14/10/2025
ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀትና ፍትህን በማስፈን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃት መቀነስ እንደሚቻል ተገለፀ
አርባ ምንጭ፦ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (ጋሞ ዞን መ/ኮሚዩኒኬሽን
"በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በጋራ እንከላከል" በሚል መሪ ቃል የጋሞ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ከዞኑ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በብርብር ከተማ ተካሂዷል።
የጋሞ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት አፌ-ጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍ በመድረኩ ማጠቃለያ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት መከላከል የሁሉም ሕብረተሰብ ተግባር እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው በተለይ በቅርብ ሰዎች እያደረሰ ያለውን ጥቃት ዜጎች በሕግ ከማስጠየቅ ባለፈ ማውገዝ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀትና ፍትህን በማስፈን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃት መቀነስ እንደሚቻል የጠቆሙት አፈ ጉባኤዋ በእጅ መንሻ የሚንቀሳቀሱ የመንግስት አካላትን ለማረም በርካታ ተቋማት ወደ ሪፎርም መግባታቸውንም አስረድተዋል።
የጋሞ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት ሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ዳርዛ በበኩላቸው በሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላትን መከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
አቶ ዳንኤል አክለውም እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን በተሳሳተ መንገድ በሽምግልና ለመጨረስ የሚሞክሩ አካላት ከድርግታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የብርብር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም አይካ በሰጡት አስተያየትም በተለያዩ ስልቶች በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀመውን ወንጀል ለመቀነስም ሆነ ለመከላከል እያንዳንዱ ግለሰብ በኃላፊነት መስራት እንደሚገባ ገልፀው መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ወንጀል ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ የገለፁት ተሳታፊዎቹ ጥቃት ደርሶባቸው በፍትህ ሂደት ላይ የሚከሰቱ እንግልቶችንም ማስቀረት ይገባል ብለዋል።
በትምህርት ቤቶችም በስርዓተ ፆታና በስነ-ምግባር ዙሪያ የሚሰሩ ክበባት መጠናከር እንዳለባቸው ተጠይቋል።
በሐይማኖት ተቋማት ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ቢሰጡ ውጤት እንደማያመጣ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ከጋሞ ዞን፣ ከደቡብ ዕዝ መከላከያ እና ከብርብር ከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።