07/07/2024
ከቤህነን ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የተከበራችሁ የድርድታችን አባላት እና ደጋፊዎች
የተከበራችሁ መላው ሕዝባችን
ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በክልላችን የተካሄደው ድጋሜ እና ጠቅላላ ምርጫ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) የተፈጠረዉ ውስጣዊ ችግሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባልፈታበት ድርጅቱ እንደ ድርጅት ሙሉ ቁመና ይዞ ባልተገኘበት እና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ታፍነው በታስሩበት የድርጅቱ ሊቀመንበር ጨምሮ ህዝባችን አምኖ የሰጧቸው ኃላፊነቶችና አደራ ወደ ግል ጥቅማቸው አዙሮ በመሸጥ ድርጅቱን አሳልፎ ለክልሉ መንግስት በሰጡ እና በሆድ ተገዝቶ ከክልሉ መንግስት ጋር በተጣበቁ አፈንጋጭ ግለሰቦች (አንጃ) እና ከክልሉ መንግስት የሚደርሱ ጫናዎች እንግልትና አስራት ባለበት እንዲሁም እንደ ድርጅት ምንም ዓይነት የይምረጡኝ ቅስቀሳ እና የተሟላ ዝግጅት ባልተደረገበት ድርጅቱን ለማዳን ሲባል የገባንበት ምርጫ ነው፡፡
ከምርጫው በፊት የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ውስን ግብረ አበሮቹ የተላላኪነት ተልዕኮአቸውን ለመፈጸምና የተሰጣቸውን ሥልጣን ለማስጠበቅ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ በመተላለፍ ለክልሉ መንግስት ታማኝና አመቻች ተወዳዳሪ ለመሆን ከዚህ በፊት በ2013 ዓ.ም የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩ ዕጩዎች በመሰረዝ ያለ ምንም የማዕከላዊ ኮሚቴ ዉሳኔ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ሌሎች ግለሰቦች እጩ ተወዳዳሪ አድርጎ በመመልመል ለምርጫው ለማቅረብ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ ይህ ሙከራው ግን ግቡን ሳይመታ እንዲከሽፍና የቀረቡ ግለሰቦች በህጉ መሠረት ከምርጫ እንዲሰረዙ እና የ2013 ዓ.ም ዕጩዎች በውድድሩ እንዲቀጥሉ ቦርዱ መወሰኑ የሚታወስ ነዉ ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ተላላኪ አንጃ ከክልሉ መንግስት ጋር በመጣበቁ ምክንያት የክልሉ የፍትህ ተቋም ሊያግዘን ይችላል ብሎ በማሰብ የተከበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ ለማሻር በክልሉ ላይ ክስ ቢመሰርትም ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ክስ መርምሮ ከምርጫ ሕግ ጋር በማገናዘብ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አንጃው የሽንፈት ቅሌቱን መከናነቡ የሚናስታዉሰዉ ጉዳይ ነዉ ፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ደካማና ተላላኪ ግለሰብ ለክልሉ መንግስት ታማኝ ተወዳዳሪ በመሆን እራሱ የሚወዳደርበትን የመንጌ ወረዳ ምርጫ ክልል ጨምሮ የኦዳ ቡልዲግሉ ወረዳ ምርጫ ክልል የይስሙላ ታዛቢዎች በመመልመልና በመመደብ የክልሉ መንግስት ብቻውን እንደፈለገ እንዲፈነጭ እንድሁም ማጭበርበርና ስርቆት እንዲፈጽም በማድረግ የህዝባችን ድምፅ አሳልፎ ለክልሉ መንግስት ሰጥቷል፡፡ በመሆኑ ቤህነን በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ሆነ በምርጫዉ ሲወዳደር በሶስቱም የወረዳ ምርጫ ክልሎች በአብዛኛዉ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎቹ የታሰሩበትና የተባረሩበት በመሆኑ የክልሉ መንግስት ካድሬዎች ; አመራሮች እና ሚሊሽያዎች በፈጠሩት ከፍተኛ ጫናና ማስፈራራት መራጩ ሕዝብ በነፃነት የሚፈልገዉ አካል ወይም ፓርቲ ሊመርጥ አልቻለም በዚህ ሁኔታ የመንግስት አካላት በምርጫዉ እንደፈለጉ እንድሆኑ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች መንግስት ከማጭበርበር አልፎ የድምፅ መስጫ ወርቀት መራጩ ሕዝብ በተሰለፈበት ቦታ ላይ ተለጥፎ ሕዝቡ ተገዶ የብልፅግና ፓርቲ እንዲመርጥ ተባባሪ ሆኗል ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በክልሉ የተካሄደዉ ምርጫ ፍተሐዊ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ አይደለም ብሎ ቤህነን አቋሙን ይገልጻል ፡፡የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው ሕዝባችን ይህ ተላላኪ ግለሰብና አንጃ የሰሯቸው አስነዋሪ ተግባራት እና የክልሉ የብልፅግና መንግስት የሚፈጽማቸዉ ጫናዎች፣እስራትና እንግልት ሳትበገሩ በአሶሳ ወረዳ ምርጫ ክልል ለተወዳደርን የድርጅታችን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከ46ቱ የኢንዲጅነሱ የምርጫ ጣቢያዎች 75 በመቶ ዉጤት እንዲናገኝ አክብራችሁን በሰጣችሁን ድምፅ የብልፅግና ዕጩዎች ማሸነፋችን እኛ ብቻ ሳይሆን ብልፅግና እራሱ የሚመሰክረው ጉዳይ ሲሆን ከዚህ ሁሉ ጫናና ትንቅንቅ በአሶሳ ወረዳ ምርጫ ክልል ብልፅግና ሊያሸንፍ የቻለው በሌላ አካል ታዝሎና ታክኮ መሆኑ የምርጫ ዉጤቱ ያረጋገጠዉ ጉዳይ ነዉ ፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሲሆን ሕዝባችን በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለድርጅታችን ቤህነን ያለው ታማኝነትና ጥንካሬ ያስመሰከረበት ምርጫ በመሆኑ የበለጠ ሞራልና ብርታት የሚሰጠን ስለሆነ ለቀጣዩ ዝግጅታችን የደውል ምልክት ነው፡፡
የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መላው ሕዝባችን ማንኛውም አካል ወይም ቡድን የፈለገውን አካል ወይም ፓርቲ የመምረጥ ሕገ-መንግስታዊ መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት ሳይኖራችሁ የመረጠንና ያልመረጠንን አካል ሁሉ ሙሉ ክብር ያለን መሆኑ አዉቃቹ ከወትሮው የበለጠ በትጋት፣በቁርጠኝነትና በታማኝነት ሥራችሁን አጠናክራችሁ ትቀጥሉ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም አሶሳ