችና ሸህ ጀማል ሌሎችም ኢማሞች ወጥተው ብዙ ታግለው ነው ያተረፉን፡፡ የኔን ብቻ ሳይሆን እዛ አካባቢ ያለውን በሙሉ ያተረፉት እነርሱ ናቸው፡፡ለምሳሌ አርሲ ነገሌ ያለው አንድ ዓይነት ድርጅቴ ተቃጥሎብኛል፡፡ ማን እንዳቃጠለው አላውቅም፡፡ሙሉ በሙሉ ነው የወደመው፡፡ ሻሸመኔም ቢሆን ማን ይሁኑ ማን አናውቃቸውም ከመቶ በላይ ሰዎች ናቸው፡፡ እናቃጥላለን አታቃጥሉም በሚል የተቀጠቀጡም ነዋሪዎች አሉ፡፡ ሀጂ ጀማል ራሳቸውን አታልፉም ብለው ሲከለክሏቸው፡ ገፍተረው ጥለዋቸው እጃቸውም ላይ ጉዳት አድርሰውባቸውም ነበር፡፡የሰፈራችን ሙስሊም ወጣቶች ላይ ራሱ በያዙት ስለት ማስፈራራት ነበር፡፡ ሰይጣን ነው ምን አይነት ሠይጣን እንደሆነ ነው የማናውቀው፡፡ ድርጅቴ ከቀን ሰራተኞች ጋር በትንሹ ከመቶ ሰው በላይ ይተዳደርበታል፡፡ ” ብለውናል፡፡
ሐጂ ጀማል
የመልካ ኦዳ፡ ኑር መስኪድ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡በአካባቢያቸው የነበሩትን ትልልቅ ተቋማትና ቤቶች እንዳተረፉ ገልጸውልናል፡፡ለምሳሌ ተወልደ ጋራዥን፣ ሰለሞን የግንድና ጣውላ መሰንጠቅያ፡ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡
“በኔ ቅርብ ያሉ የተቃጠለ ቤት የለም አልሀምዱሊላህ፡፡ ብዙ ግብ ግብ እና እንግልት ነበር፡፡ የነበረውን ስቃይ ተወው” ብለውናል፡፡
የሪፖርቱ ምንጮች
በቦታው በመገኘት የታዘብን ሲሆን የተንቀሳቃሽ ምስል፣ የምስል እና የድምጽ ማስረጃዎችን ለማስቀረት ተችሏል፡፡በተጨማሪም የነበሩንን መረጃዎች ለማጥራትና ለማመሳከር ለተከታታይ አራት ቀናት በስልክ ቃለ መጠይቅ የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷል፡፡

አቶ አብነት ገለታው (በ አዳሚ ቱሉ ጥቃት 5 የቤተሰብ አባላትን ያጡ)

አቶ ሚክያስ ገለታው(በ አዳሚ ቱሉ ጥቃት 5 የቤተሰብ አባላትን ያጡ)

አቶ አንዳልካቸው ጥጋቡ (ተጠቂ)

አቶ ብዙአየሁ ጥጋቡ (ተጠቂ)

ወ/ሮ ቆንጂት በላይ (በጥቃቱ ባለቤታቸው የተገደሉባቸው)

አቶ ይንጋልኝ ወንደሰን ( በጥቃቱ ወላጅ አባቱን ያጣ)

መምህር አስናቀ ደቻሳ ( በባቱ ለተጎዱት በቤተክርስቲያን አስተባባሪ)

አቶ መሳፍንት ተስፋዬ (ሻሸመኔ ኪዳነምህረት ለተጠቁ በቤተክርስትያን ላሉ አስተባባሪ)

ወ/ሮ አስናቀች ዘውዴ ( ተጠቂ)

አቶ ጌቱ ተመለሰው ( ተጠቂ)

አቶ መንበሩ አድገህ (ተጠቂ)

አቶ ሳብር ሀምዛ ( ተጠቂ )

አቶ ፋሪስ ሲራጅ (ተጠቂ)

ወ/ሮ ፀሐይ እልፋይ (ተጠቂ)

ወ/ሮ ስላስ አባዲ (ተጠቂ)

