03/06/2026
በሥነ ምግባር እና በእዉቀት የዳበረ ትዉልድ ለመቅረፅ የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነዉ።
🌿🌿🌿🌿🌿🌿
በአመለካከትና በእውቀት የዳበረ፣ በሥነ-ምግባር የታነጸ እና ለሀገር ተቆርቋሪ ትውልድ መቅረፅ የአንድ ሀገር የረጅም ጊዜ ህልውና እና እድገት መሰረት ነው። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ተቋማት (ከመዋለ ህፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) ግንባር ቀደም እና የማይተካ ሚና አላቸው።
ትምህርት በፈተና ውጤት እና በዕውቅና ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን የለበትም። ተማሪዎች ያገኙትን እውቀት በዕለት ተዕለት ህይወታቸው ወደ ተግባርና ወደ ፈጠራ የሚቀይሩበት የክህሎት ማእከል መሆን አለበት።
በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ጥናቶችና ምርምሮች የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እና የሀገርን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያፋጥኑ መሆን ይኖርባቸዋል።
ከሙስና፣ ከሌብነት፣ ከኮፒራይት እና ከሌሎች የሞራል ዝቅጠቶች የጸዳ ትውልድ ለመገንባት፣ የትምህርት ተቋማት የንቅናቄ ማእከል መሆን አለባቸው። ተማሪዎች ልዩነቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ የሚያስተናግዱበት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚገነባበት እና ለሕግ የበላይነት የሚገዙበት የዜግነት ትምህርት በተግባር መተግበር ይኖርበታል ማለት ነዉ።
መምህራንም እውቀት አስተላላፊ ብቻ ሳይሆኑ በአመለካከት፣ በሥነ-ምግባር እና በአሰራር ለተማሪዎቻቸው አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
መምህራን በዘመናዊ የማስተማር ስነ-ዘዴ እና በቴክኖሎጂ እንዲበለጽጉ ተከታታይ ስልጠናዎች ሊሰጧቸው ይገባል። ቴክኖሎጂን ለፈጠራ፣ ለእውቀት ፍለጋና ለበጎ ስራ እንጂ ለአሉታዊ ተፅእኖዎች፣ ለሀሰተኛ መረጃዎችና ለሳይበር ወንጀሎች እንዳይጠቀሙበት ሥነ-ምግባራዊ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ትውልድን መቅረፅ ሀገርን መስራት ነው። በአመለካከቱ የቀና፣ በዕውቀቱ የላቀ፣ በጥበብና በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ ማፍራት ከተቻለ፣ የሀገርን የዴሞክራሲ፣ የፍትህ እና የብልጽግና ጉዞ አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል ማለት ነዉ።