03/06/2026
ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሙስና ወንጀል የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት
****************
ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት በተገልጋዩ ህብረተሰብ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ባለ ግንኙነት የሚፈጸም ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ተገልጋዩ የህብረተሰብ ክፍል በህግ ክርክሮች እና በአስተዳደር አካላት የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለማግኘት ወደ ተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፊት ይቀርባሉ፡፡
በዚሁ ሁኔታ አገልግሎት ፈልጎ የቀረበው ተገልጋይ እንደ ጉዳዩ ባህሪ በህግ እና አሰራር በተቀመጠ ምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ እልባት አግኝቶ መሸኘት አለበት፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ተገልጋዮችን ተገቢ ላልሆነ እንግልት በመዳረግ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዲያባክኑ በማድረግ፣ ለከፋ ምሬት እና ተስፋ በመቁረጥ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ይሆናል፡፡
ያለአግባብ ጉዳይ ማጓተት በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 18 መሰረት ማንኛውም የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ኃላፊ ወይም ሠራተኛ በኃላፊነቱ በሥራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲል በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለውን ማንኛውንም ሰው ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት በማሰብ ከህግ፣ ከመመሪያ ወይም ከተለመደው አሰራር ውጪ ያለበቂ ምክንያት ጉዳዩን ያልወሰነ፣ ያዘገየ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ እንደሆነ እንደ ጉዳዩ ታይቶ በገንዘብ ወይም በእስራት ይቀጣል፡፡
በአዋጁ እንደተደነገገው ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሙስና ወንጀል የሆነበትን መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም መሰረት የሙስና ወንጀሎች በመሰረታዊነት የሚፈጸሙት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለአንዱ ወገን በተለያዩ ምክንያቶች በማዳላት ሌላውን ወገን ለመጥቀም በማሰብ ነው።
የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች ጉዳይን አለአግባብ የማጓተት ተግባር የሚፈጽሙት ባለጉዳዩ በመመላለስ ምክንያት ከሚደርስበት እንግልት ለማምለጥ ሲል ገንዘብ እንዲከፍላቸው ተጽእኖ ለማሳደር አልያም ባለጉዳዩ ተማሮ ጉዳዩን መከታተሉን እንዲተወው በማድረግ የባለጉዳዩን መብት ለመረጡት ሌላኛው ሰው በማስተላለፍ በዚህም የሚከፈላቸውን ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ሆኑ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የህዝባዊ ድርጅቶች ተገልጋዮቻቸውን ሲያስተናግዱ አገልግሎት ወይም ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ ያለውን ልዩ ባህሪ ግምት ውስጥ በማስገባት በህግ እና በአሠራር ሥርዓት እንዲሁም የተለመዱ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ለተገልጋዮቻቸው በተገቢው ጊዜ ውሳኔ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ያለ በቂ ምክንያት ህግ እና አሰራርን በመጣስ ተገልጋዮችን ለማንገላታት እና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት እንዲሁም አገልግሎት ጠያቂው ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ጉዳይን ያለበቂ ምክንያት ማጓተት በህግ የሚያስጠይቅ እና የሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል ተግባር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ተገልጋዩ ማህበሰረብ በመንግስትም ይሁን ህዝባዊ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄድ በህግ እና አሠራር ስርዓት የተቀመጡ የአሰራር ደረጃዎችን ተረድቶ በዛ ውስጥ ውሳኔ እንዲያገኝ መጠየቅ እና ይህ በማይሆንበት ጊዜ ጉዳዩን ያለ በቂ ምክንያት የሚያጓትቱ የመንግስት እና ህዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች ላይ የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በመጠቆም ተባባሪ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
ትውልድን በሥነምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!
የሙስና ወንጀል መጠቆሚያ አማራጮችን፣ ወቅታዊ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት👇🏾
ሞባይል መተግበሪያ
ስልክ ተጠቃሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details...
or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id659366231
ለሀብት ማሳወቅና ምዝገባ፦ https://feaccears.gov.et/
ዌብሳይት፦ https://www.feacc.gov.et
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/
ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc
ዩትዩብ፡- https://www.youtube.com/-corrupti149
ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን።