05/06/2026
መልካም ስነ-ምግባር በአንድ ጀምበር አይገነባም፤ ከልጅነት ጀምሮ በተከታታይ አርአያነት፣ ምክር፣ ፍቅር እና ትክክለኛ መመሪያ በመስጠት ይጎለብታል። መልካም ስነ-ምግባር በሁሉም የእድሜ ክልሎች ሊጎለብት ቢችልም፣ በተለይ በህፃንነትና በወጣትነት ዘመን ይበልጥ መሰረቱን ይጥላል።
☞ ከ0–6 ዓመት፤ ህፃናት የወላጆቻቸውን እና የአካባቢያቸውን ባህሪ በመኮረጅ መሰረታዊ ስነ-ምግባር ይማራሉ።
☞ ከ7–12 ዓመት፤ የሃላፊነት፣ የትብብር፣ የህግና የስርዓት ክብር እሴቶች ይጠናከራሉ።
☞ ከ13–18 ዓመት፤ የግል እሴቶች፣ ታማኝነት፣ ተጠያቂነት እና የስነ-ምግባር ውሳኔ የመስጠት ችሎታ ይዳብራል።
☞ ስለዚህ መልካም ስነ-ምግባር በተለይ በህፃንነት (0–12 ዓመት) የሚጣል መሰረት ነው፤ ከዚያም በወጣትነትና በጉልምስና ይጠናከራል።
“ልጅ በልጅነቱ የተማረው ስነ-ምግባር በህይወቱ ሁሉ ይመራዋል።” የሚለው አባባልም ይህንን ያሳያል። በመሆኑም ወላጆች የልጆቻቸው መልካም ስነ-ምግባር እንዲጎለብት የሚከተሉትን ማድረግ ይገባቸዋል፤
☞ አርአያ መሆን፤ ልጆች ከሚነገራቸው ይልቅ ከሚያዩት ይማራሉ፤ ታማኝነት፣ አክብሮት፣ ሀላፊነት እና ትህትና በተግባር ማሳየት፤
☞ ጥሩ ምክርና መመሪያ መስጠት፤ ስለ ትክክልና ስህተት፣ ሰውን ስለማክበር እና ስለ ተጠያቂነት ቀጣይነት ባለው መልኩ መነጋገር፤
☞ ጥሩ ባህሪን ማበረታታት፤ ልጆች መልካም ተግባር ሲያሳዩ ማመስገንና ማበረታታት።
☞ ሥርዓትና ደንብ ማስያዝ፤ በቤት ውስጥ ግልጽ የሆኑ ህጎችና ደንቦችን ማስቀመጥ እና በተመሳሳይ ሁኔታ ማስፈጸም፤
☞ ከልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ፤ የልጆችን ችግሮቻቸውን ማዳመጥ፣ ሃሳባቸውን ማክበር እና ጥሩ ግንኙነት መፍጠር፤
☞ መልካም ወዳጅና አካባቢ እንዲኖራቸው መርዳት፤
☞ የመረዳዳትና የመተባበር ባህል ማስተማር፤ ለሌሎች ማሰብ፣ መርዳት እና ማካፈል እንዲለምዱ ማበረታታት፤
☞ የሐይማኖትና የማህበረሰብ እሴቶችን ማስተማር፤ ሥነ-ምግባራዊ እሴቶችን የሚያጠናክሩ ትምህርቶችን ማስተላለፍ ።