11/04/2023
የከባድ ስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች
በፅኑ እስራት ተቀጡ
ተከሳሽ 1ኛ.አቶ እንቻለዉ ጌታቸዉ 2ኛ. አቶ አዝመራዉ ወንድምነህ 3ኛ. አቶ ስናማዉ ዘዉዴ 4ኛ. አቶ ሙሉጌታ ፈንታ የተባሉት ተከሳሾች የኢፌድሪ የወንጀል ህግ 669/3/(ለ) ስር የተመለከተዉን በመተላለፍ በ28/07/2015 ዓ.ም በሌሊት ባልታወቀ ሰዓት በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር እነራታ/08/ ቀበሌ ልዩ ቦታዉ የብራጌ ተብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ ላይ ንብረትነታቸዉ የአቶ ጌታቸዉ ብናልፍ የሆኑትን 04 (አራት) ከብቶች ቤት ከፍተዉ የሰረቋቸዉ በመሆኑ በፈፀመዉ ከባድ የስርቆት ወንጀል ተከሰዋል ሲል ዐ.ህግ ክስ መስርቶ አቅርቧል።
የአዋበል ወረዳ ፍርድ ቤት ለተከሳሾች መጥሪያ እንዲደርሳቸዉ በማድረግና በችሎት ቀርበዉ የክስ ቻርጅ ተነቦላቸዉ የእምነት ክህደት ቃላቸዉን እንዲሰጡ ሲጠየቁ ክሱን አንቃወምም፤ የወንጀሉንም ድርጊት ፈፅመናል በማለት በዝርዝር አምነዉ ቃላቸዉን የሰጡ በመሆኑና ዐ.ህግ በአስተያየቱ በአመኑት መሰረት የጥፋተኝነት ዉሳኔ ይሰጥልኝ በማለቱ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ዉሳኔ ከሰጠ በኋላ ማክበጃና ማቅለያ ምክንያት በመቀበል ተከሳሾችን ያርማል ሌለዉን የህብረተሰብ ክፍል ያስተምራል በሚል አራቱም ተከሳሾች እያንዳንዳቸዉ በ08 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የአዋበል ወረዳ ፍርድ ቤት በ29/07/2015 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት የቅጣት ዉሳኔ ሰጥቷል።
የአዋበል ወረዳ ፍርድ ቤት