05/06/2026
ዜና ችሎት
በሙስና ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
ግንቦት 28/2018 ዓ.ም የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የንብረት ክፍል ሰራተኛ በነበረው ተከሳሽ ሐብቴ ዳንጋርሶ ላይ የቀረበውን የሙስና ወንጀል ክስ መዝገብ መርምሮ ውሳኔ አስተላልፏል።
ተከሳሹ በአረካ ከተማ አስተዳደር ሀንጋዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የንብረት ክፍል ሠራተኛና ቁልፍ ያዥ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ላይ ከተቋሙ ንብረት ክፍል 16 ካርቶን የዋጋ ግምቱ 585,738 (አምስት መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት) ብር የሆነውን የተማሪዎች እና የመምህራን መጻሕፍትን ለግል ጥቅሙ ለማዋል በባጃጅ ሲጭን እጅ ከፍንጅ ተይዞ በከባድ እምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ተከሷል።
የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ ማስረጃ የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እና በ5,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
ዘገባው:- የወላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ክፍል