29/05/2026
"በከተሞች የደቀቁና ከደረጃ በታች የሆኑ አካባቢዎችን በኮሪደር ልማቱ እንዲሻሻሉ እየተደረገ ይገኛል"
አቶ ሱለይማን እሸቱ
የአብክመ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ኅላፊ
ባለፉት አስር ወራት በክልሉ ከተሞች በኮሪደር ልማቱ 120ሄ/ር ለመሸፈን ታቅዶ የደቀቁና ከደረጃ በታች የሆኑ አካባቢዎችን 91ሄ/ር የሚጠጋ አካባቢ የማሻሻል ስራ በማከናወን የከተሞችን ገፅታ መቀየር ተችሏል።
የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ኅላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ እንደገለጹት አገራዊና ክልላዊ ኢንሼቲቮችን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በኮሪደር ልማቱ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማትና የስማርት ከተማ ግንባታ የተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማቱ ከ118ሺህ በላይ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ሱለይማን የኮሪደር ልማቱ በ35 ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሮች፣ በክ/ከተሞችና በመሪ ማ/ቤቶች በ151 ከተሞች የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት እየተተገበረ እንደሚገኝ የገለጹት ም/ቢሮ ኀላፊዉ 281 ፕሮጀክቶች ተለይተው 96 ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁ፣ 62 ፕሮጀክቶች ከ50% በላይ የሆኑ፣ 52 ፕሮጀክቶች ከ50% በታች አፈጻጸም ያላቸው ሲሆን 62 ፕሮጀክቶች ደግሞ በጅምርና በጨረታ ሂደት ላይና 9 ፕሮጀክቶች በተለያየ ችግር ምክንያት ወደ ስራ ያልገቡ ናቸዉ ብለዋል።
የመኖሪያ ቤት ልማት በከተሞች የሚስተዋለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ እንዲሁም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ቢሮዉ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ ሱለይማን በክልሉ መጠነ ሰፊ የቅድመ ዝግጅትና የትግበራ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ይህን የቤት ልማት ኢንሼቲቭ ከመንግስት አቅም ባሻገር የግሉን ዘርፍ፣ የልማት አጋሮችንና ማኅበራትን በማሳተፍ የቤት ልማት ስታንዳርዱ የተቀረጸ መሆኑን ገልጸዋል።
በሪልስቴት 1305 ቤቶች፣ በመኖሪያ ቤት ህ/ስ/ማኅ/ 37185 ቤቶች፣ በግለሰቦች 21783 ቤቶችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች 1726 ቤቶች በድምሩ 62ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ባለፉት አስር ወራት መገንባታቸውን አቶ ሱለይማን ጨምረዉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ሙሉጌታ ስመኝ