02/06/2026
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል በስኬትና በታላቅ ድል መጠናቀቁ ተገለጸ።
በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የተካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በከፍተኛ ስኬት ስልጡን እና ህዝባዊ ተሳትፎ በጎላበት መልክ በታላቅ የህዝብ ድል መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ተወዳዳሪ የሌለው ሚና ለተጫወቱት የክልሉ ፖሊስ፣ ለጀግናዉ የመከላከያ፣ የፌደራል ፀጥታና የብሔራዊ ደህንነት አካላት ፣ለክልሉ ሚሊሻና ሰላም አስከባሪ እና ለመላዉ ህዝባችን በሙሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የላቀ ምስጋናና እውቅና አቅርቧል።
ሁሌም ሰላምና ልማትን ቀዳሚ የሚያደርገው የክልሉ ህዝብ የምርጫ ካርድ ከመውሰድ ጀምሮ በምርጫው ዕለት በታላቅ ትዕግስት እና ስነ-ስርዓት ድምፅ እስከመስጠት ድረስ ያሳየው ፍቅርና ሀገር ወዳድነት የታሪክ ማህደር የማይረሳው መሆኑን ገልጿል።
በምርጫው ዕለት ህብረተሰቡ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ በመውጣት በክልሉ በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ያከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ያለምንም መሰላቸት እስከ ምሽት ሰአት መከናወኑን አረጋግጧል።
ህብረተሰቡ ረጅም ሰልፎችን በታጋሽነት በመሰለፍ፣ የመምረጥ መብቱን በአግባቡ መጠቀሙ የሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ባህሉን ያሳየበትና ለምርጫው ስኬታማነት ትልቁን ድርሻ ያበረከተበት መሆኑንም ጠቁሟል።
ምርጫው የክልሉን ህዝብ ብስለት፣ ሰላም ወዳድነት እና ለሀገር ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም ለዓለም ያስመሰከረበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑንም ዋና ጠቅላይ መምሪያው አመላክቷል።
ሀገራዊ ምርጫው በስኬት ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን የህግ ማስከበር ስራቸውን በብቃት ለተወጡት ለክልሉ ፖሊስ አባላት፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ለብሔራዊ ደህንነት አካላት፣ለክልሉ ሚሊሻና ሰላም አስከባሪ አካላት በሙሉ ታላቅ አክብሮትና እውቅና ሰጥቷል።
የጸጥታ ኃይሉ ሂደቱን በበላይነት በመምራትና የእያንዳንዱን አካባቢ ህብረተሰብ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በማንቀሳቀስ፣ ከህዝብ የተውጣጡ የሰላም ኮሚቴዎችንና አደረጃጀቶችን ከራሱ የጸጥታ መዋቅር ጋር በማስተሳሰር የጋራ የሰላም ግንባር መፍጠር በመቻሉ ሰላሙን ማረጋገጥ መቻሉንም አረጋግጧል።
ይህንን ስራ ስኬታማ ለማድረግ የጸጥታ ኃይሉ አባላት ሌት ከቀን ያሳዩት ከፍተኛ ልፋት፣ ድካም እና ተጋድሎ በአንዳንድ ቦታዎች የምርጫውን ሂደት ለማደፍረስና ሁከት ለመፍጠር አልመው የተንቀሳቀሱ ህገ-ወጥ አካላትን የጥፋት ሴራ ቀድሞ በተዘጋጀ ስልታዊ የመከላከል እቅድ ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ መቻሉንም አመላክቷል ።
የጸጥታ ኃይሉ የተጣለበትን ታሪካዊ አደራ የመወጣት ጀግንነት፣ ሙያዊ ብቃት እና የገባውን ቃልኪዳን በታማኝነት በመፈጸም የህዝቡን ደህንነት በልዩ ጥንቃቄ የማስጠበቅ ስራ፤ ከተቋማዊ ኩራት ባሻገር ለክልሉና ለሀገሪቱ ታላቅ ክብርን ያጎናጸፈ ተግባር በመሆኑ ላቅ ያለ ምስጋናና እውቅና ሰጥቷል።
ምርጫውን ለማወክ የሞከሩ ማናቸውንም የፀረ-ሰላም ኃይሎች የጥፋት አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ያከሸፈ ታላቅ የህዝብ ድል የተመዘገበው ህዝቡ ያሳየው አስተዋይነት እና የሰላም ባለቤትነት ስሜት በመኖሩ እንደሆነም አክሏል።
ለታሪካዊ ድሉ መገኘት ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም፣ መረጃዎችን በወቅቱ በመለዋወጥ እና ለሰላም ጥበቃው ግንባር ቀደም ጠባቂ በመሆን ያሳየው ጠንካራና የተቀናጀ ጥምረት ዋነኛ መሠረት ነበር ተብሏል።
በምርጫው ወቅት የታየውን መልካም የህዝብና የፖሊስ ቅንጅታዊ አሰራርና አደረጃጀት ይበልጥ በማጠናከር የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ለሲቪክ ማህበራት፣ ለብዙሃን መገናኛ አካላት ፣ ለዉጭና የአገር ዉስጥ ታዛቢዎች እና ለሰላም ወዳዱ ማህበረሰብ በሙሉ በድጋሚ የላቀ ምስጋና በማቅረብ፤ የተጀመረውን የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ በጋራ ለማስቀጠል የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጥሪ አስተላልፏል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
ግንቦት 25/2018 ዓ.ም
ባህር ዳር