03/06/2026
ተጠቃሚዎች ለከፈሉት ገንዘብ ደረሰኝ ባለመሰጠታቸው ግብር ከፋዩች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ
በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም ወረዳና ከተማ ግብር ከፋዮች ደንብና መመሪያን አውቀው እንዲሰሩ በመድረክና በገጽ ለገጽ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የተሰጣቸውን ትምህርት በተግባር ስለማዋላቸው በተደረገ ክትትል 3 ነጋዴዎች 150 ሺ ብር ሲቀጡ 5 የሚሆኑትን በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ታልፈዋል፣ ሲሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ የታክስ ኢንተለጀንስ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡
የህግ ተገዥነትን ለማሣደግና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በተሰራው ስራ 55 ጥቆማዎችን ከህብረተሰቡ በመቀበልና በማጥራት 7.9 ሚሊዬን ብር የግብይት መረጃ የተገኘ ሲሆን ይህም በገቢ አሰባሰብ በኩል ውሣኔ እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡ እንዲሁም 322 ደረሰኞችን በመመርመር 188 የሚሆኑት ሐሰተኛ ደረሰኝ ሆነው በመገኘታቸው 10.3 ሚሊዬን ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ ተገኝቶ ውሣኔ ተሰጥቶበት እስከአሁን 3.6 ሚሊዬን ብር ገቢ ሆኗል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሠራተኞች የስራ ግብር ቀንሶ ወደ መንግስት የማስገባት ስራ በ94 ድርጅቶች ላይ ክትትል በማድረግ ተሰውሮ የነበረ 17.9 ሚሊዬን ብር ገቢ ተሰብስቧል ሲሉ አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ውጤት መምጣት ጥቆማ ሰጪዎቻችንና አጋሮቻችን ተመስጋኞች ናቸው፡፤ በሌላ በኩል የተቋሙ ባለሙያዎችና አመራሮች ከብልሹ አሰራር ነፃ ሆነው በታማኝነት ህዝብ እንዲያገለግሉ ይጠበቃል፣ ለዚህም ተከታታይ ስልጠናና ምክር ሲሰጥ ቆይቷል፣ ሆኖም ግን 1 የጽ/ቤት ኃላፊና 8 ባለሙያዎች በሁለት ወረዳ ያለአግባብ ተጠቃሚነት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛል፣ ሲሉ አስተባባሪው አስረድተው በቀጣይም ግብር ከፋዩ ለተጠቃሚ ደረሰኝ በመስጠት ግዴታቸውን እንዲወጡ እንዲሁም ሃሰተኛ ደረሰኝ ከመጠቀም አንዲጠበቁ ተከታታይ ትምህርትና ግንዛቤ እንዲሰጣቸው አሣስበዋል፡፡ በሌላ በኩል የግል ድርጅቶች ከተቀጣሪ ሠራተኞች ተገቢውን የስራ ግብር ሰብስበው ለመንግስት እንዲያስገቡ እንዲሁም በሌብነት ላይ የተሰማሩ የገቢ ተቋሙ ባለሙያና አመራር ከድርጊታቸው ታቅበው ህጋዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ሲሉ የመምሪያው የታክስ ኢንተለጀንስ አስተባባሪ አሣስበዋል፡፡
ዘገባው የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ የግብር ትምህርትና ኮሙንኬሽን ዋና የስራ ሂደት ነው ግንቦት 22/2018 ዓ.ም