03/06/2026
7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የህዝቡን የዴሞክራሲ ተሳትፎና የሰላም ባህልን ያረጋገጠ ነው "የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ፌደሬሽን
ግንቦት 26/2018 ዓ.ም
የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል ።
የክልሉ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል ሳሙኤል እንደገለጹት፣ ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባገኘው የምርጫ ታዛቢነት ፈቃድ መሰረት ተግባራትን ሲያከናውን እንደነበረ ጠቁመዋል ።
በክልሉ 54 የምርጫ አስተባባሪዎችንና ከ2000 በላይ ታዛቢዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በማሰማራት የምርጫውን ሂደት ከቅድመ ዝግጅት እስከ ድምጽ ቆጠራ ድረስ በቅርበት መከታተሉን አስታውቀዋል።
በክልሉ የተካሄደው ምርጫ መራጮች ድምጻቸውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መስጠታቸውን የገለፁት ፕሬዝደንቱ ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአረጋውያን እና የሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የዴሞክራሲ ባህልን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ወጣቶች ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ምህረቱ ዳና በበኩላቸው የክልሉ ወጣቶች በምርጫ አስፈጻሚነት፣ በታዛቢነት፣ በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ በመራጭነትና በተመራጭነት ባሳዩት ንቁ ተሳትፎ ለዴሞክራሲ ግንባታ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።
ለምርጫው ስኬት የድርሻውን አስተዋጽኦ ላበረከቱት ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ምህረቱ ምርጫው የህዝቡን የዴሞክራሲ ተሳትፎና የሰላም ባህልን ያረጋገጠ ስለመሆኑ ጠቁመዋል ።
መላው የህብረተሰብ ክፍል በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ራሱን በመጠበቅ የምርጫ ቦርድ ውጤቱን ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል ።