Elias Yitbarek

Elias Yitbarek n

27/04/2022

መከላከያ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሠማርተው ወደ አገራቸው ያልተመለሱ ጥቂት የሠራዊት አባላትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሠማርተው ወደ ሃገራቸው ያልተመለሱ ጥቂት የሠራዊት አባላትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡
በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሠማርተው ወደ ሃገራቸው ያልተመለሱ ጥቂት የሠራዊት አባላትን አሰመልክቶ የተሠጠ ማብራሪያ
አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሃገር ሉአላዊነት ምሽግ የሆነውን መከላከያ ሠራዊት በመምታት ለውጡን ቀልብሶ ወደ ስልጣን በመመለስ ኢትዮጵያን መግዛት፤ መግዛት ካልቻለ የራስን ዕድል በራስ መወሰን በሚል ክልሎችን በመገነጣጠል ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ይዞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሠሜን ዕዝ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት ከፈተ፡፡
አሸባሪው ቡድን በሠሜን ዕዝ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪዎችን "ኢንፍልትሬት" በማድረግ ለእኩይ አላማቸው በማዘጋጀት የሠሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት በመክፈት ሠራዊታችንን ከውስጥና ከውጭ እንዳጠቃ ይታወቃል፡፡
የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው ሲጀመር ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር አብረው ሲሰሩ የነበሩ ከወታደር እስከ ከፍተኛ አመራር ያሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች ለዘመቻው ስኬትና እርስ በእርስ እንዳንማታ ሲባል ደመወዝና ቀለባቸው ሳይቋረጥ በቤታቸው እንዲቆዩ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ከሰሜን ዕዝ ጥቃት በፊት ወደ ውጭ ሀገር ሰላም ለማስከበር የተላኩ ትግርኛ ተናጋሪዎች ግን በሰራዊታችንና በተልዕኮው ላይ ችግር አይፈጥሩም በሚል በስራቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን ህወሃት የትግርኛ ተናጋሪዎች ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ በውጭ በሚገኙ የወያኔ ቅጥረኞች የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመነዛቱ በአባላቱ ላይ ውዥንብር ፈጥሯል።
ሃገር ቤት ከተመለሳችሁ ትታሰራላችሁ የሚል የማስፈራሪያ ውሸት በመንዛትና በዘረኝነት በመቀስቀስ አገራቸውንና ተቋማቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላትን የማስኮብለል ስራ ተሰርቷል፡፡ የሠራዊት አባላቱ ተቋማቸውንና ሃገራቸውን ጠልተው ሳይሆን ወያኔ በሰራው አፍራሽ ስራ ስጋት ገብቷቸው የተወሰኑ ወታደሮች ሰላም ማስከበር በሄዱበት አገር ቀርተዋል፡፡ ወያኔ ጥቂት አፍራሾችን በውስጣቸው በመፍጠር የእኩይ ዓላው አስፈፀሚ አድርጓቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከዚህ ቀደምም በዳርፉር፣ ተልእኮ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ሲደረግ በተመሳሳይ ውዥንብር ጥቂት ወታደሮች ቀርተዋል፡፡ ሱዳን ከሚገኘው ሳምሪ ተቀላቅለው ሲዋጉ የሞቱም ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም ጫና ተቋቁመው ሃገርና ተቋማቸው የሰጣቸውን ግዳጅ ፈፅመው ለተመለሱ የትግርኛ ተናጋሪ የሰራዊታችን አባላት ተቋማችን ከፍተኛ ምስጋና ያቀርብላቸዋል።
በህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው ወቅት በቤታቸው እንዲቆዩ የተደረጉ እና ከሠላም ማስከበር የተመለሡ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሠራዊት አባላት እና ሲቪል ሠራተኞች ዛሬም የተቋሙ አባላት ስለሆኑ መብታቸውና ጥቅማጥቅማቸው ይከበራል፡፡ አሁን ያለው ግጭት በማናቸውም አግባብ ከተፈታ ወደ ሥራቸው ተመልሰው ሃገራቸውን ያገለግላሉ በሚል አቋም እየተሰራ ይገኛል፡፡
አሁንም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላላችሁ፤ ከሠራዊት ጋር ግዳጅ እየተወጣችሁ ላላችሁና ለጊዜው ከስራ ውጭ ሁናችሁ ነገር ግን ደመወዝና ጥቅማጥቅማችሁ ተጠብቆ ያላችሁ ወታደሮች በወያኔ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳትንበረከኩ አገራችሁን እንድታገለግሉ፤ ቤተሰባችሁን እንዳትበትኑ፤ ጥቅማችሁ እንዳይቋረጥ፤ በክህደት ታሪክ እንዳትመዘገቡ እናሳስባለን፡፡
የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር

