20/06/2024
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ59 ሺህ በላይ በጎፈቃደኞች በማሳተፍ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት ለማዳን መታቀዱ ተገለጸ
በደብረብርሃን ከተማ የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በንቅናቄ በይፋ ተጀመረ
የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ የተከበሩ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት በ2015/16 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣የአረጋውያን ቤት ጥገና፣የተፋሰስ ጽዳት፣ደም ልገሳ፣የማጠናከሪያ ትምህርትና ሌሎች በርካታ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በ2016/17 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ59 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በማሳተፉ ከ154 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ስራው መጀመሩን አብራርተዋል፡፡በዚህም ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት ማዳን እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡
በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቤት እንደሚገነባ፣የአቅመ ደካማ ቤቶች በስፋት እንደሚጠገኑ፣ደም ልገሳ፣ከተማን የማስዋብና ደም ልገሳ፣የአረንጓዴና የኮሪደር ልማት፣የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርትና ሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ አብራርተዋል፡፡
ከተማው ባለፈው ዓመት በበጎ ፈቃድ ስራ ከክልሉ 1ኛ መወጥቶ ዋንጫ መሸለሙን አስታውሰዋል፡፡በዚህ ዓመትም ከባለፈው የበለጠ ስራ ለማከናወን ዛሬ በንቅናቄ ስራው መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ በመሆኑ በስራው ሁሉም ሰው በመሳተፍ የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ ከንቲባ በድሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ቤታቸው የሚጠገንላቸው ወይዘሮ ቀለመወርቅ አክሊሉ በሰጡት አስተያየት የቤታቸው ቆርቆሮ አርጅቶ ስለተቀዳደደ ክረምት በመጣ ቁጥር ብዙ መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡
መንግስት ችግራቸውን አይቶ ዛሬ ቤታቸውን ስለጠገነላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