01/09/2024
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3.8 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ዳገቶ ኩምቢ ገለፁ።
የፌደራል ፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈፃሚዎች የጋራ ምክክር በሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ የነበረው መድረክ ተጠናቀቀ።
የኢፌዴሪ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳገቶ ኩምቢ እንደገለፁት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ መንግስት የፋይናሽያል ሪፎርም፣ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ፣ የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም የውጭና የገቢ ሥራዎች ሪፎርም ተጠቃሾች መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በሀገሪቱ 10 ሺህ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ 3.8 ቢሊዮን ዶላር መሳብ መቻሉን አቶ ዳገቶ ጠቁመው የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች ፍቃድ ካወጡ በኃላ በፕላናቸው መሰረት ወደስራ እንዲገቡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ኢንቨስትመንቱ የማይተካ ድርሻ አለው ብለዋል።
ያለውን የኢንቨስትመንት ፖቴንሽያል በውል ለይቶ በማስተዋወቅ ረገድና መሰረተ ልማት በማሟላት ያሉ ክፍተቶችን መቅረፍ እንደሚገባም ምክትል ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልፀዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ የክልሉን አጠቃላይ ገጽታ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ካለው የተፈጥሮ ሀብትና ምቹ ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆኑን በሰነድ አመላክተዋል።
ከፖቴንሽያል አንፃር የማዕድን ሀብት፣ መልማት የሚችል መሬት፣ ምቹ የሆነ የአየር ፀባይ ፣ የቡና ፣ የቅመማ ቅመም ፣ የፍራፍሬ ፣ የሰብል የመሳሰሉት የሚመረቱበት እንደሆነም በሰነዳቸው አቶ ተመስገን ጠቁመው ክልሉ የበርካታ ሀብት ባለቤት መሆኑን ጠቁመዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው በሚመለከታቸው መልስና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል ።
የምክክሩ ተሳታፊዎች በመጨረሻም በቤንች ሸኮ ዞን በቡናና ቅመማቅመም ልማት ኢንቨስትመንት ላይ ያለውን የበበቃ ኮፋ ስቴትስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የቡና ፣ የቁንዶ በርበሬ፣ የጎማ ዛፍ ልማትና ዘመናዊ የቡና መፈልፈያን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ሌላው የጉብኝት አካል ያደረጉት በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ አሮጌ ብርሃን ቀበሌ ከ1000ሄ/ር በላይ እየለማ ያለውን የሞገስ ይመር የቡናና ቅመማቅመም ልማት ድርጅትንም በመዘዋወር ተመልክተዋል።