25/11/2024
ቱሪዝም እና ሰላም
ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት የሚፈልግ ዘርፍ ነው። ከሞላ ጎደል ሁሉም የቱሪዝም ዓይነቶች የሚከወኑት በሰላም ጊዜ ነው።
ቱሪዝም ከመኖሪያ አካባቢ በመራቅ የሚደረግ ጉዞ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀደመው ዘመን ቱሪስት መሆን ራስን ለአደጋ እንደማጋለጥ ይታይ ነበር፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴም ከአደጋ (risk) መጋፈጥ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ይታመን ነበር።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን በተለይም ዘመናዊ የየብስ፣ የባህር እና አየር ትራንስፖርት መጀመር ጋር ተያይዞ ቱሪዝም አደጋ የሌለበት ወይም አደጋ የማይፈልግ እንቅስቃሴ/ጉዞ እየሆነ መጥቷል፡፡
በአሁን ጊዜ ቱሪስቶች ለጉብኝት፣ ለመዝናናት፣ ለማወቅ/መተዋወቅ፣ ለማረፍ ወዘተ በሚያደርጉት ጉዞ ወቅትም ሆነ በመዳረሻዎች የሚኖራቸው ቆይታ ሰላማዊ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቱሪስቶች ጦርነት፣ አለመረጋጋት እና ግጭት ወዳለባቸው መዳረሻዎች መሄድ አይፈልጉም፡፡
በሰላም እጦት ቱሪስቶች ወደ መዳረሻዎች የሚያደርጉት ጉዞ ሲቆም ወይም ሲቀንስ ደግሞ ከቱሪዝም የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች ሰለሚቀንስ ወይም ሰለሚቀር ሁለንተናዊ ጉዳት ያስከትላል። በመሆኑም ሁሉም ሰው ለሰላም እና መረጋጋት አበክሮ ሊሰራ ይገባል።
ቱሪዝም እና ሰላም! ቱሪዝም ለሰላም! ሰላም ለቱሪዝም!
ድንቅ ምድር