07/10/2026
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከወረዳው መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ጽሕፈት ቤት በመገኘት አጠቃላይ የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴና አስተዳደራዊ ሥራዎች ዙሪያ የድጋፍ ተኮር ውይይት አካሄደ።
በውይይት መድረኩ ተቋሙ ከተቋቋመለት ዓላማ፣ ርዕይና ተልዕኮ አንፃር አሁን ያለበትን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና የአመራር ብቃት በዝርዝር በጥንካሬና በእጥረት በየሥራ ሂደቱ ቀርቦ ተገምግሟል።
መድረኩን የመሩት የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሱራፊል ጌታነህ እንደገለጹት፤ የሥራዎች ሁሉ መጀመሪያ ዕቅድን በተገቢው መንገድ በወቅቱና በአግባቡ ሰፋ አድርጎ ማቀድ፣ ለእቅዱ ተገዥ መሆን፣ ተቋማትን በመርህ፣ በመተማመንና በመግባባት በኃላፊነት ማስተዳደር ያስፈልጋል ብለዋል።
ጊዜውን የዋጀ፣ ጥንቃቄ የተሞላበትና ሥራ ተኮር መግባባት በመፍጠር በባለቤትነትና በቁጭት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አክለውም ተቋሙ አቅምን አሟጦ በመጠቀም ፈጣንና ፈጠራ የተሞላበት በመሆን፣ ወረዳዊና ተቋማዊ ሥራዎችን ከሕዝብ ወደ መንግሥት ከመንግሥትም ወደ ማኅበረሰቡ ማድረስ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው ማሞ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም ከሚጠበቅበት ሚና አንፃር አሁን ያለው አፈፃፀም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ከጠባቂነት ችግር በመውጣት በእውቀት፣ በኃላፊነት፣ መረጃን ከትክክለኛ ምንጭ በማነፍነፍ፣ አደረጃጀትን ጠብቆና በጋራ በመቀናጀት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተቋሙ ባለሙያዎች በበኩላቸው የተደረገው የድጋፍና የውይይት መድረክ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም እና በማሻሻል፣ ያለውን ጥንካሬ በማስቀጠል ቀጣይ ተቋሙ የተሻለ አፈፃፀም እንዲያመጣ ትልቅ እገዛ እንዳለው በመገለጽ አመስግነዋል።