03/06/2026
በሐሰተኛ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለመገልገል የሞከሩ ግለሰቦች በፅኑ እስራት ተቀጡ
ግንቦት 26/2018 ዓ.ም በወላይታ ዞን በሐሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ ተቀጡ፡፡
ተከሳሾቹ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ከአይናቴ ሎሪሶ ከተባለች ግለሰብ ጋር በነበረው የውርስ ክርክር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 47413 በሆነው በቀን 12/06/16ዓ.ም ለ2ኛ ተከሳሽ ውሰኔ የተወሰነ በማስመሰል ሐሰተኛ የጠቅላይ ፍ/ቤት ማህተምና የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ምክትል ፐሬዝዳንት ፊርማ ያልሆነውን በማሳረፍ ሐሰተኛ የውሳኔ ግልባጭ ለ2ኛ ተከሳሽ የሰጠ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽም የተዘጋጀውን ሐሰተኛ ውሳኔ እያወቀ በመገልገል የግል ተበዳይ አይናቴ ሎሪሶን የውርስ ክስ በመቃወም ለዳሞት ፑላሳ ወረዳ ፍ/ቤት ያቀረበ በመሆኑ ተከሳሾች በፈጸሙት ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና መገልገል ወንጀል ተከሰዋል፡፡
የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ መዝገብ የመረመረው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹን ጥፋተኛ በማለት 2 አመት ከ9 ወር ጽኑ እስራት እና 1,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
"ይህ የቅጣት ውሳኔ ለሌሎች መሰል ድርጊት ለሚፈጽሙ አካላት አስተማሪ እንዲሆን ታስቦ የተላለፈ ነው፡፡ ማህበረሰቡም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና አጥፊዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡"
ዘገባው የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ክፍል