04/06/2026
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በተግባር አሳይቷል፦ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች
******************
ባለፈው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ድምፅ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በታሪካዊ መልኩ የተወጡበት ዕለት እንደነበር የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በሁሉም አካባቢዎች ምርጫው በሕዝቡ ንቁ ተሳትፎና ደማቅ አጋርነት የተከናወነ ሲሆን፤ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችም በዕለቱ የነበረውን ዝናብና ፀሐይ ሳይበግራቸው፣ ዲሞክራሲ መብታቸውን በመጠቀም ይበጀናል ላሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃቸውን በነፃነት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ረጃጅም ሰልፎችን በትዕግሥት በመጠበቅ ከንጋት እስከ ምሽት በትጋት ድምፅ ሲሰጡ መዋላቸው ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት መሥረታና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ የድምፅ መስጫውን ዕለት በከፍተኛ ጉጉት ሲጠብቁ እንደነበር ያወሱት ነዋሪዎቹ፥ በዕለቱ በላቀ የሀገራዊ ኃላፊነት ስሜት ድምፃቸውን ማሳረፋቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም በምርጫው አሸናፊ በመሆን በቀጣይ ሕዝቡን የሚያስተዳድረው አካል የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻልና ጥያቄዎችን ለመመለስ በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ኢቢሲ