27/05/2026
ሲዳማ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሆን በጋራ ለመስራት ቃል ገቡ
በሲዳማ ክልል ውስጥ የሚገኙ 23 ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤት የተዘጋጀ ውይይት በማካሄድ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተአማኒ፣ ነጻ እና ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትብብር ለመስራት ቃል ገብተዋል።
የውይይት መድረኩ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ በክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ እና በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በለጠ ሰጌቦ መሪነት ተካሂዷል። በመድረኩ የተለያዩ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈው ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ዋና ትኩረት የፖለቲካ ተፎካካሪዎች መካከል መተማመንን ማጠናከር፣ የምርጫ ሂደትን ማሻሻል እና ከቀድሞ ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ለማስፈጸም ሁሉም በትብብር መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
ተሳታፊዎቹ በምርጫ ወቅት ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን በቅድሚያ ለመለየት፣ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ሰላማዊ የፖለቲካ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው በአጽንኦት አንስተው ልዩነቶች በግጭት ሳይሆን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል።
በመድረኩ ውስጥ የምርጫ ሕጋዊ ሂደቶችን ማክበር፣ የምርጫ ደንቦችን በትክክል መፈጸም እና ሕዝቡ ፍላጎቱን በነጻነት እንዲገልጽ ማስቻል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመግለጽ የፖለቲካ ውድድር በኃይል ሳይሆን በሐሳብ መሆን እንደሚገባም በግልጽ ተነስቷል።
በምርጫ ሂደት ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ሕጋዊ አሰራር እንዲጠናከር ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶ የምርጫ መርሆዎች በጥብቅ እንዲከበሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም ተሳታፊ ፓርቲዎች 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝብ ተአማኒ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በቀጣይ በትብብር ለመስራት ቃል በመግባት ምርጫው ለሀገራዊ ሰላም ወሳኝ እንደሆነ አስረግጠዋል።
ዘገባው ፦ሲዳማ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ግንቦት 19/2018