05/06/2026
" የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን እንግታ " በሚል መሪ ቃል የሰሜን ሸዋ ዞንና የባሶና ወረና ወረዳ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ዓመታዊ የአካባቢ ጥበቃ በዓልን በጋራ አከበሩ
በዓለም ለ55ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ33ኛ ፣ በክልል ደረጃ ለ29ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካባቢ ጥበቃ ቀንን የሰሜን ሸዋ ዞንና የባሶና ወራና ወረዳ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት በዛሬው ዕለት በጋራ አከበሩ።
በክብረ በዓሉ ላይ የሰሜን ሸዋ ዞንና የባሶና ወራና ወረዳ አመራሮች፣ የቡድን መሪዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙ የባሶና ወራና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘሪሁን ኃይለጊዮርጊስ እንዳሉት የሰው ልጅ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሚሰጠው ተኩረት በማነሱና የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የገጠመንን ችግር ልናስተካክል ይገባል ያሉ ሲሆን ለተፈጥሮ ምቹ ነገርን ስንፈጥር ህይወት ላለው ፍጥረት ሁሉ ምቹ ነገር እናስገኛለን ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞንን በመወከል የተገኙት የዞኑ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሽፈራ ግርማ በበዓሉ የመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉትም በዓሉ ሀገራዊ ምርጫውን በሠላም ባጠናቀቅንበት ማግስት የተከበረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ልማት አሻራ ተግባር ላይ ያለንን ስራ ልናጠናክር ይገባል፤ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ ተቋም ስራ ብቻ አይደለም ሁላችንም ኃላፊነት አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከደብረብርሃን ዩንቨርስቲ በመምጣት በበዓሉ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ገብሬ ተፈራ (ዶ.ር) እንዳሉት 1972 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) የመጀመሪያው አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስብሰባ በማካሔድ የአካባቢ ጥበቃ ስራ አለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን መሠረት ተጥሏል፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይም ከሰው ልጆች ጋር ቀጥታ የሚገናኝ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለዋል።
ሌላኛው ጥናት አቅራቢ አለምነው ብርሃን (ዶ.ር) እንደገለፁትም ተፈጥሮ ሁሉን ነገር ታቀርብልናለች እኛ ግን የምንወስደው አላግባብ ነው፤ ስለሆነም ዘላቂ ልማት እናምጣ ሲባል ኢኮኖሚ ልማት፣ ማህበራዊ ልማትና የከባቢ ስነ ምህዳር ልማትን የሚያጠቃልል ስለሆነ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ሁሉም አካል በያገባኛልና ይመለከተኛል ስሜት ተግባሩን ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት የኃላፊው ተወካይ የሆኑት አቶ በሱፈቃድ ነበሩ ገድሌ እንዳሉት እንደ ሰሜን ሸዋ ዞን የአካባቢ ጥበቃ ስራውን ከአጋር አካላት ጋር ተባብረን እየሰራን ነው፤ በተለይ በካይ የሆኑ ማቴሪያል አጠቃቀም ላይ ህጎች እየተሻሻሉና መተግበር እየጀመሩ ነው ብለዋል። ተወካይ ኃላፊው ለፕሮግራሙ መሣካት ሚና የነበራቸውን አመስግነው የዕለቱ ፕሮግራምም ተጠናቋል።