ወ/ሮ መብሪት አያሌው (ተጠቂ)

አቶ ሰለሞን መኮንን (ሻሸመኔ የግንድ መሰንጠቅያ ድርጅታቸው የሙስሊም ማህበረሰቡ አትርፎላቸው አርሲ ነገሌ የተቃጠለባቸው)

አቶ መኮንን ወ/ገብርዔል ( የሙስሊም ማህበረሰቡ ንብረታቸውንና ሕይወታቸውን ያተረፈላቸው)

ሐጂ ጀማል ( የሻሸመኔ መልካ ኦዳ ኑር መስኪድ አስተዳዳሪ)

* ይህ ሪፖርት በሁለቱ ቀናት ከጎበኘናቸው ቦታዎችና አግኝተን ካነጋገርናቸው ተጎጅዎች መካከል የተወሰኑትን የያዘ እንጂ በአጠቃላይ በከተማዎቹ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት የሚያሳይ አይደለም፡፡

ማጠቃለያ
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሪፖርቱን ገምግሞ በተጠቀሱት ስፍራዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ማለትም

ሀ. በዘር

ለ. በሐይማኖት
ሐ. በዘር እና በሐይማኖት መፈፀማቸውን ተገንዝቧል፡፡

በየደረጃው ያለው የፀጥታ እና የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ እነዚህን ጥቃቶች ለማስቆም ከፍተኛ ዳተኝነት ታይቶ እንደነበር ተረድቷል፡፡

ይህንን ወንጀል ፈፃሚዎችም ሆኑ አስፈፃሚዎች ቀድሞ የታቀደ እና ዝግጅት የተደረገበት እንደነበር በሚያሳይ መልኩ በተወሰኑ ስፍራዎች ላይ፡ የስም ዝርዝር በመያዝ ጭምር ቤታቸውና የስራ ቦታቸው በመሄድ በሕይወት እና ንብረታቸው ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ተረድቷል፡፡

ተጎጂዎችም ሆነ ከአሁኑ ጥቃት የተረፉ ዜጎች

ሀ. አሁንም ዛቻና ማስፈራርያ እንደሚደርስባቸው
ለ. ለደህንነታቸው በክልል የፀጥታ ኃይል እምነት እንዳጡ እና
ሐ. ዳግም ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ተረድቷል፡፡

እንደ ማህበረሰቡ ፤ በነበረው አቅም፡ ወገኑን መከላከል፣ መደበቅ፣ ማሸሽ እና ተማፅኖ ባይሆን ኖሮ የደረሰው ጥፋት ከዚህም የከፋ ይሆን እንደነበር ተገንዝቧል፡፡

ማሳሰብያ

መንግስት የዜጎችን ደህንነት ከመጠበቅ የቀደመ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም!
የዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ በሕይወት የመኖር፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልሎች መኖር፣ተንቀሳቅሰው የመስራትና ንብረት የማፍራት መብት አላቸው፡፡ በማንኛውም የማንነት መገለጫቸው፤ በመረጡትም ቢሆን ባልመረጡት፤ በየትኛውም አካል ፡ በምንም አይነት መልኩ፤ እንኳን ጥቃት፡ አድልዎ ሳይደረግባቸው፡ በነፃነት፡ የመኖር መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ከዚህ የሚቀድም ምንም አጀንዳ ሊኖር አይገባም፡፡ ሌላው ችግር እና ፈተና ሁሉ ዜጎች በሰላም ሲኖሩ እና በህብረት ሲቆሙ፡ በአንድነት፡ ፊት ቀላል ነው፡፡
በዓለም ላይ ማንነትን በዘርም ይሁን በሐይማኖት መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ድንገት የሚከሰቱ አይደሉም፡፡ የሩዋንዳው ፍጅት የረጅም ጊዜ የጥላቻ ንግግር፣ የሚድያ ቅስቀሳ፣ ማንቋሸሽ እና ዝግጅት የተደረገበት በኃላ ለተፈጠረው ዕልቂትም የተለያዩ ምልክቶች እየሰጠ ቆይቶ የተፈፀመ ነው፡፡