27/04/2022

በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ።
የአማራ ሕዝብ በተለያዩ ቦታዎችና ዘርፈ ብዙ በሆኑ ውጫዊ እና ውስጣዊ የማጥቂያ ስልቶች የተወነጨፉበትን ቀስቶች መክቶ ሳይጨርስ በታሪካዊቷና ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ተምሳሌት በሆነችው ጎንደር ከተማ ውስጥ ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ ግጭት በመቀስቀስ የሕዝቡን አንድነት ለመስበር ጥረት ተደርጓል።
በዛሬው እለት የጎንደር ከተማ ነዋሪ እና የጎንደር ሕዝበ ሙስሊምና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም የሁሉም አባት የነበሩት ታላቁ ሸኽ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር እየተፈጸመ በነበረበት ሰዓት ከቀብር ቦታው ጋር ድንበርተኛ የሆነው ቤተ ክርስቲያን ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ "እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው" በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል።
በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን እየገለጽን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን እንመኛለን፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት በማንኛውንም አይነት የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ሆነ በንጹሃን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስን ጥፋትን የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም፡፡ ስለሆነም በጥፋተኞች ላይ አስፈላጊውን ሁሉ ህጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃም ይወስዳል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግሥት የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ፤ በድርጊቱ የተሳተፉትንና ግጭቱን እያባባሱ ያሉ አካላትንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልላችን የጸጥታ ኃይል፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሰላም ወዳድ የሆኑት የጎንደር ከተማ ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በመሆኑም አካባቢውን በማረጋጋት እና ህግና ሥርዓትን በማስከበር ግጭቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማሳባሰብ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን የመግለጽ፣ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ሥር የማዋል፣ ተጎጅዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማጣራት ሥራዎችን በማከናወን ለሕዝብ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡
መላው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ራሱን፣ አካባቢውና እና ከተማውን በማረጋጋት፣ በመጠበቅና የበኩሉን አስተዋጽኦ በመወጣት መንግሥት አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ እያከናወነ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ከጸጥታ ኃይላችን ጎን በመሆን በተለመደው መንገድ ትብብሩን እንዲያስቀጥል እንጠይቃለን፡፡
ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም.
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

09/04/2022

የሁሉንም ድርጅቶች የሂሳብ አያያዝ ማዘመን እንደሚገባ ተጠቆመ
(ዜና ፓርላማ)፣ ሚያዚያ 01፣ 2014 ዓ.ም፤ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሁሉንም ድርጅቶች የሂሳብ አያያዝ ማዘመን እንደሚገባ ጠቆመ።
ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው ሰሞኑን በመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር የመስክ ምልከታ በአደረገበት ወቅት ነው።
በምልከታውም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ተቋሙ ድርጅቶች ውጤታማና ትርፋማ እንዲሆኑ እያደረገ ያለው ጥረትና የሰነድ አያያዝ እንዲሁም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በጥንካሬ አንስተዋል።
በአንፃሩ ሁሉንም ድርጅቶች ወደ ዘመናዊ ሂሳብ አያያዝ ማስገባት፣ ያልተከፈሉ ብድሮችን ማስከፈል እና እየከሰሩ ያሉትን ጥናት አድርጐ ውሳኔ መስጠት እንዲሁም በድርጅቶች ያለአግባብ ተጠቃሚነት እንዳይኖር መከታተልና መቆጣጠር፣ በየድርጅቶቹ ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶችን ማስወገድ እና ችግር ውስጥ ያሉትን ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል እና የስራ ባልደረቦቻቸው በልማት ድርጅቶች የኮርፖሬት ገቨርናንስ ስርዓት ለመዘርጋት እና ስርዓቱን ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎች ተዘጋጅተው በሥራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
የስርዓቱን ትግበራ ወጥነት ባለው መልኩ ለመመዘን የሚያስችል የኮርፖሬት ገቨርናንስ ስኮር ካርድ ተዘጋጅቶ ሙከራ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ2ዐ1ዐ በጀት ዓመት ጀምሮ IFRS እንዲተገብሩ እየተሠራ እንደሚገኝና ከ36 ድርጅቶች ውስጥ 25ቱ የIFRS ትግበራውን አጠናቀው በውጭ ኦዲት ያስመረመሩ፣ 4ቱ በውጭ ኦዲት ምርመራ ሂደት ላይ፣ 5ቱ ትግበራ ሂደት ላይ ሲሆኑ 2ቱ ድርጅቶች የIFRS ትግበራ ያልጀመሩ ናቸው፡፡
ከድርጅቶች አቅም በላይ የሆኑ ብድሮች በመንግሥት ውሳኔ ማግኘታቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ ከ1987 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ከ370 በላይ የልማት ድርጅቶችና ቅርንጫፎች ወደ ግል አልሚዎች በተለያየ የሽያጭ ሞዳሊቲ መተላለፋቸውንና በቀጣይም በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብረ-መልሶችን እንደግብአት ወስደው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በፋንታዬ ጌታቸው

09/04/2022

Address

Adis
Dabra-Berhan
L

Telephone

+251973091608

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Elias Yitbarek posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share