በሀገራችንም ከፍተኛ የጥላቻ ንግግሮች፡ የሚድያ ቅስቀሳዎች፡ የተዛቡ የታሪክ ትርክቶች፡ ያላግባብ የተለጠጡ እና ጥላቻን መሰረት ያደረጉ የማንነት ግንዛቤዎች፡ፍረጃዎች፡ ከዘመኑ ጋር ያልዘመነ በሃሳብ ላይ ያልተመሰረተ የፖለቲካ አካሔድ የፈጠረው ውጥረትና ትኩሳት፡ ተደጋጋሚ ግጭቶችን እየፈጠረ፡ የንፁሃንን ደም በተደጋጋሚ እያፈሰሰ፡ ንብረታቸውን እያወደመ፣ እያፈናቀለ፣ የቆየ አብሮ የመኖር እሴታቸውን እና ማሕበራዊ መሰረታቸውን ቀስ በቀስ በመሸርሸር መቃቃርን እያመጣ ነውና፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ወደ ለየለት፡ በዓለም፡ የዘርና የሐይማኖት ጭፍጨፋ፡ ጥቁር መዝገብ ላይ የሀገራችን እና የሕዝቦቿን ስም እንዲሰፍር ሊያደርግ የሚችልን አደገኛ ልምምድ መንግስትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመተባበር ማስቆም ይገባናል፡፡ አንዳችን ሰላም ካልሆንን ሁላችንም ሰላም አይደለንም፡፡

በመሆኑም የጥቃቱን አይነትና ስያሜ ላይ ጊዜ ማጥፋቱን ትተን የአንድም ሰው እንኳን ሕይወት ቢሆን ክቡር እና ታላቅ ነው፤ በየትኛውም ምክንያት ሊያልፍ አይገባም! በማለት ጠንካራ አቋም በመያዝ መንግስት

አሁንም ስጋት ላይ ያሉ ወገኖችን ከሌላ ጥቃት እና ዛቻ በዘላቂነት እንዲታደግ

የሕግ የበላይነት እንዲከበር፡ የዜጎች በየትኛውም የሀገራቸው ክልሎች በእኩልነት የመኖር መብት እንዲረጋገጥ

በቶሎ ጥፋተኞችን ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ በማድረግ ለተጎጂዎች ፍትህ እንዲሰጥ

ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ተሰይሞ ጥቃቱ እንዲጣራና ውጤቱ በቶሎ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ

ቤተሰቦቻቸውን እና ንብረታቸውን ያጡ ዜጎች ካሳ እና መልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች

አንድ አንድ የፀጥታ እና የአስተዳደር ተቋማት በማህበረሰቡ እምነት እየታጣባቸው ያለበት ሁኔታ ስር ሳይሰድና ወደ ለየለት ስርዓት አልበኝነት ሳይመራን መንግስት ከላይ እስከታች የጀመረውን መዋቅሩን የመፈተሸ ስራ በማጠናከር ዜጎች፡ ተቋማትን ”የኔ” የሚሉበትን ስርዓት እንዲፈጠር አበክሮ እንዲሰራ

የፌደራል መንግስት፣ የክልል መንግስታት፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችና የሚመለከታችሁ በሙሉ፡ አሁንም በተከበረው ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን፡ ማህበራዊ ሰላም እና የማይበጠሱ ተፈጥሯዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ስነልቦናዊ እና የደም ትስስሮችን መሰረት ያደረገ፣ መሬት ላይ በዜጎች መካከል ያለውን ውህደት፣ የማይክድ፣ ሰው መሆናችን አንድ ያደረገን ታላቅ ማንነት መሆኑን፡ በማጉላት ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርበት፤ በሌሎች ማንነቶቹ ደግሞ በብዝኃነት በሕብረት የሚደምቅበት፡ የመንግስት የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት በቅንነት እና በዕውነት በመቆም ታሪክ ሰርተን እንድናልፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ነሐሴ 4 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

Address

Debre Tabor

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የደቡብ ጎንደር ዞን አብን ፅ/ቤት South Gondar Zone NaMA posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share